የኢትዮጵያ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥቅማችን አልተከበረም ያሉ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ እንደተዘጋጁ ሲገልጹ፣ የመምህራን ማኅበር ደግሞ ስለተጠራው አድማ የማውቀው ነገር የለም ብሏል።
የጥሪው አስተባባሪ ነን ያሉ መምህራን ለቢቢሲ እንደገለጹት ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚያገኙ ድረስ ከሰኞ ኅዳር 26/2015 ዓ.ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በሥራ ገበታቸው ላይ እንደማይገኙ የገለጹ ሲሆን፣ ይህንንም ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ግልጽ ድብዳቤ መጻፋቸውን አስታውቀዋል።
ሆኖም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ ይህን የሥራ ማቆም አድማ ስለመኖሩ እሳቸውም ከማኅበራዊ ሚዲያ እንደሰሙና ይህንን ጥሪ የሚያደርጉት አካላትም እነማን እንደሆኑ እንደማይታወቁ ገልጸዋል።
ተጠሪነቱ እሳቸው ለሚመሩት አገር አቀፍ ማኅበር የሆነ የዩኒቨርሲት መምህራን ማኅበር መኖሩን የጠቀሱት ዶ/ር ዮሐንስ በመምህራኑ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አቅርቦ “የተገኘ ምላሽ አለ” ብለዋል።
አድማውን ጠሩ የተባሉት መምህራን ደሞዛቸው እንዲስተካከል እና ሌሎች ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ስማችን አይጠቀስ ያሉት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ መምህራን ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም አሁን ካለው የዋጋ ግሽበት ጋር ሲነጻጸር ኑሮችንን ከባድ አድርጎታል ይላሉ።
የሥራ ማቆም አድማውን ለማድረግ “ከመገደዳችን” በፊት ተደጋጋሚ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበናል ያሉት መመህራኑ ጥያቄዎቻቸው ችላ እንደተባሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር ዮሐንስ ግን “ላያረካቸው ይችላል እኛ ግን [የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጥያቄዎች] እየጠየቅን ነው” ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲ መምህራን አለን ያሉትን ጥያቄ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መገባደጃ ላይ ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እንዲሁም ለኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በጻፉት ደብዳቤ ላይ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ካለገኙ የሥራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው ነበር።
ይህ ከሆነ ከአራት ወራት በኋላ ግን ምንም ለውጥ አልመጣም ብለዋል።
ለመሆኑ የመምህራኑ ጥያቄዎች ምንድ ናቸው?
ደሞዝ እና እድገት
የመምህራኑ ቀዳሚ ጥያቄ በአገሪቱ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር የሚያገኙት ደሞዝ ላይ መንግሥት ማሻሻያ እንዲያደርግ የሚጠይቅ ነው።
የዚህ ጥያቄ መነሻ ደግሞ ሦስት ዓመታት ወደኋላ የሚሄድ ነው።
ሐምሌ 1/2011 ዓ.ም. ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የሥራ ምዘና እና የደረጃ ማስተካከያ [Job Evaluation and Grading/JEG] የዩኒቨርሲቲ መምህራን ያለምንም ማሻሻያ ባሉበት እንዲቆዩ አድርጓል።
ይህ ማለት በሲቪል ሰርቪስ የሚመሩ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች በሙሉ በሥራ የቆዩበት ጊዜ ታሳቢ ተደርጎ ደሞዝ ሲከፈላቸው እና ወደ ጎን የማደግ ዕድል ሲኖራቸው፣ በዩኒቨርሲቲዎች ግን ጀማሪዎችን እና በርካታ ዓመታት የሰሩ መምህራን በደሞዝ እኩል የሚያደያርግ ነው።
ይህ ደግሞ በመምህራኑ ዘንድ ቅሬታን መፍጠሩን መምህራኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቅሬታውን ለመፍታት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራን የሥራ ደረጃ ማሻሻያ (JEG) የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በጋራ አጥንተው ሦስት አማራጮች ያሉት ምክረ ሃሳብ ለትምህርት ሚኒስቴር አቅርበዋል።
