መቀለ በመከላከያ ሠራዊት ከመያዟ በፊት የነበሩት ቀናት በነዋሪዎች ዐይን - ሁለት ዓመታትን የኋሊት

የመከላከያ ሰራዊት አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“የደብረ ጽዮን ፎቶ ያለበትን መጽሄት አቃጠልን፣ የትግራይ ሰንደቅ አላማን አቃጠልን።”

“ድሮኖች 'ትራክ' እያደረጉ መኪኖችን እያጠቁ ነው ስለተባልን፤ የግል መኪኖች በተለይም ነጭ ቀለም ያላቸውን በጭቃ፣ በቀለም፣ በአፈር፣ ካርታሜ (የአስፓልት መስሪያ ሬንጅ) ቀብተን ከዕይታ ለመደበቅ ሞከርን።”

እነዚህ ንግግሮች የተሰሙት ከሁለት ዓመት በፊት መቀለ ከነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ነው።

የትግራይ ክልል መዲና መቀለ በፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ከመዋሏ በፊት።

ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት ኅዳር 19/2013 ዓ.ም. የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት መቀለን ተቆጣጠረ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ወጥተው መቀለ በመከላከያ ቁጥጥር ስር መዋሏን በሰበር ዜና ተናገሩ።

የአንዱ ምርቃት ለሌላው እርግማን እንዲሉ።

ጦሩን የደገፉ በአንድ ጎራ ጮቤ ረገጡ፣ እልልታቸውን አቀለጡት፣ ምስጋናቸውን አሰሙ።

በሌላኛው ጽንፍ ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ሰማይ እንደተደፋባቸው በሐዘን ተዋጡ፣ ለቅሶ ድንጋጤ

ተመሳሳይ ሐዘን እና ደስታን የማይጋራ ሕዝብ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ሁነት።

ጫፍና ጫፍ ላይ ያሉ የማይታረቁ ስሜቶች ማኅበራዊ ሚዲያዎቹን አጥለቀለቁ።

ከሁለት ዓመት በኋላ ሁነቶች ተቀያይረዋል።

መቶ ሺዎች እንደ ቅጠል የረገፉበትን ጦርነት ለመቋጨት የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ተስማምተዋል።

መከላከያም በክልሉ ያሉ የፌደራሉ ተቋማትን እንዲቆጣጠር ይሁንታ ተገኝቷል።

ከ24 ወራት በፊት በዚህ ወቅት የመቀለ ነዋሪዎች በአብዛኛው ፈርተው አቅራቢያ ወዳሉ ከተሞች ሸሽተው ነበር።

የመከላከያ ወታደሮች ሃወልቲ አካባቢ በአንቶኖቭ መግባታቸውም ከተሰማ ከቀናት በኋላ ነው የተመለሱት።

መከላከያ መቀለን ከመቆጣጠሩ ከቀናት በፊት ምን ተከሰተ?

በአሁኑ ወቅት ከዕይታ የጠፉት የመከላከያው ኮሎኔል መቀለን በታንክ የመክበብ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ተደርሷል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የእስር ትዕዛዝ ለወጣባቸው የትግራይ አመራሮች የእጅ ስጡ የ72 ሰዓታት ጊዜ ገደብ አስቀመጡ።

ከሁለት ዓመት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት ከዓለም በተሰወረ መልኩና በመረጃ ጨለማ ከመከናወኑ አንጻር በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ምን ነበር ስንል ነዋሪዎችን ጠየቅን።

ኅዳር አጋማሽ አካባባቢ መቀለ በመድፍ ልትታጠር ነው የሚል ዜና የሰሙት እነ ፀደይ አብርሃ (ስሟ የተቀየረ) “ፍርሃት፣ ግራ መጋባት፣ ድንጋጤ” ቤታቸውን ሞላው።

ህወሓት ጋር ሊነካኩ የሚችሉ ብቻ ሳይሆን የትግራይ መለያ የሆኑ አሻራዎችን ለማደብዘዝና ለማጥፋት ሞከሩ።

ባለ ቢጫ ኮከቡን የትግራይ ሰንደቅ አላማ፣ የትግል ታሪክና ሌሎች ሌሎችንም።

ግራ የገባቸው እናቷ ለትግራይ የተቋቋመው የልማት ማኅበር (ቲዲኤ) አባልነት መታወቂያቸውን፣ የምስክር ወረቀቶችንም አቃጠሉ ።

“ሰንደቅ ዓላማው የትግራይ ሕዝብ ነው። ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረ ሕጋዊ ባንዲራ ነው። ህወሓት የራሱ ባንዲራ አለው። ከህወሓት ጋር ብቻ ሳይሆን ከትግራይ ታሪክ ጋር ግንኙነት ያለውን ነገር በሙሉ አቃጠልን” ትላለች።

መቀለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለዚህም ደግሞ የመቀለ ትከበባለች ብቻ ሳይሆን በመከላከያና በኤርትራ ጦር ስር ከነበሩ የትግራይ ከተሞች ነዋሪዎች እየተፈናቀሉ ወደ መቀለ መምጣታቸውም ጋር እንደሚያያዝ ይናገራሉ።

በተለይም የኤርትራ ጦር በተቆጣጠራቸው ሽረና አካባቢዎች ስለደረሰው ግፍ፣ ቤት ለቤት ስለነበረው አሰሳ፣ ስለተፈጸሙ ግድያዎች፣ መደፈሮች እና ዘረፋዎች ተናገሩ።

“ሽረ አካባቢ ቤት ለቤት እንደሚፈትሹ፣ ወጣቶችን እንደሚገድሉ፣ ሴቶችን እንደሚደፍሩ ነገሩን። ስለዚህ በተቻለ መጠን ምንም ነገር እንዳይገኝነው ዝግጅቱ” ትላለች ፀደይ።

የትግራይ አመራሮች ወደ ቆላ ተምቤን ከማምራታቸው በፊት ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በሽረ የደረሰውን አስመልክቶም “ሁላችንም ወጥተን ካልታገልን ሁሉም ሰው ነው ሰለባ የሚሆነው። ሽረ ገብተው የፈጸሙትን ግፍ አይተናል” አሉ።

ይህንንም ተከትሎ እነ ፀደይም የሚችሉትን አቃጠሉ “ያልቻልነውንም ደበቅን” ትላለች።

በየማኅበራዊ ድረ ገጹ የነበሩ መረጃዎችን፣ ትግሉን በመደገፍ የተለጠፉ የፌስቡክ ልጥፎችን መሰረዝ፣ እንዲሁም ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን እንዳጠፉ ለዚህ ዘገባ ያናገርናቸው ነዋሪዎች ነግረውናል።

በወቅቱ ከትግራይ በኩል ሲነገር የነበረው መረጃ ጦርነቱን እያሸነፉ እንደሆነ ስለነበር የሽረ መያዝ በርካቶችን ቢያስደነግጥም መቀለ ትያዛለች የሚል ጭራሽ ስሜት አለመኖሩንም ፀደይ ታስታውሳለች። 

ፀደይ እንደምትለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ72 ሰዓት እጅ ስጡ ጥሪ የመቀለን መያዝ እርግጥ አደረገው።

“መቀለ ይገባሉ የሚል ስሜት አልነበረኝም። አለማመን፣ ፍርሃት፣ ድንጋጤ፤ አመራሩ ራሱ የት እንደነበረ አይታወቅም። ግራ የሚያጋባ ወቅት ነበር” ትላለች ፀደይ።

የመቀለ መያዝ ብቻ ሳይሆን የጦርነቱም ጅማሮም ለፀደይ እንደማይነቁበት መጥፎ ቅዠት ነበር።

ከጓደኞቿ ጋር አመሻሹ ላይ ቢራ እየጠጣች በተኩስ እሩምታ ጦርነቱ ሀ ብሎ መጀመሩን ለተረዳችው ፀደይ ጦርነት እንዲህ ይጀመራል ብላ አላሰበችም ነበር።

ጦርነቱ ከተጀመረባት ዕለት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሁሉ ሰላም ብላ “ቤቢ ሻወር” ለምትወልደው ነፍሰ ጡር ጓደኛዋ ድግስ ደግሳ፣ አዲስ ሕይወት ይህችን ዓለም በሰላም ይቀላቀል ዘንድ በጎ ተመኝተው በአብሮነት አክብረዋል።

“ጦርነት የሆነ ቦታ የሚጀመር ነው የሚመስልሽ፤ ድንገት የሁሉም ሰው ሕይወት የሚቀየር አይመስልም” ትላለች።

ከሰዓታት በኋላም ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ መብራት ተቋረጠ፤ ባንክም ተዘጋ።

