በመላው ዓለም የሴቶች ብስጭት መጋጋሉን አንድ ጥናት አመለከተ፣ ለምን ይሆን?

ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጋሉፕ የተባለው የአሜሪካ ተቋም በሠራው ጥናት፣ ባለፉት አሥር ዓመታት፣ በመላው ዓለም ያሉ ሴቶች እጅግ ቁጡ እየሆኑ መጥተዋል።

ሴቶች ብስጩ የሆኑት ለምንድን ነው? ብስጭቱ ለምስን እየተባባሰ መጣ?

ታሻ ረኔ ከሁለት ዓመት በፊት ተሰምቷት የማያውቅ ቁጣ አስተናግዳለች።

ጓዳ ሳለች ድንገት ድምጿን ከፍ አድርጋ፣ በጥልቀት ጮኸች።

“ብዙ ጊዜ በቀላሉ እበሳጫለሁ። የዚያን ቀኑ ስሜት ግን የተለየ ነበር” ትላለች።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መላው ዓለምን ያሸበረበት ወቅት ነበር። ለ20 ደቂቃ ገደማ ያበሳጯትን ነገሮች እየመዘገበች ነበር። ከዚያ ድንገት ጮኸች።

ጩኸቷ አንዳች እፎይታ ሰጥቷታል።

ታሻ እንዴት የተሻለ ሕይወት መኖር እንደሚቻል ታሠለጥናለች። አማካሪም ናት።

ጓዳዋ ውስጥ ከጮኸች በኋላ ሴቶችን በዙም እየሰበሰበች ታወያያለች። የሚያበሳጯቸውን ነገሮች ገልጸው እንዲጮኹ ሴቶቹን ታበረታታለች።

ጋሉፕ ላለፉት አሥር ዓመታት በሰበሰበው መረጃ መሠረት የሴቶች ብስጭት እየተጋጋለ መጥቷል።

ጋሉፕ በየዓመቱ በ150 አገራት ከ120,000 በላይ ሰዎችን ያሳተፈ ጥናት ይሠራል።

የጥናቱ ተሳታፊዎች ጥናቱ በተሠራበት ቀን ዋዜማ ምን ዓይነት ስሜቶች እንደተሰሟቸው ይጠየቃሉ።

ቁጣ፣ ብስጭት፣ ጭንቀት እና ስጋት የሚሉ የስሜት አማራጮች ሲቀርቡ፣ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ናቸው መበሳጨታቸውን የሚገልጹት።

ሴቶች ከወንዶች በበለጠ በተሰማቸው ቁጣ መሠረት የኮሎምቢያውያኔ በ17 በመቶ ሲበልጥ፣ የሕንድ እና የፓኪስታናውያኑ በ12 በመቶ ልቆ ተገኝቷል።

የቢቢሲ ተንታኞች በሠሩት ዳሰሳ እአአ ከ2012 ወዲህ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ሐዘን እና ጭንቀት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

የወንዶች ጭንቀትም እየጨመረ ቢመጣም የሴቶችን ያህል ግን አይደለም።

በ2012 ወንዶች እና ሴቶች ላይ የሚስተዋለው ቁጣ እና ጭንቀት ተመሳሳይ ነጥብ ላይ ነበረ። አሁን ግን የሴቶች በስድስት በመቶ በልጧል። መጠኑ በወረርሽኙ ወቅት ጨምሮ ታይቷል።

ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሜሪካዊቷ የሥነ ልቦና አማካሪ ሳራ ሀርመን የሴቶች ቁጣ እየጨመረ መምጣቱ አያስገርማትም።

አምና ሕክምና የምትሰጣቸውን ሴቶች ሜዳ ላይ ሰብስባ እንዲጮሁ አድርጋለች።

“የሁለት ልጆች እናት ነኝ። በወረርሽኙ ወቅት ከቤት እየሠራሁ ነበር። አንዳች ወደ ቁጣ የሚገፋፋ ጭንቀት ይሰማኝ ነበር” ብላለች።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሕክምና የምትሰጣቸውን ሴቶች በድጋሚ ወደ ሜዳ ወስዳቸው እንዲጮሁ ጠየቀቻቸው።

“መጮሃችን መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል” ትላለች።

በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ሴቶች የሚሰማቸውን ቁጣ የሚገልጹበት ቦታ እንዳመቻቸች ሳራ ትናገራለች።

ወረርሽኙ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህም ቁጣን ቀስቅሷል።

ከሁለት ዓመት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በ5,000 ጥንዶች የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፣ የቤት ውስጥ ሥራ ጫና የሚበረታው ሴቶቹ ላይ ነው።

ሴቶቹ ከወንዶቹ የበለጠ ገቢ የሚያገኙ ቢሆንም እንኳን ከመደበኛ ሥራቸው በበለጠ በቤት ሥራቸው እንዲጠመዱ ጫና ይበዛባቸዋል።

የሥነ ልቦና ሐኪሟ ዶ/ር ላኪሽሚ ቪጃያኩመር እንደምትለው፣ ሴቶች የተማሩ፣ ባለሥራ እና ራሳቸውን የቻሉ ቢሆኑም የአባታዊ ሥርዓት የሚያደርስባቸው ጫና ያስቆጣል።

