ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦርነቱን በመቀስቀስና በማጋጋል ምዕራባውያንን ተጠያቂ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን በመቀስቀስ እና በማባባስ ምዕራባውያኑ ተጠያቂዎች ናቸው አሉ።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦርነቱ የተቀሰቀሰው እና የተስፋፋው "አሜሪካ እና አጋሮቿ የኃይል ጥማት ስላለባቸው ነው" በማለት ምዕራባውያኑን የወቀሱት በዛሬው ዕለት በሞስኮ ባደረጉት ብሔራዊ ንግግር ነው።
አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀረው የዩክሬኑን ጦርነት ዓለም አቀፋዊ የማድረግ ፍላጎት አላቸው ሲሉም ወቅሰዋቸዋል።
የጦርነቱን መነሻ እና አይቀሬነት የገመገሙት ፕሬዝዳንቱ፤ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወደ ምስራቅ አውሮፓ እያደረገ ያለውን መስፋፋት እና በሩሲያ ላይ ያሳዩትን ጠብ አጫሪነትም አውግዘዋል።
ፑቲን ለጦርነቱ መነሻም ሆነ ማጋጋል ተጠያቂዎቹ ከምዕራባውያኑ በተጨማሪ ዩክሬንን ከሰዋታል።
"ዩክሬን እና ዶንባስ ፍጹም የውሸት ምልክት ሆነዋል" ያሉት ፑቲን ምዕራባውያን ሃገራቱ የገቧቸውን መሰረታዊ ስምምነቶች ጥሰዋል እንዲሁም ተገቢ ያልሆኑ መግለጫዎችን ይሰጡ ነበር ብለዋል።
በተጨማሪም የኔቶን ጦር በማስፋት ለሩሲያ ስጋት ደቅነዋል ሲሉም ከሰዋል።
“ለጦርነቱ ዋነኛ ተጠያቁ እነርሱ ናቸው እኛም የነሱን ተግባር ለማስቆም የኃይል እርምጃ እየወሰድን ነው” ብለዋል።
በዩክሬን ጦርነት የሩሲያ ወታደሮች ጀግንነት አወድሰው ለነሱም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
ምዕራባውያን ሃገራት ለሁሉም ነገር ሩሲያውያንን ተጠያቂ ያደርጋሉም በማለት ጥፋተኝነታቸውን ለማዛወር እየሞከሩ ነው ብለዋል።
ምዕራቡ ዓለም ግጭቱን በማባባስ እንዲሁም የምጣኔ ኃብት ጦርነትም እየተዋጉ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዚህም ጦርነት በሌላ የምዕራቡ ዓለም ይህንን እንደማያሳኩ ቃል ገብተዋል።
ፑቲን የምዕራባውያኑ የምጣኔ ሃብት ማዕቀብ እንደታሰበው ሩሲያን አላሽመደመደም በማለት እንዳልተሳካ ተናግረዋል።
በተለያዩ ሃገራት በሩሲያ ላይ በተጣሉት ማዕቀቦችም እራሳቸውን እየቀጣቸው ነው በማለትም የዋጋ ግሽበት፣ በርካታ የንግድ ተቋማት መዘጋት እና በዓለም ላይ ያለውን የተከሰተውን የኃይል (ኢነርጂ) ቀውስም በምሳሌነት አንስተዋል።
የምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ የጣለው ማዕቀብ ፍጹም አልተሳካም ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በአማራጭነት በምዕራቡ ዓለም ላይ ያለውን ጥገኝነት የሚቀንስ አስተማማኝ የዓለም አቀፍ የክፍያ ስርዓት የመገንባት አስፈላጊነትንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ስህተቶቻችንን መድገም የለብንም። ምጣኔ ኃብታችንን እንዲወድም መፍቀድ የለብንም” ብለዋል።
የምዕራባውያን ማዕቀብ የተነደፉት የሩሲያን ሕዝብ ለማሰቃየት ነው ሲሉ የወነጀሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሆኖም ምዕራባውን በማዕቀቦቻቸው ያሰቡትን ለማሳካት አልተቻላቸውም ብለዋል። እንዲያውም አሉ ፕሬዝዳንቱ፤ የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ ሩብል በዓለም አቀፍ ግብይት ውስጥ ያለው ድርሻ “በእጥፍ ጨምሯል”።