“በሚቀጥለው ቀን ራሳችንን ከዓለም ጋር ተቆራርጠን አገኘነው፞” ትላለች ፀደይ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ72 ሰዓታት እጅ ስጡ ጥሪ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእስር ትዕዛዝ ለወጣባቸው የህወሓት አመራሮች እጃቸውን እንዲሰጡ የ72 ሰዓታት ጊዜ ገደብ ሰጡ፤ ኅዳር 13/2013 ዓ.ም. ባስተላለፉት መልዕክት።

ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህወሓትን አባላት ለፍርድ የማቅረብ የመጨረሻና ሦስተኛው ምዕራፍ ላይ ተደርሷል ብለው ነበር።

“የጥፋት ጉዟችሁ ተጠናቋል። የማትመለሱበት ደረጃ ላይ ደርሳችኋል፤ ይህንንን የመጨረሻ ዕድል ተጠቀሙበት።

“ከተጨማሪ እልቂት እና ከተማዎችን ከማውደም እናም በታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ለዘላለም ከመኮነን ራሳችሁን አድኑ” ሲሉም ለትግራይ አመራሮች ጥሪ አቀረቡ።

ለትግራይ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻም በተመሳሳይ መልኩ በ72 ሰዓታት በሰላም ለመንግሥት እጃቸውን እንዲሰጡ ጠየቁ።

ለመቀለ ሕዝብም መልዕክት የተላለፈ ሲሆን የህወሓትን አመራሮች ወደ ፍርድ ለማምጣት ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ቁሙ ተብለው ተጠየቁ።

የትግራይ አመራሮች እጅ አንሰጥም የሚል ምላሽ ሰጡ። ለመሞትም ዝግጁ ነን አሉ።

“ስንት ጊዜ ነው ሦስት ቀን የሚሰጠው። ማንነታችንን አልተረዱም። እኛ ለመርኅ የቆምን ነን። ክልላችንን የማስተዳዳር መብታችንን ለማስጠበቅ ለመሞት ዝግጁ ነን” አሉ ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል።

"መቀለን በታንክ ለመክበብ የሚያስችል ምዕራፍ ላይ ነን"

ለህወሓት አመራሮች 72 ሰዓታት ከመቀመጡ አንድ ቀን በፊት መቀለን በታንክ የመክበብ እና የውጊያው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መደረሱን ኮሌኔል ደጀኔ ፀጋዬ ተናገሩ።

በወቅቱ የጦር ግንባሩ ሚዲያ አስተባባሪ የነበሩት ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ “መቀለ ያለው ሕዝባችን ከከባድ መሳሪያ ጥቃት ራሱን እንዲታደግ ጥሪ የሚተላለፍበት ነው። ራስህን አውጣ፤ ከእነዚህ ጁንታዎች ተላቀቅ ተብሎ መመሪያ የሚተላለፍበት ሰዓት ደርሷል” እንዲሁም “ከዚያ በኋላ ምህረት የለም” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላለፉ።

ይህ ንግግራቸውም በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባለሙያዎች ቡድን መቀለ በከባድ መሳሪያ መደብደቧን አስመልክቶ እንደ ዋቢ ተጠቅሷል።

እስካሁን ድረስ መከላከያ በጥንቃቄ ለይቶ በማጥቃት ላይ የተመረኮዘ ውጊያ ነው ያካሄደው ያሉት ኮሎኔሉ በመቀለ እንዳዚያ ላይሆን ይችላልም ሲሉ ጠቆሙ።

“በጣም አስፈሪ ነበር፤ የራስ አገር መንግሥት ሳይሆን ከሌላ ዓለም የሚመጣ ወራሪ፣ ነብሰ ገዳይ እንደሆነ ነው የሚሰማው፤ ሰባ ሁለት ሰዓት ሲባል ለማን ነው የተሰጠው? እንደ ተባለው ጥቂት አመራሮችን ለመያዝ ነው? መቀለን በታንክና በመድፍ ማጠር ለምን አስፈለገ? የነበረው ፍርሃት ከቃላት በላይ ነበር” ትላለች ፀደይ።

ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ያሉ ክስተቶችን እያንዷን ዝርዝር መረጃ ሰንቆ የያዘው አንዶም ገብረእየሱስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሦስተኛ ጊዜ የ72 ሰዓታት ቀነ ገደብ ባስቀመጡበት ዕለት በከተማዋ በርካታ ጉዳዮች ተከናውነዋል ይላል።

የመጀመሪያው የሚጠቅሰው 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጠው ድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን መቋረጥ ነው።

