የአፍሪካ መሪዎች በዩኤስ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ዋሽንግተን እያመሩ ነው

ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ

የፎቶው ባለመብት, @KagutaMuseveni

የምስሉ መግለጫ, የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጉባኤው ስፍራ ለመጓዝ ከአገራቸው ሲነሱ

ነገ ማክሰኞ አሜሪካ በምታስተናግደው የዩኤስ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የአፍሪካ መሪዎች ወደ ዋሽንግተን እያመሩ ነው።

በፕሬዝዳንት ባይደን መሪነት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት መሪዎች መካከል 49ኙ የተጋበዙ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማትም ይሳተፋሉ።

ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ጉባኤ ነገ ማክሰኞ ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. የሚጀመር ሲሆን፣ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ አህጉርን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ያለመ መሆኑን የጉባኤው አዘጋጆች ገልጸዋል።

በጉባኤው ላይ እንዲገኙ ጥሪ የተደረገላቸው 49 የአፍሪካ አገራት መሪዎች እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዚህ ጉባኤ ለመታደም ያልተጋበዙት ማሊ፣ ጊኒ፣ ሱዳን እና ቡርኪና ፋሶ በተካሄደባቸው መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት ከአፍሪካ ኅብረት በመታገዳቸው ነው።

በተጨማሪም ከአሜሪካ ጋር ጥሩ ግንኙነት የሌላት ኤርትራም በጉባኤው እንድትሳተፍ አልተጋበዘችም።

በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ወደ አሜሪካ እያቀኑ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል በጉባኤው ላይ ማን ተሳታፊ እንደሚሆን ይፋ አልሆነም።

አንዳንዶች ርዕሰ ብሔሯ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በጉባኤው ላይ እንደሚታደሙ ሲናገሩ፣ ሌሎች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተሳታፊ ይሆናሉ እያሉ ነው።

ነገር ግን ከጉባኤው አስተናጋጆችም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱን ወክሎ በዋሽንግተኑ የሦስት ቀን ስብሰባ ላይ እንደሚገኝ እስካሁን ያሳወቁት ነገር የለም።

በዚህ ጉባኤ ላይ ከሚሳተፉት የአፍሪካ አገራት መሪዎች በተጨማሪ የአህጉሪቱ ግሉ ዘርፍ እና የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላትም ይታደማሉ ተብሏል።

ይህ ጉባኤ በአሜሪካ እና በአፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የሁለዮትዮሽ እና የጋራ አህጉራዊ ግንኙነትና ትብብርን ለማጎልበት የታለመ መሆኑ ተነግሯል።

በጉባኤው ላይ የአህጉሪቱ አገራት ከአሜሪካ ጋር ስለሚኖራቸው ሁለንተናዊ ግንኙነት በተጨማሪ አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ላይም ይነጋገራል ተብሏል።

ከታኅሣሥ 04 አስከ 06/2015 ዓ.ም. ድረስ በሚካሄደው የዩኤስ-አፍሪካ ጉባኤ፣ አዲስ የምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነትን ለመመስረት፣ የዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት ጥበቃን ለማጎልበት፣ ሰላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ እንዲሁም የምግብ ዋስትና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን ፕሬዝዳንት ባይደን ቀደም ሲል ተናግረው ነበር።

እንዲህ አይነቱ በአሜሪካ እና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ጉባኤ ሲካሄድ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የመጀመሪያው ከስምንት ዓመት በፊት በፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመን መካሄዱ ይታወሳል።