ፈረንሳይ የሞሮኮን ግስጋሴ በመግታት ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ አለፈች

ምባፔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍሪካና የአረቡ ዓለም ብቸኛ ተስፋ የነበሩት ሞሮኮዎች ትናንት ምሽት ተስፋቸው ተቀጭቷል።

ትልቅ ወኔ፣ ትልቅ ልብና በራስ መተማመን ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት ሞሮኮዎች ገና ጨዋታው በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ የገባባቸው ጎል ወሽመጥ በጣሽ የሚባል ነበር።

ጎሏ የተቆጠረችው በሃርናንዴዝ ነበር።

ሞሮኮዎች ቁልፍ ተከላካይ መሥመር ተጫዋች ናይፍ አጉዋርድ እንደሚሰለፍ አሳውቀው የነበሩ ቢሆንም የደረሰበት ጉዳት ግን ለመጫወት አላበቃውም።

ይህ ለሞሮኮዋያን ትልቅ ሐዘን ነበር።

ሞሮኮዎች ከድንገተኛና ፈጣን የሃርናንዴዝ ጎል አገግመው ወደፊት ተጭነው መጫወት ቢችሉም ወደ ጎል የሚቀይሩት ኳስ ግን አላገኙም።

የፈረንሳዩ ተቀያሪ ራንዳል ኮሎ ሙዋኒ በመጪው እሑድ በሉሳይል ስታዲየም ለሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ኒዯኔል ሜሲን ላያፈናፍነው ይችላል እየተባለ ነው።

ትናንት ምሽት ቡድኑን ለታሪካዊ ድል ያበቃውም እሱ ነው።

ሞሮኮዎች ከእረፍት በፊት ሮማይን ሳይሲን በጉዳት ቢያጡም ሙሉ ስታዲየም ያልተቋረጠ ድጋፍ እያገኙ ወደፊት ጫና ፈጥረው ተጫውተው ነበር።

ከአሁን አሁን ጎል አስቆጥረው አቻ አስቆጠሩ ሲባል ግን እየመከነባቸው ተቸግረው አምሽተዋል።

ለምሳሌ ጃዋድ ኤል ያሚቅ በ43ኛው ደቂቃ በመቀስ ምት ያደረገው ሙከራ የፈረንሳዩን ግብ ጠባቂን የሁጎ ሎሪስን ልብ ማስደንገጥ የቻለች ነበረች። ሆኖም አንግል ገጭታ መክናለች።

ሁለቱም ቡድኖች ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ሲመለሱ በፈረንሳይ 1-0 መሪነት ቢሆንም ሞሮኮ ታሪክ የመሥራት ዕድሏ ፈጽሞ አልተመናመነም ነበር።

ሆኖም ከእረፍት መልስ በ78ኛው ደቂቃ ምባፔ ተቀይሮ ከገባው ኮሎ ሙዋኒ ጋር በፈጠሩት ቅንጅት ከምባፔ የተላለፈለትን ኳስ ሙዋኒ በቀላሉ ወደ ጎልነት ቀይሯታል።

ይህቺ ጎል በስታዲየሙ ከፍተኛ ድጋፍ የነበራቸውን ሞሮኮዎች ተስፋቸውን ያጨለመች ነበረች።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችና በተጨማሪው 6 ደቂቃ ሞሮኮዎች ያለቀላቸው የሚባሉ ኳሶችን አምክነዋል።

የትናንት ምሽቱን ድል የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በስታዲየም ተገኝተው ተከታትለውታል።

ደስታቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹም ታይተዋል።

የፊታችን እሑድ የሜሲና የምባፔ ፍልሚያን ቢሊዮኖች ይመለከቱታል ተብሎ ይጠበቃል።

ፈረንሳይ በፈረንጆቹ 2018 የሞስኮው የዓለም ዋንጫ በፍጻሜ ክሮሺያን የረታችበትን ታሪክ ትደግም ይሆን?

ሜሲ ዋንጫ ለአገሩ በማንሳት የዓመታት ሕልሙን ያሳካ ይሆን?