በርካታ የጦርነት ድሎችን ሲያበስር የነበረው ድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን መቋረጥ በርካቶችን ያስደነገጠ እና ከበድ ያለ ነገር እየተከናወነ መሆኑንም ያመላከተ ነበር።

ሌላኛው ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ክልከላ ተጥሎበት የነበረው የነዳጅ ሽያጭ ገደብ ተነሳ።

ጥንቃቄ እንዲደረግበትና ለ'ሪዘርቭ' የተቀመጠው ነዳጅም ሽያጭ መፈቀድ ለአንዶም የትግራይ አመራሮች ከመቀለ መውጣታቸውን ያመላከተ ነው ይላል።

የወጣ ይፋዊ መረጃ ባይኖርም አንዳንድ የውስጥ አዋቂዎች የትግራይ አመራሮች በዚያች ቀን ወደ ቆላ ተምቤን እንደወጡ ነግረውታል።

የተመድ ሪፖርትም የትግራይ አመራሮችም ሆነ ተዋጊዎች መከላከያ ከመግባቱ በፊት መውጣታቸውን ጠቅሷል።

ሌላኛው ደግሞ ወደ ዋጅራት አካባቢ የጦር ሄሊኮፕተር መትተው መጣላቸውን የትግራይ ኃይሎች ተናገሩ።

ተመታ የተባለውንም የሄሊኮፕተር ቁርቁርጥራጭ በአይሱዚ ጭነው፣ በበርካታ ጭነት መኪኖች የትግራይ ኃይሎች የመቀለን ከተማ ዞሩ።

በርካቶችም ደስታቸውን እየገለጹና እየጨፈሩ ሠራዊቱን በመኪና ተከትለው ከተማዋን መዞር ጀመሩ።

የ72 ሰዓቱ ቀነ ገደብ ሊጠናቀቀው አንድ ቀን ሲቀረው የግል መኪኖች በተለይም ነጭ የሆኑትን በቀለም እንዲሸፍኑ ወይም ጭቃ እንዲቀቡ ተነገራቸው።

ለዚህም ድሮኖች እየተከታተሉ መኪኖችን እየመቱ ነው የሚል ዜና ከአስተዳደሩ ወጥቷል ተብሎ በሰሚ ሰሚ በመነገሩ ነው።

ከተማ ውስጥ የሚዘዋወሩ መኪኖች በጭቃ ተቀቡ።

የአንዶምም ኮሮላ መኪናውን ከጓደኞቹ ጋር ሆነው ካርታሜ ከላይ አፈሰሱበትና አፈር ነሰነሱበት። በዚህም መኪናቸውንም መሸፈን ቻሉ።

በትግራይ ጦርነት ከፍተኛ ሚና አላቸው ስለተባሉት ድሮኖች ነዋሪው ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው የሽረን መያዝ ዶክተር ደብረጽዮን በተዘዋዋሪ በተናገሩበት መግለጫ እንደነበር አንዶም ያስታውሳል።

ዶክተር ደብረጽዮን ድሮኖች (ሰው አልባ አውሮፕላኖች) ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነ አስረዱ።

የ72 ሰዓታት መጠናቀቅ

ከሦስት ቀናት በኋላ ኅዳር 17/2013 ዓ.ም. የተሰጠው የ72 ሰዓታት ጊዜ እንደተጠናቀቀ ታወጀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ተደጋጋሚ ዕድሎችን ሰጥተናቸው ነበር አልተጠቀሙበትም፤ የመጨረሻው ሰላማዊ በር በህወሓት ምክንያት ተዘግቷል” አሉ።

በዚህም የመከላከያ ሠራዊት የመጨረሻውን ምዕራፍ እንዲፈጽም ትዕዛዝ እንደተሰጠው አስታወቁ።

“የመቀለና የአካባቢው ሕዝባችን ትጥቁን ፈትቶ በቤቱ በመቀመጥ እና ከወታደራዊ ዒላማዎች በመራቅ፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን” አሉ።

ጉዳቱንም ለመቀነስ “የጁንታው አባላትን” አሳልፈው በመስጠት የበኩላችሁን አስተዋፅኦም አድርጉ ተባሉ።

በመቀለ የሚገኘው የአሉላ አባ ነጋ ሐውልት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የመቀለ ነዋሪዎች በዚያች ወቅት

