ዚነዲን ዚዳን - በስፖርት ከዘር እና ከሃይማኖት ልቆ የተገኘው የዘመን ክስተት

የዚዳን ስዕል የዓለም ዋንጫን ይዞ

በፈረንሳይዋ ማርሴ ከተማ ‘ኮብል ስቶን’ መንገድ ዳር ኳስ እየለጋ ያደገው ዚዙ አገሩ ፈረንሳይ ከዓለም ዋንጫ ስተሰናበት ገና የ10 ዓመት ነበር።

ሕልሙ ብስክሌት እንዲገዛለት ከተቻለም የቆዳ ኳስ እንዲመረቅለት እንጂ የወርቅ ኳስ ሽልምት (ባሉን ዶር) አልነበረም።

እኛ ዚነዲን ዚዳን እንለዋለን፤ ሲያሻን ደግሞ ዚዙ ብለን እናቆላምጠዋለን። አብሮ አደጎቹ ግን ያዝ ይሉታል።

ዚዳን አደገ። ተመነደገ። አገሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ እንድታነሳም አደረገ። በዘር የተከፋፈለችውን ፈረንሳይ በኳስ አዋሃደ።

ግን ይህ እንዲሆን ዚዙ ብዙ ከፍሏል።

የዚዳን ቤተሰቦች ከአልጄሪያ ተሰደው ፈረንሳይ ከተሙ። ዚዳን ተወለዶ ያደገባት አካባቢ ላ ካስታላን ትባላለች። በወንጀል እና በሥራ አጥነት የታመሰች መንደር።

ፈረንሳይ በፍፁም ቅጣት ምት በጀርመን ተርትታ ከዓለም ዋንጫው በተሰናበተችበት ዓመት ዚዳን የመጀመሪያ ክለቡን አገኘ።

የዘር ልዩነት የሚፈጥረው ውጥረት የፈረንሳይ ፖለቲካ መለያ ነው። ልክ እንደ ማሪ ለ ፔን ያሉ ቀኝ ዘመም አክራሪ ፖለቲከኞች ከስፔን፣ ከሴኔጋል፣ ከጋና፣ ከአርሜኒያ እና ከፖርቹጋል የመጡ ተጫዋቾች እኛን አይወክሉንም ሲሉ በግልብ ይናገሩ የነበሩበት ዘመን ነበር።

ነገር ግን በዚዳን የተመራው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ‘ለ ብሉ’ (ሰማያዊዎቹ) በ1998 (እአአ) የዓለም ዋንጫን ሲያነሱ የፓሪስ መንገዶች በእግር ኳስ ደጋፊዎች ታጨቁ።

ከሰሜን አፍሪካዊቷ አገር የተገኘው እና ከስደተኛ ቤተሰብ የተወለደው ዚዳን፣ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ደጋፊዎች ታጅቦ ዋንጫውን አንግቦ ነገሰ።

“ዚዙ እናመሰግናለን” ይላል ደጋፊዎች የያዙት አርማ። “ዚዳን ፕሬዝዳንታችን” ይላል ሌላኛው የያዘው ወረቀት።

በማርሴይ አቧራማ መንገዶች ኳስ እያሳደደ ያደገው ዚዙ፤ በፍፃሜው ብራዚል ላይ ሁለት ጎሎች አስቆጠረ፤ ፈረንሳይ 3 ብራዚል 0።

“ሕልምህ ቢሆንም፣ የፈለገ ብትመኘው ውስጥህ ይህም አይቻልም ይልሃል። ለዚህ ነው ከዚህ በኋላ ምንም ማድረግ የማልችለው ነገር እንደሌለ የማምነው” ሲል ዚዳን በወቅቱ ተናግሮ ነበር።

የካንቶና ጫማ ጥፊ

በ1994 ብሔራዊ ቡድኑን የተረከቡት ጃኬ ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር በነበረው ግጥሚያ የ22 ዓመቱን የቦርዶ ተጫዋች ከተቀያሪ ወንበር አንስተው አስገቡት።

ፈረንሳይ ይህን ፍልሚያ 2 ለ 2 አጠናቀቀች። ሁለቱንም የፈረንሳይ ጎሎች ያስቆጠረው ዚዳን ነበር።

የማንቸስተር ዩናይትዱ ኤሪክ ካንቶና አንዱን ደጋፊ እንደ ጃኪ ቻን አየር ላይ ተንሳፎ በጫማ ጥፊ ከመታው በኋላ ለዘጠኝ ወራት ከእግር ኳስ እንዲርቅ ታገደ።

