ለተሰንበት ግደይ በአውስትራሊያው ውድድር ማጠናቀቂያ ላይ የገጠማት ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቅዳሜ ዕለት በአውስትራሊያ በተደረገው 44ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በሴቶች ወርቅ እንደምታስገኝ ስትጠበቅ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ አትሌት ለተሰንበት ግደይ በውድድሩ የመጨረሻ ላይ ያልተጠበቀ ጉዳት ገጥሟት አሸነፊነትን አጥታላች።
ለተሰንበት የውድድሩን የአሸናፊነት መስመር ልታልፍ ጥቂት ሜትሮች ሲቃርት በድንገት በገጠማት ጉዳት እግሯ ለማዘዝ ተስኗት የድል ሪቫኑን ቀድማ መበጠስ ተስኗት ነበር።
በዚህ ጊዜ የአሸናፊነቱን ክብር ልትቀዳጅ ጥቂት ሲቀራት የወደቀችውን ለተሰንበትን አሰልጣኟ ኃይለ ኢያሱ ወደ ውድድር ሜዳው በመግባት እንድትነሳ በመርዳት የውድድሩን ፍጻሜ መስመር እንድታልፍ ቢያደርጋትም አትሌቷ ከውድድር ውጪ ሆናለች።
በዚህም ምክንያት ኬንያዊቷ ቢያትሪስ ቺቤት ውድድሩን ለማሸነፍ በቅታለች።
ለተሰንበት ሰኞ ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሰች ሲሆን፣ በዚህ አትሌቷን በገጠማት ጉዳይ ዙርያ አሰልጣኝ ኃይለ ኢያሱ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ በውድድሩ ስፍራ በነበረው ከባድ ሙቀት እና ሌሎችም ጉዳዮች ተደራርበው ጫና እንደፈጠሩባት ገልጿል።
የአውስትራሊያው ውድድር ከለተሰንበት አቋም አንጻር ብዙም የማያስቸግራት እና ውጤታማ ልትሆን የምትችልበት የአገር አቋራጭ ውድድር እንደሚሆን አሰልጣኟ ተስፋ አድርጎ ነበር።
በቅዳሜው የአገር አቋራጭ ውድድር ስፍራ የነበረው ሙቀት 30 እና 40 ሴንቲ ግሬድ በመሆኑ ወበቁ ለአትሌቶቹ ፈታኝ ሊሆን ስለሚችል አሰልጣኟ እና ለተሰንበት ሙቀቱን ለመቋቋም የተለያዩ ዘዴዎችን ለመጠቀም ወስነው ነበር ሩጫው የተጀመረው።
አሰልጣኝ ኃይለ እንዳለው ለተሰንበት ውድድሩን በብቃት ለማሸነፍ በሚያስችላት ደረጃ ላይ ነበረች። “በአቅም ደረጃ ለተሰንበት ችግር አልነበረባትም። ለውድድሩ የሚመጥን ብቃት ላይ ሆና ነው የሄደችው።”
ነገር ግን በውድድሩ ስፍራ የነበረው የሙቀቱ መጠን፣ ቀደም ሲል ያደረገቻቸው ተደራራቢ ውድድሮች የፈጠሩባት እረፍት ማጣት እንዲሁም ወደ አውስትራሊያ ያደረገችው ረዥም ጉዞ ባላት ብቃት ላይ ፈታኝ ሁኔታን እንደፈጠረባት ይጠቅሳል።
በውድድሩ ላይ “አንድ ኪሎ ሜትር ሲቀር አወጣጧ ጥሩ አልነበረም። እንዲሁም ሙቀቱ ጋር ተደርቦ ትንሽ የቴክኒክ ችግር ነበር። ፈጥና ነው ዳገቱን የወጣችው። አንዲት ልጅ ነበር የምትፎካከራት ዳገታማ ቦታ ቆርጣ አንድ ሰከንድ ጥላት ሄዳ ነበር” ይላል የመጨረሻውን የውድድሩን ሁኔታ ሲያስረዳ።
ይህ ሁኔታ እና ለተሰንበት እና አሰልጣኟ ከውድድሩ ቀደም ብለው ባወጡት ታክቲክ መሠረት ወደ ፍጻሜው ስትቃረብ ከቀሪዎቹ ተፎካካሪዎቿ ተለይታ ፈጥና ለመውጣት ከተስማሙበት ርቀት እና ጊዜ መሳሳት እንደነበር ኃይለ ለቢቢሲ ገልጿል።
“ይህ የአወጣጥ መዛባት እና ባለው ከባድ ሙቀት ምክንያት በሰውነቷ ውስጥ ያለው ፈሳሽ በላብ አማካይነት በመሟጠጡ (ዲሃይድሬሽን) ከባድ ጫናን አሳድሮባት ወደ መጨረሻው በተቃረበችበት ጊዜ እግሯ ልፍስፍስ ብሎ መራመድ አቅቷት ወደቀች” በማለት የገጠማቸውን አሳዛኝ ሁኔታ ተናግሯል።
አሰልጣኝ ኃይለ ኢያሱ ጨምሮም ለተሰንበት ግደይ ከአውስትራሊያው ውድድር በፊት ያለበቂ እረፍት ተከታታይ ውድድር ማድረጓ እንድትዳከም እንዳደረጋት እና ይህም ለቅዳሜ ዕለት ክስተት ምክንያት እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለተሰንበት ግደይ በአሁኑ ወቅት በዓለም ተጠቃሽ ከሆኑ የረጅም ርቀት ሴት ኮከብ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። በዚህም ምክንያት በተለያዩ አገራት በሚካሄዱ ታላላቅ ውድድሮች ላይ በመጋበዝ እንድትሳተፍ በሁሉም የውድድር አዘጋጆች ትፈለጋለች።