ይህም ሲተገበር የመምህራኑ ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ እምነት ተፈጥሮ ነበር።
ሆኖም ትምህርት ሚኒስቴር ከእነዚህ አማራጮች ውጪ የሆነና “ብዙም ለውጥ” የማያመጣ ነው ያሉትን ማሻሻያ መተግበሩን ስማችን አይጠቀስ ያሉት መምህራን የተናገሩት።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካሉት 9 ደረጃዎች መካከል ከረዳት ምርቁ እና ከፕሮፌሰር በስተቀር በሁሉም ላይ ማሻሻያ በማድረግ አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል ሆኗል ይላሉ።
ይህም እሳቸው በሚመሩት ማኅበር የመጣ ውጤት እንደሆነ የሚገልጹት ፕሬዝዳንቱ፣ የተቀሩት ሁለት የሥራ መደቦች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበናል ብለዋል።
“እነሱ የሚሉት ይሄ ‘አላረካንም’ ነው። አዎ፣ ይሄ ላያረካ ይችላል። ግን ይሄ አንድ ነገር ነው። ይሄንን ይዞ ጥያቄ ማቅረቡን መቀጠል ነው ያለው አማራጭ እንላለን እኛ” ብለዋል።
ለሥራ ማቆም አድማው ተዘጋጅተናል የሚሉት መምህራን ደግሞ ቀደም ሲል ከቀረቡት አማራጮች የመጀመሪያው ይተግበር የሚል ነው።
በመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ማስተርስ ዲግሪ ያለው መምህር በአማካኝ የተጣራ 8 ሺህ ብር ደሞዝ ያገኛል።
በምሁራኑ በኩል ከተጠኑት አማራጮች መካከል አንዱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በአገልግሎት ዘመን መጠን ደሞዝ እንዲያገኙ ወይም ወደ ጎን እንዲያደጉ ያደርጋል የሚል ነው።
ዶ/ር ዮሐንስም ወደ ጎን ማደግን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ እየተተገበረ አይደለም ያሉ ሲሆን “እሱ አንድ ክፍተት ነው።...ጥያቄው ግን መንገድ ላይ ነው” ብለዋል።
“የዩኒቨርሲቲ መምህር ድሮ በያዘው ደሞዝ ነው እስካሁን እየኖረ ያለው። አሁን ላይ መኖር እየቻለ አይደለም። . . . ስለዚህ አሁን እኛ እየጠየቅን ያለነው የሚያኖረን ደሞዝ ይሰጠን የሚል ነው” ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያለፈለጉ እና ከአስተባባሪዎቹ አንዱ ይናገራሉ።
ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች
በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ የቤት ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፣ መምህራንም ከዚህ አንጻር ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የመኖሪያ ቤት አበልን የሚመለከት ነው።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚሰራ የማስተርስ ዲግሪ ያለው መምህር የቤት አበል 500 ብር ሲከፈለው ሦስተኛ ዲግሪ ያለው መምህር ደግሞ 800 ብር ያገኛል።
“ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙት ከተሞች አካባቢ ነው። አንድ ደህና የሚባል አንድ ክፍል ቤት በትንሹ 2 ሺህ ብር ነው” የሚለው እና ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ለሥራ ማቆም አድማ ከነሳሱ ጥያቄዎች አንዱ ይህ ነው ብሏል።
የማኅበር ቤት መሥሪያ ቦታ ይሰጠን፣ በዩኒቨርሲትዎች መካከል ነጻ የመምህራን ዝውውር ይኑር እንዲሁም የጤና እና የሕይወት መድህን ያስፈልገናል የሚሉት ጥያቄዎችንም አንስተዋል።
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲ መመህራም ቤተሰቦች ነጻ ህክምና እንዲያገኙ እና ልጆቻቸውን በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ሲማሩ ከወጪ መጋራት (cost sharing) ነጻ ሆነው ሙሉ ወጪያቸው በመንግሥት እንዲሸፈን የሚለውም ከጥያቄዎቻቸው መካከል ነው።
እንደ መምህራኑ ገለጻ የሥራ ማቆም አደማውን ለማድረግ ከመወሰናቸው በፊት ባለፉት ዓመታት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት አድረገዋል።
ጥር 30/2013 ዓ.ም. ጥያቄዎቻቸውን በወቅቱ ለነበረው ለሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለገቢዎች ሚኒስቴር እና ለብልጽግና ፓርት ጽህፈት ቤት አቅርበን ነበር የሚሉት አስተባባሪው ከሁሉም አካላት ወኪሎቻችን መልካም ምላሽ አግኝተው ተመልሰዋል ብለዋል።
ሆኖም የተገቡልን ቃሎች ከመተግበር ስለዘገዩ ግንቦት 22/2014 ዓ.ም. ተወካዮቻቸው በድጋሚ ጥያቄ ለማቅረብ ቀርበው ከሐምሌ 2014 ጀምሮ ምላሽ እንደሚያገኙ ተናግሯቸው ነበር ይላሉ።