ይህ ለአሠልጣኝ ጃኩዌ እና ለዚነዲን ዚዳን ምርጥ አጋጣሚ ሆነ። በ1996 የአውሮፓ ዋንጫ ዚዙ የካንቶናን ቦታ ተክቶ በቋሚነት ይጫወት ጀመር።

ነገር ግን በዚያ የአውሮፓ ዋንጫ ፈረንሳይ አልተሳካላትም። የፈረንሳይ መገናኝ ብዙኃንም አሠልጣኙን ይወርዱበት ጀመር። የጃኩዌ ቡድን ገና ለጋ ነው ሲሉ ወቀሱ።

ቢሆንም ገና በ20ዎቹ ዕድሜው ፀጉሩ እየሸሸው የነበረው ዚዳን ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ዓለምን ጉድ ሊያሰኝ እየተሰናዳ ነበር።

1998 ዚዳን ከቦርዶ ወደ ጁቬንቱስ ተዛወረ። በድንቅ ብቃቱ ብዙዎችን አጀብ ያሰኝ ጀመር። ከጁቬንቱስ ጋር የስኩዴቶውን (ሴሪ አ) ዋንጫ አንስቶ፤ በቻምፒዮንስ ሊጉ ሁለተኛ ወጥቶ ነው ወደ ዓለም ዋንጫ ያቀናው።

“እሱ በእግሩ የሚያደርገውን አንዳንዶች በእጃቸው እንኳ አይችሉትም” ሲል ቲዬሪ ኦንሪ በቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ላይ ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር።

ዚዳን

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰማያዊዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ዚዳን ባደገባት የማርሴይ ከተማ ነው።

ዚዳን ሰፊ 10 ቁጥር ማሊያ ለብሷል። ነጭ ቁምጣ ታጥቋል። ፈረንሳይ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ደቡብ አፍሪካን 3 ለምንም በመርታት አጠናቀቀች።

ሁለተኛው ጨዋታ መጣ። ከሳዑዲ አረቢያ ጋር፤ ፈረንሳይ እንደለመደችው 3 ለ 0 ትመራ ያዘች። ደንገት ከሳዑዲው ፉዐድ አሚን የተገናኘው ዚዳን ጥፋት ፈፀመ።

ሜክሲኳዊው ዳኛ አላመነቱም። ቀይ ካርዳቸውን መዥረጥ አድርገው ለዚዙ አሳዩ። ደጋፊዎች ኡኡታቸውን አሰሙ።

ዚዳን ዘና፣ ፈታ ያለ፣ ኳስን እንደብይ የሚጫወትበት ቢሆንም ስለቤተሰቡ ሲነሳበት ውስጡ ይገነፍላል። ገና ታዳጊ ሳለ አንድ ተጫዋችን በቴስታ ነቅሎ ጥሎታል።

ዚዳን በእግር ኳስ ዘመኑ 14 ጊዜ ቀይ ካርድ ተመልክቷል። የመጨረሻዋን ግን ማንም አይረሳትምለ። በ2006 የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ የጣልያኑን ተከላካይ ማርኮ ማቴራሲን በግንባሩ ያነጠፈበት።

ወደ 1998ቱ ዓለም ዋንጫ እንመለስ። ዚዳን በቀይ ካርድ ሳቢያ ሦስተኛውን የምድብ ጨዋታ ሳይሳተፍ ቀረ። ነገር ግን ፈረንሳይ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋ ስለነበር ብዙም አልተጨነቀም።

በዙር 16 ፈረንሳይ ከፓራጓይ ተደለደለች። ይህ አስጨናቂ ጨዋታ ዚዳን ከዳር ሆኖ ከመመልከት ውጪ አማራጭ አልነበረውም። ዕድሜ ለሎረን ብላን ፈረንሳይ በወርቃማ ጎል ሕግ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈች።

ዚዳን ተመለሰ። በሩብ ፍፃሜው ፈረንሳይ ከጣልያን። ነጭ በነጭ ማሊያ የለበሱት ‘ሌ ብሉዝ’ ወደ ፍፁም ቅጣት አመሩ። የዚዙ ፍፁም ቅጣት ደረሰ። ጂያንሉካን ወደቀኝ አስተኝቶ ኳሷን ወደ ግራ ሰደዳት።

ፈረንሳይ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተሻገረች።

በግማሽ ፍፃሜው ከክሮሺያ የገጠመችው ፈረንሳይ በሊሊያም ቱራም ተመርታ 2 ለ 1 በመርታት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ፍፃሜ በቃች።