ለተሰንበት “ባለፈው ታኅሣሥ ወር ስፔን ቫሌንሺያ ላይ በተካሄደ የማራቶን ውድድር ላይ 2 ሰዓት 16 ደቂቃ 46 ሰከንዶ ሮጣለች። ከዚህ ውድድር በኋላ በቂ እረፍት ሳታደርግ ወደ አውስትራሊያው የአገር አቋራጭ አምርታለች። ይህም በአራት ሳምንት ውስጥ የተደረገ ነው።”
በተጨማሪም ለተሰንበት ከቫሌንሺያው ውድድር ከሁለት ሳምንት በኋላ ጃንሜዳ የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ ተሳትፋለች። እነዚህ ተደራራቢ ውድድሮች ደግሞ ሰውነቷ የሚያስፈልግውን የማገገሚያ ጊዜ እንዳያገኝ እንዳደረገው አሰልጣኟ ይናገራል።
“ይህ የአውስትራሊያው ውድድር ለለተሰንበት ብዙም የማያስቸግር ከአቅም በታች የሆነ ነው። ነገር ግን ከፌዴሬሽን ጋር ተወያይተን አገር ለማገዝ በሚል ነው እንድትሳተፍ የተደረገው።”
አሰልጣኟ ጨምሮም ለተሰንበት የአገር አቋራጭ ውድድሩን ስታደርግ ከረዥም ጊዜ በኋላ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ገልጾ፣ የነበረው ሙቀት ጭቃ፣ አቀበት እና ቁልቁለቱ ሁኔታውን ከባድ እንዳደረገው ጠቅሷል።
ለተሰንበት ግደይ በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር ለመጨረሻ ጊዜ የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ የተሳተፈችው። ከዚያ ወዲህ ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና ጦርነቱን ተከትሎ ለአምስት ዓመታት ያህል የትራክ እንጂ የአገር አቋራጭ ውድድርም ሆነ ልምምድ እንዳላደረገች አሰልጣኟ አስታውሷል።
ከውድድሩ ከባድነት የተነሳ ሌሎች አትሌቶች ለአገር አቋራጭ ውድድር እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ዝግጅት እና ልምምድ ያደርጋሉ የሚሉት አሰልጣን ኃይለ፣ ለተሰንበት ግን ለውድድሩ በፌዴሬሽኑ ጥሪ ከተደረገላት በኋላ የአንድ ወር ልምምድ ብቻ ነበር ያደረገችው።
“ለተሰንበት አቅም ስላላት ትወጣዋለች በሚል፣ አገርን ለማገዝ እና አስተዋጽኦም ለማድረግም ነበር በዚህ ውድድር ላይ እንድትሳተፍ የተደረገው። ነገር ግን አየሩ ሁኔታ በፈጠረባት የሰውነት ፈሳሽ መሟጠጥ (ዲሃይድሬሽን) ምክንያት የታሰበው አልተገኘም።”
ምንም እንኳን ለተሰንበት ተደራራቢ ጫና ቢያጋጥማትም የውድድሩ አብዛኛውን ክፍል በብቃት በመሸፈን በበላይነት ወደ ፍጻሜው መስመር ስትቃረብ እግሯ እንደፈለገችው መሮጥ ብቻ ሳይሆን ለመራመድ አዳገታት፣ ተዝልፍልፋም ወደቀች።
በዚህ ጊዜ አሸናፊነቷን ሲጠብቅ የነበረው አሰልጣኝ ኃይለ ወደ መሮጫው መስመር ዘሎ በመግባት ለተሰንበትን ከወደቀችበት በማንሳት ወደ ውድድሩ የመጨረሻ መስመር እንድትደርስ ቢያደርጋትም አሸናፊነትን ልታገኝ አልቻለችም።
“እኔ አጥሩን ዘልዩ በመግባቴ ውጤቷ እንደሚሰረዝ አውቅ ነበር። ሆኖም ቁልቁለት ላይ ስለነበረች ሌላ አደጋ እንዳይደርስባት በማሰብ ነው ያን ያደረኩት” ብሏል አሰልጣኝ ኃይለ ኢያሱ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ለተሰንበት ግደይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሸናፊ እና ባለ ክብረ ወሰን በመሆኗ በቀጥታ በተጋበዘችበት እና በመጪው ነሐሴ ላይ በሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ውድድር ላይ እንደምትሳተፍ አሰልጣኟ ገልጿል።
ለተሰንበት ግደይ በ10 ሺህ ሜትር፣ በ5 ሺህ ሜትር እና በግማሽ ማራቶች ሦስት የዓለም ክብረ ወሰኖችን የያዘችው አትሌት ስትሆን ባለፈው ዓመት በተካሄደው የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ላይ በ10 ሺህ ሜትር አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል።
አሜሪካ ዩጂን ኦሪገን ላይ በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ፤ ለተሰንበት ያስገኘችውን ጨምሮ በአራት ወርቅ፣ በሦስት ብር እና በሁለት የነሐስ ሜዳሊያ ከአሜሪካ ቀድማ ከዓለም ሁለተኛ ሆና ውድድሩን አጠናቃለች።












