በቀደሙት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ የነገሡ 6 ኮከብ ተጫዋቾች

በእግር ኳስ ሜዳው ብዙ አስደናቂ ክስተቶችን ያሳየን ደማቁ የኳታሩ 2022 የዓለም ዋንጫ እሑድ ፍጻሜውን ያገኛል።
ሳዑዲ አረቢያ አርጀንቲናን ያሸነፈችበት፣ ጃፓን የአውሮፓ ኃያል የሆኑትን ጀርመንን እና ስፔንን አሸንፋ የምድብ የበላይ ሆና ያለፈችበት፣ ሞሮኮ ሳትጠበቅ ቤልጅዬምን፣ ስፔንን እና ፖርቹጋልን ረትታ ግማሸ ፍጻሜ ስትቀላቀል ያሳየን የኳታሩ 2022 የዓለም ዋንጫ ነው።
ባለፉት ሳምንታት ለአገራቸው ኩራት፤ ለብሔራዊ ቡድናቸው የጀርባ አጥንት ሆነው የዘለቁት ሊዮኔል ሜሲ እና ኪሊያን ምባፔ ደግሞ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ዋንጫ ለማንሳት ተፋጠዋል።
ሊዮኔሊ ሜሲ በእግር ኳስ ሕይወቱ ያላሳከው ነገር ቢኖር የዓለም ዋንጫውን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ማንሳት ነው። የ35 ዓመቱ የእግር ኳስ ጥበበኛ ለመጨረሻ ጊዜ ተሰልፎ በሚጫወትበት በዚህ የዓለም ዋንጫ፤ ቡድኑ አሸናፊ ከሆነ ምናልባት ይህ የዓለም ዋንጫ ‘የሜሲ የዓለም ዋንጫ’ ተብሎ ይታወስ ይሆናል።
ፈጣኑ፣ የተከላካዮች ራስ ምታት፣ ኪሊያን ምባፔ ፍረንሳይ ክብሯን አስጠብቃ ዋንጫውን እንድታነሳ ያስችላት ይሆን?
ሜሲም ይሁን ምባፔ ድል ይቅናቸው፤ አንድ ሁሉም የሚስማማበት ሃቅ ሁለቱም ተጫዋቾች ቡድናቸው አሁን ለደረሰበት ደረጃ ትልቅ አበርክቶ አላቸው።
የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ወደ መቋጫው በደረሰበት በሁኑ ወቅት ወደኋላ መለስ ብለን ከዚህ ቀደም በዚህ ተወዳጅ የእግር ኳስ መድረክ ደማቅ ኮከብ ሆነው ጀግና ተብለው ያለፉ ቀደምት ስድስት ተጫዋቾችን እናስታውስ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፔሌ፤ ብራዚል - 1958
ብራዚል ለ1958ቱ የዓለም ዋንጫ ወደ ስዊድን ስታቀና ፔሌ ገና የ17 ዓመት ጎረምሳ ነበር።
ብራዚል ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ስትጫወት ወጣቱ ፔሌ በመጀመሪያዎች ሁለት የምድብ ግጥሚያዎች ተሰልፎ የመጫወት ዕድል ሳይሰጠው ቀረ።
በሦስተኛው የምድብ ጨዋታ ብራዚል ከሶቪየት ኅብረት ስትጫወት ዕድል አግኝቶ ወደ ሜዳ ገብቶ አስደናቂ አቋም አሳየ። በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ ብራዚል ዌልስን 1 ለ 0 ስታሸንፍ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ሲያስቆጥር ትኩረትን መሳብ ቻለ።
ከዚያማ ፔሌን የሚያስቆመው አልተገኘም።
በግማሽ ፍጻሜው ፈረንሳይ ላይ ሦስት ጎሎችን አስቆጥሮ ብራዚል 5 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፋ ወደ ፍጻሜው አመራች። ከዚያም በፍጻሜው ስዊድን ላይ ሁለት ግብ አስቆጥሮ አገሩ ብራዚል ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ እንድታነሳ አስቻለ።
ፔሌ በእግር ኳስ ሕይወቱ በሦስት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል። ቺሊ ባሰናዳችው የ1962 ዓለም ዋንጫ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ተሰልፎ በጉዳት ከውድድሩ ውጪ ሆነ።
በ1970 የዓለም ዋንጫ ፔሌ ድንቅ አቋሙ የታየበት ነበር። በዚህ መድረክ የፍጻሜው ጨዋታን ጨምሮ 4 ጊዜ ጎል አስቆጥሮ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማሪዮ ኬምፕስ፤ አርጀንቲና - 1978
አርጀንቲና ሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫን አንስታለች። ለሁለቱም የእግር ኳስ ድል አንድ ተጫዋች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፤ ይህ ተጫዋች ማሪዮ ኬምፕስ ነው።
የቫሌንሺያው አጥቂ አገሩ ወዳዘጋጀችው የ1978 የዓለም ዋንጫ ያመራው በላሊጋ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብርን ይዞ ነበር።
ማሪዮ በመጀሪያው የምድብ ጨዋታ ጎል ማስቆጠር ተሳነው። በሁለተኛው ጨዋታ ግን ፖላንድን የረቱበትን 2 ጎሎች አስቆጠረ። በቀጣይ ደግሞ ፔሩ ላይ ሁለት ጊዜ ኳስን ከመረብ አገናኘ።
አርጀንቲና በማሪዮ ኬምፕሳ ተመርታ ለፍጻሜው ደረሰች። አርጀንቲናዎች ኔዘርላንድስን 3 ለ 1 ሲረቱ ኬምፕሳ ሁለት ጎሎች አስቆጥሯል።
ይህ ድንቅ ተጫዋች አገሩ ዋንጫ እንድታነሳ ከማሳቻሉም በላይ በዓለም ዋንጫው ኮከብ ግቢ አግቢ እና ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጦ ነበር።

