በኢትዮጵያ ይጀመራል የተባለው ክሬዲት ካርድ ምንድነው? አገልግሎቱን ለማግኘት ከእርስዎ ምን ይጠበቃል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዋሽ ባንክ በኢትዮጵያ የክሬዲት ካርድ አገልግሎት በመስጠት የመጀመሪያው ባንክ ለመሆን መቃረቡን አሳውቋል።
ባንኩ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው ‘ዴቢት ካርድ’ ከተሰኘው አገልግሎት በተጨማሪ፣ የክሬዲት ካርድ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።
በዚህም ሁለት ዓይነት የክሬዲት ካርድ አገልግሎት እንደሚጀምር በገለጸበት ወቅት አንደኛው ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ የሚመለስ፣ ሌላኛው ደግሞ ተከፋፍሎ የሚመለስ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ባንኮች ከዴቢት ካርድ አገልግሎት በቀር ሌሎች የካርድ አገልግሎቶች ለደንበኞቻቸው አይሰጡም።
ከዚህ ቀደም ዳሸን ባንክ ኢንተርናሽናል ዴቢት ካርድ የተሰኘ የውጭ ምንዛሪ ለሚጠቀሙ ደንበኞች የሚሆን ካርድ ይፋ አድርጎ ነበር።
ይህ የተለያየ ዓይነት የገንዘብ ዝውውር የካርድ አገልግሎት በዓለም ዙሪያ ያሉ ታላላቅ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት ነው።
በርካታ አገር በቀል ባንኮች ያሏት ኢትዮጵያ በቅርቡ የውጭ አገር ባንኮች ወደ ገበያው እንዲገቡ እንደሚፈቅድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማሳወቁ ይታወሳል።
አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ ባንኮች የዴቢት ካርድን ጨምሮ የክሬዲት ካርድ እንዲሁም ሌሎች የካርድ አገልግሎቶች ለደንበኞቻቸው ይሰጣሉ።
ለመሆኑ ክሬዲት ካርድ ምንድነው? እርስዎስ የክሬዲት ካርድ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ? ጥቅም እና ጉዳቱስ?
ክሬዲት ካርድ ምንድነው?
የዩናይትድ ኪንግደም የተመሰከረላቸው የሒሳብ አዋቂዎች ማኅበር አባል ጥላሁን ግርማ ባንኮች በተለምዶ ሁለት ዓይነት የካርድ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ያስረዳሉ።
የማማከር እና ኦዲቲንግ ባለሙያው እንደሚሉት ዴቢት፤ ደንበኛው ባለው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከኤቲኤም ወጪ ማድረግ የሚያስችለው፤ እንዲሁም በክፍያ ማሽን መጠቀም የሚያችለው ካርድ ነው።
“ነገር ግን ክሬዲት ካርድ ማለት ባንኩ ‘ካለህ ተቀማጭ ገንዘብ በላይ ይህን መጠቀም ትችላለህ’ ብሎ የሚፈቅድልህ ጊዜያዊ ብድር ነው።”
ባንኮች ለደንበኞቻቸው ይህን የካርድ አገልግሎት የሚፈቅዱት የቀደመ የሒሳብ አጠቃቀም እንዲሁም የገቢ ምንጭ እና መጠናቸውን ከግምት አስገብተው ነው።
አቅም ላላቸው ደንበኞች ካላቸው ተቀማጭ ገንዘብ በላይ ወጪ ማድረግ እንዲችሉ ሊፈቀድላቸው እንደሚችልም ያስረዳሉ።
ባለሙያው የክሬዲትና ዴቢት ካርድ ልዩነት ሰርፆ እንዲገባን በምሳሌ ያስረዱናል።
ለምሳሌ ይላሉ. . . “ለምሳሌ 20 ሺህ ብር ካለህ፤ ከኤቲኤምም አውጣ፣ ግብይትም ፈጽመበት፣ ካለህ በላይ ማውጣት አትችልም።”
ክሬዲት ካርድ ግን ባንኮች የደንበኛው መልሶ የመክፈል አቅም ከግምት በማስገባት ለአጭር ጊዜ የሚሰጥ ብድር ዓይነት ነው።
በበርካታ የዓለም አገራት የክሬዲት ካርድ ብድር ወለድ የሚከፈልበት ነው። ነገር ግን በአንዳንድ አገራት ደንበኞች በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ካልከፈሉ ነው ወለድ የሚጣልባቸው።
“ለምሳሌ በ15 ቀናት ውስጥ እከፈላለሁ ብለህ ሳትከፍል ቀኑ ካለፈብህ ወለድ ይኖረዋል። የአዋሽ ባንክ ፖሊሲ ምን ሊሆን እንደሚችል የምናየው ነው የሚሆነው።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካርዱን ለማግኘት ምን ያስፈልጋል?