መቀለ ለቀናት ያህል ጸጥ ረጭ አለች። የእምነት ተቋማት፣ መስጊዶች እና አብያተ ክርስቲያናት ወና ሆኑ።

የትግራይ እናቶች በችግር እና በመከራ ወቅት መሬት ላይ እየወደቁ ፈጣሪን የሚማጸኑበት፣ ምህረት የሚጠይቁበት “ምህላም ተቋረጠ”።

ከተማዋ በመድፍ እና በከባድ መሳሪያ መደብደብ፣ የአየር ጥቃት ያለማቋረጥ እንደተፈራረቁባት እነ አንዶም ያስታውሳሉ።

በርካቶች ከሕንጻ ስር ባሉ የምድር ቤቶች ውስጥ ተደበቁ።

የመቀለ ነዋሪዎች ያላለቁ ህንጻዎች ስር አርባ፣ ሃምሳ እየሆኑ ይገቡ ጀመር።

“እናቶች ልጆቻቸውን የሚደብቁበት ጠፋቸው” ትላለች ፀደይ።

በወቅቱ መቀለ የነበረው ሃብቶም ኃይላይ (ስሙ የተቀየረ) የህክምና ባለሙያ የመድፉ ጥቃት እረፍት እንዳልነበረው ያስታውሳል።

“በጣም ያስደነግጣል። ፍርሃት ይፈጥራል፤ ያርዳል፤ ከተማዋ ስትንቀጠቀጥ ነበር። የሚቃጠል ነገር እናያለን፤ ሁሉም ሰው ዛሬ ስለማደሩ እርግጠኛ አልነበረም” ብሏል።

ሥራ ያላቋረጠው የህክምና ባለሙያ በአይደር በርካታ ቁስለኞችንና የሞቱ ሰዎች መቀበላቸውን ያወሳል።

ከተማ ውስጥ የሚደበቁት እንዳለ ሆኖ በርካቶች ወደ ገጠር መጉረፍ ጀመሩ።

ፀደይ ከእናቷ እና ከትንሽ ወንድሟ ጋር ከመቀለ ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወዳለችው ደብሪ ለመሄድም ወሰኑ።

መጀመሪያ ሃሳባቸው መቀለን ጥለው ለመውጣት ባይሆንም፣ በዚያች ቀን ግን ከቤታቸው የተወሰነ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመድፍ ሲመታ ነው በድንጋጤ ተነስተው የወጡት።

“ምንም ቢሆን እዚህ ብንቆይ ይሻላል ብለን ከወሰንነው ሰዎች መካከል ነበርን። ትምህርት ቤቱ ሲመታ ግን እኛው ነን ቀጣዮቹ ብለን እግራችን ወዳመራው ለመሄድ ተነሳን” ትላለች።

የተወሰኑ መድኃኒቶች፣ ለቁስል የሚሆኑ ፋሻዎች እንዲሁም አንቲባዮቲክስ ያዙ።

ቤት ውስጥ የነበረቻቸውን 700 ብር እስከ መቼ እንደሚቆዩም ሆነ እንደምታቆያቸውም ባያውቁም እሷን ያዙ።

ከዚያ ውጪ ይዘው መሮጥ የሚችሏቸውን እቃዎች ብቻ ይዘው ቤታቸውን ቆልፈው ወጡ።

ህጻናቶች፣ ነፍሰጡሮች፣ የዕድሜ ባለጸጋዎች፣ ነዋሪው ወደ ተምቤን፣ ገረአልታ፣ ግጀት አቀኑ።

መንገድ ላይም ሰው ስጋጃ፣ ምንጣፍ ይዞ ይነጉዳል።

ደብሪ ያየቻትን ትንሽ የገጠር ሱቅ አሁንም ቢሆን አትረሳትም፤ የገጠር የመስኮት ሱቅ ናት ከመቶ ሰው በላይ ተሰልፎ ነበር።

ሱቋ ለተሰለፈው ሰው የሚሆንም ሸቀጥ አልነበራትም።

ትንሿ የገጠር ከተማ ደረሱ፤ ሁለት ጠባብ ክፍሎች ያሏት የገጠር ቤት ሞልታለች።

በርካቶች መሬት ላይ ተኝተዋል። እነ ፀደይም ወለል ላይ ጥጋቸውን ያዙ።

በቀን አንዴ ነው የሚመገቡት የአካባቢው ነዋሪ ያለውን ይዞ ይመጣል።

አንዱ ጎረቤት እንጀራ፣ ሌላው ያለውን ወጥ።

ምቾት በጭራሽ የማይታሰብ ነው።

“ለስንት ጊዜ ነው በዚያ ሁኔታ ላይ የምንቆየው የሚለውን አለማወቅ አስፈሪ ነበር” ትላለች ፀደይ።

መጀመሪያ ላይ የት ቢሄዱ ሕይወታቸውን ማትረፍ እንደሚችሉ መስማማት ስላልተቻለ በቤተሰቡ ውስጥ በሃሳብ መከፋፈል ነበር።

ዋና ከተማ ላይ መቆየት ይሻላል ቢሉም፣ አጎቷ ግን ሊስማማ ባለመቻሉ የ15 ዓመቱን እና የቤቱን ትንሽ ወንድማቸውን ይዞ ወደ ተምቤን ሄዱ።

