በውጭ አገር ሥራ ሽፋን 'አሜሪካውያንን በፍቅር እንዲያጠምዱ' የተገደዱት ኬንያውያን

የቲንደር ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"አንዳንዴ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ገነትን በምድር እናቀርብልዎታለን ቢሉዎት ጥርጣሬ ቢገባዎት መልካም ነው።"

ይህንን መልዕክት ያስተላለፈው ከፍተኛ ገንዘብ ይከፈላችኋል እየተባሉ የሚታለሉ ዜጎቹን ለማስጠንቀቅ በሚል የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።

ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ በከፍተኛ ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም እንሰጣችኋለን የሚሉ ባዶ ተስፋዎችም ተበራክተው በርካቶች መታለላቸውን ተከትሎ ነው መንግሥት ይህንን ያለው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ጥቂት ወራት ከምንያማር እና ላኦስ 60 ዜጎቼን ታድጌያለሁ ብሏል።

ግለሰቦቹ በታይላንድ ለሽያጭ እና ለደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ ያመለከቱት ሥራ ከስፍራው በደረሱበት ወቅት የወሲብ ንግድ፣ የሰውነት አካል ስርቆት እንዲሁም በኢንተርኔት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን ማከናወን ሆኖ አግኝተውታል።

“በምንያማር ቻይናውያን በሚቆጣጠሯቸው ፋብሪካዎች ዶክተር ነን የሚሉ ግለሰቦች ባደረጉት ቀዶ ህክምና አንድ የኬንያዊ ወጣት ሕይወቱ አልፏል” ሲል ሚኒስቴሩ ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።

ተጭበርብረው ወደእነዚህ የእስያ አገራት የሄዱ ሁለት ሴቶችን ስላጋጠማቸው ጉዳይ ጠየቅኳቸው።

ሁለቱም ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሲሆን፣ አንደኛዋ የ31 ዓመት ወጣት እና በሆቴል ማኔጅመንት የዲፕሎማ ምሩቅ ናት። ሁለተኛዋ ደግሞ 35 ዓመቷ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃለች።

ሁለቱም በነሐሴ ወር 800 ዶላር ወርሃዊ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው ቃል ተገብቶላቸው ለሥራ ወደ ታይላንድ እንዳቀኑ ይናገራሉ።

ከመሄዳቸው ከአንድ ወር በፊት ለሥራ ቀጣሪ ወኪሎቻቸው ለጉዟቸው የሚሆን እያንዳንዳቸው ሁለት ሺህ ዶላር ተበድረው ከፍለዋል። እንዲሁም አጭር ሥልጠናም ወስደዋል።

ሆኖም ታይላንድ እንደደረሱ ተቆጣጣሪዎቻቸው ረዘም ወዳለ የመንገድ ጉዞ አስገቧቸው። በመጨረሻም ወንዝ አቋርጠው ወደ ጎረቤት አገር ላኦስ ደረሱ።

ባለ 15 ፎቅ ህንጻ ውስጥም ገቡ። ይህም የሙሉ ጊዜ ሥራቸው እና መኖሪያቸው ሆነ። በወቅቱ በየትኛዋ ከተማ እየኖሩ እንደሆነም አያውቁም ነበር።

በዚህም ስፍራ ቃል የተገባላቸው ደንበኞች አገልግሎት ላይ መሰማራት ሳይሆን በሳይበር ወንጀል ተሳታፊ እንደሆኑ አወቁ።

ይህም ቲንደር፣ ኢንስታግራም እና ፌስቡክ ላይ አጓጊ የሆኑ አካውንቶችን በመፍጠር አሜሪካውያንን ኢላማ ማድረግ ነበር።

“በፍቅር ወጥመድ በማስገባት ስለ ክሪፕቶከረንሲ እንነግራቸዋለን። ከእነሱም መስረቅ እንጀምራለን” ስትል የ31 ዓመቷ ኬንያዊት ትናግራለች።

ሁለቱም ሰፊና አዳራሽ በሚመስል ክፍል ውስጥ በጥሪ ማዕከል ውስጥ ተገድደው ይሰሩ ነበር።

ከእነሱም በተጨማሪ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ነበሩ።

አንዳቸውም ቢሆን የተገባላቸው ደመወዝ አልተሰጣቸውም፣ በምትኩ በኢንተርኔት በቂ ሰዎችን መሳብና ማጥመድ ካልቻሉ ለአስገዳጅ ወሲብ ሥራ እና የሰውነት አካላቸውንም እንሸጣለም ሲሉ ያስፈራሯቸዋል።

“እንደ ሴት ወደ አስገዳጅ የወሲብ ንግድ ሥራ ሊያስገቡን ይችላሉ። ይህ ካልሆነም የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎቻችንን ሸጠው ወጪያቸውን ሊመልሱ ይችላሉ” ስትል ታብራራለች።

