ዩክሬን፣ የሩሲያ ቅጥረኛ ገዳዮች የሚያዘወትሩት ሆቴል ላይ ጥቃት ሰነዘርኩ አለች

የፎቶው ባለመብት, SERHIY HAIDAI
የዩክሬን ኃይሎች ለሩሲያ መንግሥት ይሠራል የሚባለውን ዋግነር ቅጥረኛ ቡድን ማጥቃታቸውን ገለጹ።
በተለይም ይህ ጥቃት የዚህ ቅጥረኛ ቡድን አባላት ያዘወትሩታል የተባለና በካዲቭካ ከተማ፣ ሉሃንስክ ግዛት የሚገኝ ሆቴል ላይ ያነጣጠረ ነው።
ጥቃቱ መፈጸሙን ያረጋገጡት በስደት ላይ የሚገኙት የክልሉ ገዥ ሰርሂ ሃይዳይ ናቸው።
በስደት ላይ ያሉት የክልሉ ገዥ ሃይዳይ በሆቴሉ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰናል ብለዋል።
ትናንት ድንገተኛ ጥቃት ተፈጸመበት የተባለው ሆቴል የዋግነር ነፍሰ ገዳዮች ቡድን እንደ ዋና ጽሕፈት ቤቱ ይጠቀምበት የነበረ ነው ተብሏል።
ቢቢሲ በዚህ ሆቴል ውስጥ የዋግነር ቅጥረኛ ገዳዮች ስለመኖራቸው በተጨባጭ ከገለልተኛ ቡድን ማረጋገጥ አልቻለም።
ቅዳሜና እሑድ በደቡባዊ ዩክሬን ከባድ ጦርነት ሲካሄድ ነበር ተብሏል።
ሩሲያ ኦዴሳን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች ስትፈጽም ነበር። የዩክሬን ኃይሎች በበኩላቸው ሚሊቶፖል ከተማን ሲያጠቁ ነበር።
ዋግነር የሚባለው የቅጥረኛ ገዳዮች ቡድን ከክሬምሊን ትዕዛዝ እየተቀበሉ ግድያ የሚፈጽሙ አልያም የሚዋጉ ናቸው።
ምዕራባዊያን እንደሚሉት ይህ ቡድን ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጽምና ለንጹሐንም የማይራራ በገንዘብ የሚነዳ ተዋጊ ኃይል ነው።
ዋግነር የቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን የግል ኩባንያ ሲሆን ወንጀለኞችን ከእስር ቤት ጭምር እየመለመለ በጥሩ ገንዘብ ያዋጋል ይላሉ የምዕራብ ተንታኞች።
ይህን ቡድን የመሠረተውና የሚመራው የቭጌኒ ፕሪጎዚን የተባለ ሰው ነው። ግለሰቡ የቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ረዳት ነበር።
ይህ የዋግነር ቅጥረኛ ገዳዮች ቡድን ከዚህ ቀደም በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በማሊ እና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በውጊያዎች ላይ ተሳትፏል።
በትናንቱ ጥቃት ሩሲያ በካዲቭካ ከተማ ከባድ ምት እንደደረሰባት የቀድሞው ገዥ ተናግረዋል። በከተማዋ ከሚገኘው 50 ከመቶ የሚሆነው የሠራዊት አባል በመድኃኒት እጦር ሞት አፋፍ ላይ ይገኛልም ብለዋል።
ባይደን ለዩክሬኑ አቻቸው ዘለንስኪ የአየር መቃወሚያ አቅማቸውን እንደሚያዳብሩላቸው በስልክ ቃል ገብተውላቸዋል፥
ሁለቱ መሪዎች ጦርነቱን ለማቆም ዘሌንስኪ “ፍትሐዊ ሰላም” መኖር አለበት ብለው በያዙት አቋም ላይም ተነጋግረዋል።
ትናንት ድንገተኛ ጥቃት ተፈጸመበት የተባለው ሆቴል የዋግነር ነፍሰ ገዳዮች ቡድን እንደ ዋና ጽሕፈት ቤቱ ይጠቀምበት የነበረ ነው ተብሏል።
ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ የዩክሬን ሠራዊት እንዳለው 10 ድሮኖችን ጥሏል፤ ሌሎች አምስት ድሮኖች በኦዴሳ የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማትን አውድመዋል። በዚህ የተነሳ በአካባቢው ሚሊዮን ተኩል ሕዝብ ያለ መብራት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነው የሚገኘው።
ዘሌንስኪ በኦዴሳ አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል። የኃይል አቅርቦቱን ለመመለስም ቀናት ሊወስድ ይችላል ብለዋል።
ወሳኝ የተባሉት የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች የተደበደቡት በኢራን ድሮኖች እንደሆነም ተነግሯል።
የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ዛሬ ሰኞ የሰባቱን ብልጹግ አገራት (ጂ7) ስብሰባ በበይነ መረብ ያስተናግዳሉ።
በዚህ ስብሰባ ኢራንና ሩሲያ ላይ ምን ዓይነት ማዕቀብ ይጣልባቸው በሚለው ላይ ይመክራሉ።