የህወሓት አመራሮች በወቅቱ ቆላ ተምቤን ናቸው ይባል ስለነበር ከፍተኛ የድሮን ድብደባ ነበር የጠበቃቸው።

ተምቤን ስለሄዱት ወንድማቸው ምንም መረጃም አለመኖሩም ሌላ ህመም ነበር።

የነ አንዶም ሰፈር ዲያስፖራ የሚሰኝ እና ለአሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ቅርብ ሲሆን ጥቃት የሚያደርሱ አውሮፕላኖችን ድምፅ መስማት የተለመደ ነበር።

በርካታ የአየር ጥቃቶች መድረሳቸውን ተከትሎ ገጠር ሕዝቡ በተበታተነ መልኩ ስለሚኖር የአየር ጥቃት ላይኖር ይችላል የሚል ግምት ነበር።

አንዶምም ከፍተኛ የከባድ መሳሪያ ድብደባ እና የአየር ጥቃት መቀለን ሲያናውጣት ከቤተሰቦቹ ጋር ከመቀለ ለመውጣት ወሰኑ።

“የአውሮፕላን ድብደባውን እየሰሙ ልጆቼ ያለቅሱ ነበር” ይላል።

በየቀኑ ድብደባ የደረሰባቸውን አካባቢዎችን ይሰሙ ነበር፤ 05 ቀበሌ፣ መናኸሪያ፣ ላጪ፣ አጼ ዮሐንስ፣ ቀበሌ 14፣ ተቋሟት፣ ሆቴሎች ሌሎችም. . . ።

ሰዎች መሞታቸውን መጎዳታቸውን የየቀኑ ዜናም ሆነ።

በወቅቱ መቀለ የነበረው የህክምና ባለሙያም ሆነ የተመድ ሪፖርት ከትግራይ በኩል አጸፋዊ የተኩስ ምላሽ አንዳልነበር ይፋ አድርጓል።

ከትግራይ በኩል መግለጫው ቀዝቀዝ ብሎ እንደነበርም አንዶምም ያስታውሳል።

በዚያን ወቅት የከተማውን ጸጥታ የሚያስከብረው የአካባቢው ሕዝብ ተደራጅቶ ነበር። ሠራዊቱ በከተማው ውስጥ አልነበረም።

የማስጎብኘት ሥራ የሚሰራው አንዶም የነበሩትን ሃምሳ የሚሆኑ ድንኳኖቹን ለጎረቤቶቹና ለጓደኞቹ አከፋፈለ።

መጀመሪያ ጉዟቸውን ያደረጉት ከመቀለ ስልሳ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወዳለችው ግጀት ነበር።

መንገድ ላይ ሕዝቡ በእግሩ፣ በሚኒባሶች፣ በእቃ መጫኛ ላይ ሳይቀር አቅራቢያው ወዳሉ ገጠር ከተሞች እየተመመ ነበር።

የሚያውቁት ሰው ባይኖርም ግጀት አንድ ሰው ቤት ደረሱ።

የአካባቢው ሰው ከመቀለ የመጣውን መመለስ የሚባል ነገር የለም።

ሁሉም በቻለው ያስተናግዳል፤ የቻለው በቤቱ፣ ያልቻለ በውጭ።

እነ አንዶም ሰውየው ቤት ሲደርሱ ቤቱ ጢም ብሎ ሞልቷል።

ሆኖም ባለቤቱ አልመለሳቸውም፣ እንዲያውም ግቢ ውስጥ አንዱን ጥግ ያዙ ብሎ መጠለል እንደሚችሉ ነገራቸው።

እዚያም አልቆዩም ወደ መቀለ ተመለሱ።

መቀለ በዚያችን ቀን ጸጥ ረጭ ብላለች፤ የንግድ ተቋማቶች ተዘግተዋል፤ ሁሉም ተፈራርቶ ጸጥ ረጭ ብሏል።

ከዚያም በአስጎብኝነት ሥራው ስለሚያውቀው ጉዟቸውን ወደ ገረዓልታ አደረጉ።

የጎረቤቱ ቤተሰቦች ገረአልታም ስለነበሩም ነው ሚኒባስ ኮንትራት ይዘው ወደዚያ ያቀኑት።

ሁለት ፍራሽ፣ ቅያሪ ልብስ፣ ለልጆቹ የሚሆን ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ኢንዶሚ እና ስኳር ይዘው ቤታቸውን ዘግተው ወጡ።