“ቤት ውስጥ ጫና የሚያስከትለው አባታዊ ሥርዓት እና ሴቶች በሥራ ገበታቸው የሚሰማቸው አንጻራዊ ነጻነት አብረው አይሄዱም። ይሄም ያበሳጫል” ትላለች።

በሕንድ ወንዶች ከሥራ ሲወጡ ወደ ሻይ ቤት ሲያመሩ፣ ሴቶች ግን በጥድፊያ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ይስተዋላል። ይህ ያልተመጣጠነ የሥራ ጫና ቁጣ እንደሚቀሰቅስ የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ይናገራሉ።

“ወንዶቹ ይዝናናሉ። ሻይ ይጠጣሉ። ያጨሳሉ። ሴቶች ግን እየተጣደፉ በአውቶብስ ወይም በባቡር ቤት ይገባሉ። የሚጓዙት ምን እንደሚያበስሉ እያሰቡ ነው። ባቡር ውስጥ ሳሉ ሽንኩርት መክተፍ የሚጀምሩም አሉ” ትላለች።

ከዚህ ቀደም ሴቶች ቁጣቸውን ሲገልጹ መስማት የተለመደ አልነበረም። አሁን ግን ያ እየተለመደ መጥቷል።

ባለሙያዋ እንደምትለው፣ ሴቶች ቁጣን ጨምሮ ስሜታቸውን እየገለጹ መጥተዋል።

ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቢቢሲ 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶችን የሚዘክርበት 10ኛ ዙር ላይ ደርሷል። ይህንንም በማስመልከት ሰቫንታ ኮምሬስ በ15 አገራት ያሉ ሴቶች ያለፉትን አሥር ዓመታት አሁን ካለው ጋር እንዲያወዳድሩ እንድትጠይቅ ጋብዟል።

ጥናቱን የሠራችው 15,723 ሴቶችን አሳትፋ ነው።

ሰቫንታ በሠራችው ዳሰሳ ከተሳተፉ ሴቶች ግማሹ ባለፉት አሥር ዓመታት በተሻለ ሁኔታ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ውሳኔ መወሰን ችለዋል።

ከአሜሪካ እና ፓኪስታን ውጭ በሚገኙ ጥናቱ በተሠራባቸው አገራት፣ ሴቶች ከወንድ ጓደኛቸው ጋር ሲሆኑ ፈቃዳቸውን ለመግለጽ እየቀለላቸው መጥቷል።

ሁለት ሦስተኛው ሴቶች እንደሚሉት ማኅበራዊ ሚዲያ በሕይወታቸው ውስጥ አወንታዊ ሚና አለው። በአሜሪካ እና ዩኬ ቁጥሩ 50 በመቶ ነው።

ጥናት ከተሠራባቸው 15 አገራት በ12ቱ ከሚገኙት ሴቶች 40 በመቶው ባለፉት አሥር ዓመታት በሕይወታቸው ለውጥ ያዩት ስሜትን በነጻነት ከመግለጽ ጋር በተያያዘ ነው።

በአሜሪካ ጥናቱ ሲሠራ ከተሳተፉ 46 በመቶዎቹ ባለፉት አሥር ዓመታት ጽንስ ማቋረጥ ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ።

የሥነ ጾታ አቀንቃኝ እና ፀሐፊ ሶርያ ቼማሊ ‘ሬጅ ቢካምስ ኸር’ የተባለ ስለ ሴቶች ቁጣ የሚገልጽ መጽሐፍ አሳትማለች።

የአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ በብዛት ያሉት ሴቶች እንደሆኑና ኮሮናቫይረስ በይበልጥ የጎዳው ይህንን ዘርፍ እንደሆነ ትናገራለች። ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ቀውስ የበለጠ የተጎዱት ሴቶች የሆኑትም ለዚህ ነው።

“እነዚህ ሥራዎች የሚከፍሉት አነስተኛ ቢሆንም ሴቶች ሳይታክታቸው እንዲሠሩ ይጠበቃል። ይሄ ደግሞ የታመቀ ቁጣና ብስጭት ይፈጥራል” ትላለች።

ከአሜሪካ ጋር ሲነጻጸር በብራዚል፣ በኡራጓይ፣ በፔሩ፣ በቆጵሮስ እና በግሪክ ያሉ ሴቶች ከፍተኛ ቁጣን ገልጸዋል።

በቦሊቪያ እና ኤኳዶርም በሴቶች እና በወንዶች መካከል የተለያየ የብስጭት መጠን ተመዝግቧል።

ከ2012 ወዲህ በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ሴቶች ቁጣ ቢገልጹም፣ ከጊዜ ወዲህ እየተባባሰ መጥቷል።

ነገር ግን ሴቶች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው እየተለመደ መምጣቱን ታሻ ረኔ ትናገራለች።

“ሴቶች ቁጡ መሆናቸው ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል። ለውጥ ለማምጣት መቆጣትና መበሳጨት ያስፈልጋል” የምትለው የተባበሩት መንግሥት ድርጅት የሴቶች ጉዳዮች ተቋም ባልደረባ የሆነችው ጂኔት አዚኮና ናት።