ደንበኞች የክሬዲት ካርድ አገልግሎት ለማግኘት ለባንኩ ይህን ያህል ብድር ይፈቀድልኝ ብለው ማመልከቻ ማስገባት አለባቸው።
ባንኩ ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት የደንበኞችን አቅም እንዲሁም ከባንኩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ተመልክቶ ፈቃድ ይሰጣል።
“የደመወዝ መጠንህ ሊሆን ይችላል፤ ከባንኩ ጋር ያለህ ግንኙነት ሊሆን ይችላል፤ ነጋዴ ከሆንክ የንግድ ሁኔታህ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ባንኩ ኪሳራውን እያወቀ ሊፍቀድ ይችላል።”
ባለሙያው ደጋግመው የባንክ ተጠቃሚዎች የክሬዲት ካርድን ዓላማ በግልፅ ማወቅ እንዳለባቸው ይመክራሉ።
“ክሬዲት ካርድ የሚሰጥህ ለአጭር ጊዜ የብድር ፍላጎትህ ነው። እንጂ ቋሚ ንብረት [መኪና፣ ቤት] እንድትገዛበት አይደለም።”
የክሬዲት ካርድ ዋነኛው ዓላማው ድንገተኛ ለሆነ የገንዘብ ችግር መውጫ ነው። ለዚህ ነው የሚመለስበት የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት ይላሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው።
“አዋሽ ባንክም የተጠቀምከውን ገንዘብ የምትመልሰው በምን ያህል ጊዜ ነው የሚለውን በተመለከተ የራሱን ፖሊሲ ያወጣል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ይህ የሚወሰነው በደንበኛው የገቢ ምንጭ ነው።”
ለምሳሌ እርስዎ ተቀጣሪ ከሆኑ በወሩ መጨረሻ ደመወዝ ሲቀበሉ ለመክፈል ሊስማሙ ይችሉ ይሆናል፤ በንግድ ከተሠማሩ ደግሞ ምናልባት በወር ሁለት ጊዜ ለመክፈል ይፈርማሉ።
አዋሽ ባንክ ይህንን አገልግሎት ለባንኩ ተጠቃሚዎች በሙሉ ለመስጠት ቃል ገብቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የክሬዲት ካርድ ጥቅምና ጉዳቱ
የ44 ዓመቱ እንግሊዛዊ ዳረን የ32 ሺህ ዩሮ ዕዳ ውስጥ ከገባ በኋላ የሚያደርገው ጠፍቶት ነበር።
ዳረን ከባንክ የወሰደውን ክሬዲት ካርድ እየመዠረጠ ለሚያስፈልገው ጉዳይ ጥቅም ላይ ቢያውለውም ዕዳውን በጊዜ መክፈል የሚያስችል አቅም አልነበረውም።
“እንኳን ልቀንስ ይቀርና በዕዳ ላይ ዕዳ ስጨምር ነው የከረምኩት። ከወር ወር ሲያድግ፤ ከዓመት ዓመት እዳዬ ሲያሻቅብ ነው የከረመው። በጣም ጭንቀት ውስጥ ነበርኩ።”
ምንም እንኳ ዳረን አሁን ዕዳውን ከፍሎ ቢገላገልም በርካታ እንግሊዛዊያን አሁንም የክሬዲት ካርድ ዕዳ ውስጥ ናቸው።
ጥላሁን እንደሚሉት ክሬዲት ካርድ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ተጠቃሚውንና ባንኮች ለኪሳራ ሊዳርግ ይችላል። ለዚህ ነው የክሬዲት ካርድ ዋነኛ ዓላማው መሆን ያለበት አንድን ችግር ወዲያው ለመፍታት መሆን አለበት የሚሉት።
“ለምሳሌ ቤተሰብ ቢታመምብህ አሊያም በሚቀጥለው ወር ዕቁብ የሚወጣልህ ቢሆንና አሁን አንድ ዕቃ መግዛት ብትፈልግ ክሬዲት ካርድ መጠቀም ትችላለህ።”
ባለሙያው ክሬዲት ካርድ ማለት “ልክ እንደ ቴሌ ብር ነው” ይላሉ። “ቴሌ ገንዘብ ሳይኖርህ ሲቀር የብድር አገልግሎት ይሰጥሃል። በሚቀጥለው ስትሞላ ከሒሳብህ ላይ ይወስዳል።”