ገረአልታ አልአሳ የሚባል ስፍራም ደረሱ።

አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለመሰብሰብ ይሯሯጣሉ፤ ሰብላቸው የተቃጠለባቸው አርሶ አደሮች ነበሩ።

አልአሳ ሲደርሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ እየጨፈረ እያለፈ ከነበረ የትግራይ ሠራዊት ጋር ተገናኙ።

የትግራይ ሠራዊት ወደ ተምቤን በሚወሰስደው አልአሳ አካቢ ሰፍሮ ነበር።

በዚያም ከባድ ውጊያ ቀጠለ፤ የፍንዳታ ድምጽ ይሰማሉ።

“ሌሊት ሙሉ እሳት ነው የሚታየው። ትልቅ ተራራ አለ። እሱን አልፎ እሳት ይታያል። በተምቤን በኩል ግን የተቃጠሉ ነገሮች ይታያሉ። ተራራ እየነደደ እንደሆነ ነው የሚታየው። ለሦስት ቀናት ልጆቹም አልተኙም፤ ለአምስት ቀናትም ያህል ዋሻ ውስጥ ነበርን” ይላል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች እና ነዋሪዎች እንስሶቻቸውን ይዘው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ገረአልታ ዋሻ ገቡ።

ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የአየር ጥቃትን ሸሽተው ነዋሪዎች ይደበቁበት የነበረው ዋሻ እንደሆነም የዕድሜ ባለጸጎቹ ነዋሪዎች ይነግሯቸው ነበር።

አካባቢው ገዳማት ያሉበት ስፍራ ሲሆን ውሃ ለማግኘት አስከ ሁለት ሰዓት የሚደርስ መንገድ መጓዝ ያስፈልጋል።

“ንጹህ ውሃ የሚባል የለም፤ ድፍርስ ነው እሱም ከተገኘ ነው” ይላል።

ቂጣ እየጋገሩ፣ ቆሎ እየቆሉ፣ በቆሎ እየተቆላ ያንን ጥዋት ማታ መብላት ሆነ።

ከቀናት ውጊያ በኋላ አልዓሳ ግንባር የነበረው የትግራይ ሠራዊት ለቆ ወጣ።

ጦርነቱም ጋብ አለ። የገጠሩም ሰው ወደየቤቱ ተመለሰ።

“እንደ አጋጣሚ ሆኖ የሄድንበት ወቅት ጥሩ ነበር። ምርት ይዞ ነበር፤ ገበሬዎቹ ናቸው ያቆዩን፤ ይዛን የሄደችው ልጅ ቤተሰቦቿ ቤትም ለቀቁልን” ይላል።

እዚያም ለአንድ ወር ያህል ቆዩ።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተመድ መቀለ ላይ ስለተፈጸመው ምን አለ?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከወራት በፊት ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ መከላከያ ኅዳር 19 ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታልን ጨምሮ 15 የሲቪል ተቋማት ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙን አስታውቋል።

በዚህ ድብደባ ሦስት ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 29 ሰላማዊ ነዋሪዎች መገደላቸውን እንዲሁም ከ100 በላይ ነዋሪዎች መቁሰላቸውን ያስታወቀ ሲሆን፣ ቢቢሲ ያናገረው የህክምና ባለሙያም ይህንኑ አረጋግጧል።

በመቀለ ከተማ ከባድ የመሳሪያ ድብደባ በሚፈጸምበት ወቅት የጦር መሳሪያ ወይንም አቅርቦት ስለመኖሩም ሆነ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ስለማነጣጠሩ ምንም መረጃ አላገኘሁም ብሏል።

የዐይን እማኞችም ሆነ ሌሎች ታማኝ ምንጮች የትግራይ ኃይሎች የጦር መሳሪያቸውን ይዘው ኅዳር 19/2013 ዓ.ም መቀለን ለቀው መውጣታቸውን ይናገራሉ።