ፓውሎ ሮሲ፤ ጣሊያን - 1982
ሮሲ ወደ 1982ቱ የስፔን የዓለም ዋንጫ ሲያቀና ከገና ከሁለት ዓመታት ቅጣት ወደ ሜዳ መመለሱ ነበር።
የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የጨዋታ ውጤትን ሆነ ብሎ በመቀየር ቅሌት (ማች ፊክሲንግ) ለሁለት ዓመታት የተቀጣን ተጫዋች በቡድኑ አካተቱ ተብለው ተብጠልጥለው ነበር።
ፓውሎ ሮሲ ግን ብራዚል ላይ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር አገሩ ጣሊያ ሩብ ፍጻሜን እንድትቀላቀል አስችሏል።
በግማሽ ፍጻሜው ፓውሎ ሮሲ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ጣሊያን ፖላንድን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸነፈች።
በቡድኑ ለምን ተካተተ ተብሎ የነበረው ተጫዋች በፍጻሜው ጨዋታ ጣሊያን ምዕራብ ጀርመንን 3 ለ 1 ስታሸንፍ ጎል ማስቆጠር ችሎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዲዬጎ ማራዶና፤ አርጀንቲና - 1986
አምበሉ ዲዬጎ ማራዶና ሜክሲኮ ያዘጋጀችውን የ1986 የዓለም ዋንጫ አገሩ አርጀንቲና እንድታሸንፍ ትልቅ ሚና ነበረው።
አርጀንቲና ከምድቧ እንድታልፍ ያስቻለችውን ጎል ማስቆጠር ችሏል። ማራዶና ሁሌም በሚታወሳው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ሁለት ጊዜ ኳስን ከመረብ አገናኝቶ እንግሊዝ 2 ለ 1 ተሸንፋ ከውድድሩ እንድትባረር አድርጓል።
ማራዶና እንግሊዝ ላይ ያስቆጠራት የመጀመሪያዋ የጎል “የፈጣሪ እጅ” ተብላ የምትታወቀዋ ነች። ማራዶና ኳሷን በእጁ ገፍቶ ከመረብ ሲያዋህድ ዳኞች አልተመለከቱም ነበር። እንግሊዝ ላይ ያስቆጠራት ሁለተኛ ጎል ግን አሁንም ድረስ የምንጊዜም የዓለም ዋንጫ ምርጧ ጎል ትባላለች።
በሩብ ፍጻሜው ሁለት አስናቂ ጎሎችን ቤልጂየም ላይ ካስቆጠረ በኋላ በፍጻሜው አገሩ አርጀንቲና ምዕራብ ጀርመንን አሸንፋ ዋንጫ እንድታነሳ ምክንያት ሆኗል።
በዚህ ውድድር 5 ጎሎችን በማስቆጠር ድንቅ አቋም ያሳየው ማራዶና፣ የ1986 ዓለም ዋንጫ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተሸላሚ ሆኗል።

ዚነዲን ዚዳን፤ ፈረንሳይ - 1998
ባለ ብዙ ተሰጥኦው ዚነዲን ዚዳን አገሩ ፈረንሳይ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ተጫዋች ሆኖ ነበር።
ዚዳን ተሰልፎ በተጫወተባቸው ውድድሮች ቁልፍ ሚናን ተወጥቷል። ፈረንሳይ በዚህ ውድድር ደቡብ አፍሪካን፣ ሳዑዲ አረቢያን በምድብ ጨዋታዎች እንዲሁም ጣሊያንን በሩብ ፍጻሜው ስታሸንፍ ዚዳን ምርጡ ተጫዋች ነበር።
በፍጻሜ ጨዋታው ዚዳን ብራዚል ላይ ሁለት የጭንቅላት ኳሶችን በማስቆጠር ፈረንሳይ 3 ለ 1 እንድታሸንፍ አስችሏል።
ዚዳን በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ የምርጥ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችሏል።

ሮናልዶ፤ ብራዚል - 2002
ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በጥምረት ያዘጋጁት የ2002 ዓለም ዋንጫ ሲነሳ ሮናልዶ ይታወሳል።
ሮናልዶ በዚህ ውድድር ድንቅ ሆኖ ዘልቋል።
ብራዚል ከፈረንሳይ ለፍጻሜ ስትደርስ ሮናልዶ ደምቆ የሚታይበት መድረክ እንደሚሆን ተገምቶ ነበር። ይሁን እንጂ ከጨዋታ በፊት ባጋጠመው ሕመም የታሰበው ሳይሆን ቀርቷል።
እአአ 1999 ላይ ያጋጠመው ከባድ የጉልበት ጉዳት ከኳሱ ዓለም እስከ ወዲያኛው ያርቀዋል ተብሎ የነበረው ሮናልዶ፤ ከሦስት ዓመታት በኋላ በደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በጥምረት ባስተናገዱት የዓለም ዋንጫ ድንቅ አቋሙን ማሳየት ችሏል።
ሮናልዶ በዚህ ውድድር በ7 ጨዋታዎች 8 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። እስካሁን ድረስም በዓለም ዋንጫ መድረክ 8 ጎሎችን ያስቆጠረ ተጫዋች የለም።