በውጭው ዓለም ‘ክሬዲት ስኮር’ የሚባል ሐሳብ አለ። የክሬዲት ስኮር ማለት አንድ ሰው ብድር ወስዶ የመመለስ ታሪኩ እንዴት ያለ ነው የሚለውን የሚያሳይ ነው።
ብድር ወስደው በጊዜ የሚመልሱ ሰዎች መልካም ‘ክሬዲት ስኮር’ ያላቸው ተብለው ይጠራሉ። የክሬዲት ታሪካቸው ጥሩ የሆኑ ሰዎች በባንኮች ዘንድ ይከበራሉ፤ የሚፈልጉት ጉዳዩ በቶሎ ይሳልጥላቸዋል።
በአብዛኛዎቹ አገራት የክሬዲት ካርድ ወለድ፣ የባንኮች ለደንበኞቻቸው ከሚሰጧቸው ሌሎች ካርዶች ወለድ ከፍ ያለ ነው።
“ብድር ስለሆነ ወልድ አለው። አደጋ ስላለው ነው ወለዱ ከፍ የሚለው። ንብረት አስይዞ የሚወስድ ሰው እና ንብረት ሳያስዝ ብድር የወሰደ ሰው እኩል ስላልሆነ የወለድ መጠኑን ከፍ በማድረግ ነው ስጋቱን የሚያጣጡት።”
ትንሽ ስለክሬዲትና ዴቢት ካርድ ልዩነት
ዴቢት ካርድ ሲጠቀሙ ቀረጥ የሚጥል የግል ማሽን [ኤቲኤም፣ የግብይት ማሽን] ካልሆነ በቀር ተጨማሪ ክፍያ አይከፍሉም። አልፎም ለተጠቀሙበት ክፍያ ካለው ቀድሞ ያሳወቆታል።
ወደ ክዴዲት ካርድ ስንመጣ ግን ከኤቲኤም ማሽን ገንዘብ ሲያወጡ ክፍያ ይከፍላሉ። አንዳንድ ጊዜ ካርዱን የሰጠዎት ባንክ የአገልግሎት ክፍያ ያስከፍላል።
በበይነ መረብ ዕቃና አገልግሎት የሚሸጡ ድርጅቶች ከዴቢት ካርድ ይልቅ ክሬዲት ካርድ ይመርጣሉ። ለዚህ ምክንያቱ ክሬዲት ካርድ ሲሆን ገንዘቡን ከባንክ ቀጥታ ማግኘት ስለሚችሉ ነው።
ባለሙያዎች ክሬዲት ካርድ ተጠቅሞ ከኤቲኤም ገንዘብ ማውጣትን አይመክሩም። ከዚያ ይልቅ በሚገበያዩበት ወቅት ክሬዲት ካርድዎን ይጠቀሙ ይላሉ።
ቪዛ፣ ማስተርካርድ፣ አሜሪካን ኤክስፕረስ እና ዲስከቨር የክሬዲት ካርድ ኔትዎርኮች ናቸው። ባንኮች እኒህን ኔትዎርኮች ተጠቅመው ነው ለደንበኞቻቸው ክሬዲት ካርድ የሚያውጁት።
አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ ባንኮች የክሬዲት ካርድ ለሚጠቀሙ ደንኞቻቸው ማበረታቻ ሽልማት ይሰጣሉ።
ለምሳሌ የአውሮፕላን ቲኬት ለመቁረጥ፣ ለሆቴል ክፍያ፣ ለበይነ-መረብ ግብይት ክሬዲት ካርድ ከሚጠቀሙ ደንበኞቻቸው ማበረታቻ ይሰጣሉ። ማበረታቻው በአየር መንገድ ማይል፣ በተጨማሪ የሆቴል ክፍያ እንዲሁም በስጦታ ካርድ መልክ ሊሰጥ ይችላል።
ባንኮች ለደንበኞቻቸው በየወሩ ‘ስቴትመንት’ [የባንክ ሒሳብ መረጃ] ይልካሉ። ይህ ስቴትመንት ደንኞች ክሬዲት ካርዳቸውን ተጠቅመው ምን ያህል ክፍያ እንደፈፀሙ፣ የወለድ መጠኑን እና ተጨማሪ ክፍያውን የሚያካትት ነው።
አክሎም፤ ክሬዲት ካርዳቸው ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ እንደቀረ፤ መልሰው ሊከፍሉ የሚገባቸው ዝቅተኛ መጠን ስንት እንደሆነ እና እንዴት መክፈል እንደሚችሉ ይካተትበታል።
የሒሳብ አዋቂው ጥላሁን ከአዋሽ ባንክ እርምጃ በኋላ “ሌሎች ባንኮች ተኝጠው አያድሩም” ይላሉ።
“ይህ አገልግኮት እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይጀመር መቆየቱ በጣም የሚገርም ነው። ሌሎችም ባንኮች ለመጀመር ዝግጅት ላይ ናቸው አሊያም ከአዋሽ ባንክ በኋላ መጀመራቸው አይቀርም።”