ድብደባው በሚፈጸምበት ወቅት ከትግራይ ኃይሎች በኩል የአጸፋ የተኩስ መልስ አልነበረም ማለታቸውን ነዋሪዎችን ዋቢ አድርጎም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ሰፍሯል።

የፌደራል መንግሥቱ በአጠቃላይ ግኝቶቹ አልተስማማም።

የመልስ ጉዞ ቀደ መቀለ

እነ ፀደይም ከሦስት ቀናት በኋላ ነበር ወታደሮች መታየታቸውን እና ገብተዋል ሲባል ወደ መቀለ ለመመለስ የወሰኑት።

መቀለ ላይ የሚጠብቃቸውን ነገር ስላላወቁ መጀመሪያ ወታደሮች በአንቶኖቭ ተጭነው እንደገቡ እና በኋላም ሠራዊቱ እንደገባ ሰምተዋል።

ከደብሪ ተመልሰው ወደቤት አልሄዱም፤ ተኩሱም ስላልቆመ በፍርሃት አክስታቸው ቤት ሄዱ።

የአክስቷ ቤት ባለ ሁለት ፎቅ እና ትልቅ የምድር ቤት ስላለው ደኅንነታችን ይጠበቃል በሚል ነው።

ሲመለሱ መንገዱ ላይ የመቀለ ነዋሪ አይታይም።

ወታደሮች አስርም፣ ሃያም ሆነው በቡድን ይንቀሳቀሳሉ። በመኪናም ተጭነው ያልፋሉ።

“ተወልጄ ያደግኩበት ከተማ አልመስልሽ አለኝ፤ የሙት ከተማ (ጎስት ሲቲ) ነው የመሰለው። የማላውቃት ከተማ ነው የመሰለችኝ። በጣም ፈርቼ ነበር። ቀና ብዬ የወታደሮቹን ዐይን መመልከት አልቻልኩም። አንገቴን ደፋሁ። መንገዱ ጭር ብሏል” ትላለች።

አጎቷ እና ወንድሟም ለሁለት ሳምንት ያህል በረሃ ለበረሃ ከተንከራተቱ በኋላ የከፋ መሆኑ ሲገባቸው በእግራቸው ከተምቤን 103 ኪሎ ሜትር አቆራርጠው መቀለ ገቡ።

እናቷ ልጇ በሕይወት አለ የሚልም እምነት አልነበራትም ሆኖም ተዓምር ሆኖ ደረሱ።

“በጣም ቀንሰውና ተጎሳቁለው ነው የመጡት ለሁለት ሳምንት የሚረባ ምግብ አልበሉም። ሲንከራተቱ ነበር፤ የገዛ ወንድሜን ማወቅ ተሳነኝ” ትላለች ።

መከላከያ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ ሰዓት እላፊ ታወጀ።

ከ12 ሰዓት በኋላ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ላይ እርምጃ ይወሰድበታል ተባለ።

ቀን ቀን ዝምታ የሰፈነበት ነበር “በሕዝቡ እና በወታደሩ መካከል ያለው ውጥረት ከፍተኛ ነበር፤ ጸጥ ያለ ግን ከፍተኛ ጩኸት ያለበት” ትላለች ፀደይ ስትገልጸው።

ለቀናትም ማታ ከተማዋ በተኩስ ትናጥ እንደነበር እና ነዋሪዎች ተገድለው ተገኙ ሲባልም መስማት የተለመደ እንደነበር እነ ፀደይ ያስታውሳሉ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀለን ከተቆጣጠረ እስከ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም. በነበረበት ወቅት መጠነ ሰፊ የመበት ጥሰቶች፣ የዘፈቀደ ግድያዎች፣ መደፈሮች፣ የመንግሥት ቢሮዎች፣ ሆስፒታሎች ተቋማት መዘረፋቸውን የተመድ ሪፖርት ያመለክታል።

አንዶም መቀለ ከተመለሰ በኋላ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲሰራ ቢጠየቅም ፈቃደኛ አልነበረም። በአሁኑ ወቅት ኑሮውን በናይሮቢ አድርጓል።

አንዶም ስለቤተሰቦቹ የሰማው ግንቦት ወር ነበር።

በዚያን ወቅት የኤርትራ ወታደሮች መቶ ብር እያስከፈሉ ሚስድ ኮል ያደርጉላቸው ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን በሕይወት ይኑሩም አይኑሩ አያውቅም።