“ነጻነታችንን ለማግኘት 1.2 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ (10 ሺህ ዶላር) መክፈል እንዳለብን ነግረውናል። ካለበለዚያ የእኛ ንብረት ሆናችሁ ትቆያላችሁ አሉን” ትላለች።

የማጭበርበሪያ ፋብሪካዎች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ ዕድል ሆኖ ሁለቱም ግለሰቦች ‘አዌርነስ ኤጌይንስት ሂውማን ትራፊኪንግ’ ከተሰኘ በችግር ላይ ያሉ ስደተኞችን ከሚረዳ የኬንያ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር መገናኘት ቻሉ።

በመጨረሻም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የኬንያ ባለሥልጣናት ታድገዋቸው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ታሪካቸው የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የማጭበርበሪያ ፋብሪካዎች” እና “የግዳጅ የጉልበት ሥራ ካምፖች” ብሎ በሚጠራቸው ፓስፖርታቸው ተነጥቆ በወንጀለኞች ቡድን ቁጥጥር ስር ካሉ ኬንያውያን ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ምንም እንኳን ብዙዎቹ የሠራተኛ ቀጣሪ ወኪሎች በፖሊስ የሚፈለጉ ቢሆንም፣ በታይላንድ ውስጥ የሌሉ ሥራዎችን እያስተዋወቁ እንደሆነና ኬንያውያንም የእነዚህ ማጭበርበሮች ሰለባ እንደሆኑ ገልጿል።

ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ከዳኑት መካከል በፋብሪካው ውስጥ በሚንቀሳቀሱ እስከ 20 በሚደርሱ የወንበዴዎች ቡድን አባላት ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባቸው አካል ጉዳተኛ ሆነው የተመለሱ ይገኙበታል።

በቅርቡ የወጣው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ በምያንማር ከሚገኙት የኬንያ ዜጎች መካከል የተወሰኑት በካቺን ግዛት ውስጥ የሚገኙ ይመስላሉ።

ይህች ግዛት ተገንጣይ አማፂያን ከመንግሥት ጋር የሚዋጉበት የጦር ቀጠና ስትሆን፣ ይህም ዜጎቹን በሰላም የማስወጣት ጥረቶችን እያደናቀፈ ነው።

“በቅርቡ በነበረ ወታደራዊ ዘመቻ በአማፂ ቡድኑ ቁጥጥር ስር ባሉ ስፍራዎች ስልሳ ሰዎች ተገድለዋል። እነዚህም ለቻይናውያን ወንበዴዎች ጥበቃ የሚያደርጉ ናቸው” ሲል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስጠንቅቋል።

በታይላንድ በሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ ባለሥልጣናት እርዳታ 10 ኡጋንዳውያን እና አንድ የብሩንዲ ዜጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 76 ሰዎችን ከነሐሴ ወር ጀምሮ ወደ አገራቸው መመለስ ተችሏል።

የበይነ መረብ [ሳይበር] ወንጀሉን ለመፈጸም የተሻሉ ናቸው ተብለው በወንበዴዎቹ ኢላማ የተደረጉት ወጣት እና የተማሩ አፍሪካውያን ናቸው።

ይህ የሚያሳየው በአህጉሪቱ ያለውን አስከፊ የሥራ አጥነት እና የተለያዩ መንግሥታት ለሕዝባቸው የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ቃል ቢገቡም ማሳካት አለመቻላቸውን ነው።

የአፍሪካ ልማት ባንክ በአፍሪካ በየዓመቱ ከ12 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ለሥራ ዝግጁ ቢሆኑም፣ በዓመት በመደበኛነት የሥራ ዕድል የሚፈጠረው ለሦስት ሚሊዮን ብቻ መሆኑን ጠቅሷል።

ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ባደረገው ጥናት 80 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካውያን አህጉሪቷን ለቀው ወደ አውሮፓ የሚያቀኑት ለሥራ ፍለጋ እንደሆነ ይፋ አድርጓል።

አውሮፓ ከደረሱም በኋላ ሥራ በማግኘት ዕድለኛ የሆኑት የቤተሰብ አባላትን ለመደገፍ ገንዘብ ይልካሉ።

ነገር ግን በርካቶቹ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥሏቸዋል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ይፋ የሆነው በመካከለኛው ምሥራቅ አፍሪካውያን ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት የሚገልጹ በርካታ ሪፖርቶችን ተከትሎ ነው።

ሁለቱ ወጣት ሴቶች በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ዕዳ መዘፈቃቸውን ተናግረዋል፤ ከአምስት ወራት በፊት ከነበሩት በከፋ ሁኔታ ውስጥም ይገኛሉ።

የ35 ዓመቷ ግለሰብ በውበት ሳሎን ሥራ ያገኘች ሲሆን፣ ጓደኛዋ ግን ገና ሥራ ፍለጋ ላይ ናት።