ከግጥሚያው በኋላ ፕሬዝዳንት ዣክ ሺራክ የፈረንሳይ ማሊያን ደርበው ወደ መልበሻ ክፍል ዘለቁ። ዚዳንን ጨበጡ፤ የግብ ጠባቂው ባርቴዝን ግንባር ሳሙ።

ዚዳን ብራዚል ላይ በቴስታ ግብ ሲያስቆጥር
የምስሉ መግለጫ, ዚዳን ብራዚል ላይ በቴስታ ግብ ሲያስቆጥር

ፈረንሳይ ከብራዚል

ፈረንሳውያን በደስታ ጦዘዋል። ራሳቸው ባዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ታሪክ ሊሠሩ ተሰናድተዋል። ፓሪስ ቀን ማታ ሳትል ጭፈራ ላይ ናት።

ፈረንሳይ ከብራዚል የእግር ኳስ አድናቂዎች በጉጉት የጠበቁት ጨዋታ።

“በጣም ያስደነቀኝ መንገድ ላይ ያየሁት ሰው ብዛት ነው” ይላል ዚዳን። “ጥቁር፣ ነጭ፣ ክልስ። ባስ ውስጥ ከኋላ ነበር የተቀመጥኩት። ዞር ብዬ ስመለከት ቢያንስ 500 ሞተር ሳይክል ይከተለናል። በጣም አስደናቂ ነበር። አስደናቂ።”

ዚዳን የፈረንሳይ ድንቅ ልጅ ሆኖ ቢመጣም፤ ብራዚልም የራሷ ተዓምረኛ ነበራት። ሮናልዶ ሉዊዝ ናዛሪዮ ደ ሊማ።

ነገር ግን ሮናልዶ አሞታልና አይሰለፍም የሚል ወሬ መሰማት ጀመረ። ቢሆንም በፍፃሜው ከመሰለፍ የከለከለው አልነበረም።

ሮናልዶ በፍፃሜው ጨዋታ የሚታወቅበት ብቃቱን ሊያሳይ አልቻለም። ብራዚልም እንደቀድሞው ሳትሆን ቀረች። በተቃራኒው ዚዳን እሳት ለብሶ፤ እሳት ጎርሶ ነው ወደ ሜዳ የገባው።

ሰማያዊ ማሊያ የለበሰው ዚዳን በቢጫ ለባሹ የብራዚል ተከላካይ ሥፍራ ፈነጨ። ሁለት ድንቅ የጭንቅላት ጎሎችንም አስቆጠረ። ኢማኑዔል ፔቲት ሦስተኛዋን ጎል አከለ።

ፈረንሳይ ጮቤ ረገጠች። ፓሪስ በደስታ ተናጠች። ደጋፊዎች ጮቤ ረገጡ። ሚሊዮኖች ዋንጫዋን ለማየት አደባባይ ወጡ።

ከሁለት ቀናት በኋላ ዚዙ እና የቡድን አጋሮቹ ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ-መንግሥት በክብር ተጠርተው የአገሪቱ የጀግና ሽልማት ተበረከተላቸው።

የወቅቱ የፈንሳይ ቡድን ‘ቀስተ ደመና’ የሚል ቅጥል ተሰጠው። ቡድኑ ከሁሉም ዘር የተውጣጡ ተጫዋቾችን ማካተቱን ተከትሎ የተሰጠው ስያሜ ነው።

የፈረንሳይ የዓለም ዋንጫ ድል ለጊዜውም ቢሆን በአገሪቱ ሰፍኖ የነበረውን የዘር ፖለቲካ አረጋጋው።

ዚዳን ግን ፖለቲካዊ አስተያየት ከመስጠት ተቆጠበ። ወንድሙ ኖርዲን፣ ዚዳን አስተያየት ቢሰጥ ኖሮ ሊጠቀሙበት የሻቱ ብዙ ፖለቲከኞች ነበሩ ሲል ተናግሯል።

ዚዳን ለፈረንሳይ የዓለም ዋንጫ ድል ያበረከተው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም። ስፖርት፣ ከዘር እና ከሃይማኖት ልቆ ተገኘ። ባሉን ዶር ተሸለመ። ከማይክል ጆርዳን ልቆ የዘመኑ ምርጥ አትሌት ተባለ።

በፈረንሳይኛ ለ‘ፌት ዚዳን’ ይሉታል። የዚዳን ተፅዕኖ ማለት ነው። ዚዳን ማኅበራዊ ክስተት ነው። በዘመናት አንዴ ብቅ የሚል። ከሁሉም ልቆ የሰው ልጅን አንድ የሚያደርግ።