ይህ ከመሆኖ ቀድም ብሎ በሰኔ ወር ግን ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራን የሥራ ደረጃ ማሻሻያ (JEG) ይፋ አደረገ።
ይህን “ጥቅማችንን አያስከብርም” ያሉትን አዲስ ማሻሻያ በመቃወም እስከ ባለፈው ወር ድረስ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ ቢያቀርቡም “ጠብ የሚል ነገር” አላደረጉልንም ብለዋል።
በዚህም ሳቢያ ከቀጣዩ ሳምንት መግቢያ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ ተገደናል ያሉት መምህራኑ፣ ጥያቄያችን የማይመለስ ከሆነ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት እቅድም አለን ሲሉ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ፣ በመምህራኑ ይደረጋል የተባለው አድማ በተመለከተ ቢያንስ በእሳቸው ስር ላለው የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር ወይም ለአገር አቀፉ መምህራን ማኅበር ደብዳቤ መላክ አለበት።
ተጠራ የተባለውን የሥራ መቆም አድማን ማኅበራቸው እንደማያውቀውና “እንደዚህ አይነት ሁኔታ ደግሞ ለአሰራርም አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል” ብለዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ምን አለ?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰኞ ዕለት ኅዳር 19/2015 ዓ.ም. የትምህርት ሚኒስቴርን እና በስር ያሉ ተቋማትን የዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርት አድምጦ ጥያቄዎችንም አቅርቧል።
ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ደግሞ የዩኒቨርሥቲ መምህራንን ጉዳይ የሚመለከት ነው። የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ መሥሪያ ቤታቸው ከመምህራን ማኅበር ጋር ተገናኝቶ እንደሚሰራ ገልጸው “የሚነሱ ጥያቄዎች ደግሞ የሕዝብና የአገርን አቅም ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ቅደም ተከተል ወጥቶላቸው እንዲመለስ እናደርጋለን” ብለዋል።
በፌድደራል መንግሥት ስር የሚሰሩ ተቋማት ወጥ አሰራር እንዲኖራቸው የተተገበረው የሥራ ምዘና እና ደረጃ ማስተካከያ (Job Evaluation and Grading/JEG) 22 ደረጃዎች እንዳሉት ጠቅሰው፣ 22ኛውን ወይም ከፍተኛውን ደረጃ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ፕሮፌሰሮች ሰጥቶ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላሉ የምህራን ደረጃዎች ሰጥቷል ብለዋል።
ሆኖም ይህ አሰራር የመምህራንን የሥራ ልምድ ስላላገናዘበ ከረዳት ምርቁ እና ከፕሮፌሰር ወጪ ባሉት ደረጃዎች ላይ ከሲቪል ሰርቪስ ጋር በመነጋገር ማሻሻያ አድርገናል ብለዋል።
ሆኖም ሚኒስትር ዲኤታው ወደጎን ማደግን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።
ዶ/ር ሳሙኤል የዩኒቨርሲቲ መምህራን የቤት አበል ለመጨረሻ ጊዜ ማሻሻያ የተደረገበበት ከ10 ዓመታት በፊት መሆኑን ጠቅሰው ዳግም እንዲሻሻል ጥያቄ መቅረቡን ገልጸው “መንግሥት ጉዳዩን አጢኖ በቅርቡ ምላሽ ይሰጣል የሚል እምነት አለን” ብለዋል።
ሌሎቹ የመምህራን ጥያቄዎች ግን በመካከለኛ፣ በረዥም ጊዜ እና “የአገር የመክፈል አቅም” ሲሻሻል ሊመለሱ የሚገባቸው ናቸው ብለዋል።
በሌላ በኩል የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብሃኑ ነጋ “ዩኒቨርሲቲዎች በሲቪል ሰርቪስ ሕግ እና የደሞዝ ስኬል እስከሰሩ ድረስ የሚመጥነን የሚሉት ዓይነት ገንዘብ ሊያገኙ አይችሉም” ካሉ በኋላ መንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በራሳቸው ሥልጣን የሚመሩ መሆን አለባቸው የሚለው ለዚህ ነው ብለዋል።
ፕሮፌሰሩ ተደርጓል ባሉት የዳሰሳ ጥናት 30 በመቶ የዩኒቨርሲቲ መምህራን “የማያስፈልጉ” መሆናቸውን ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት ደሞዝ ከጨመረ ለመምህራን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ነው ሲሉ የተናገሩት ሚኒስትሩ “ያ ደግሞ የማይቻል ነገር” ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ “ለመምህራኑ የሚከፈለው ደሞዝ በቂ አለመሆኑ ጥያቄ አያስነሳም” ያሉ ሲሆን “አሁን ካለንበት ቀውስ ከወጣን በኋላ መምህራኖቻችንን የተከበሩ እንዲሆኑ በደንብ እንደገና አስበን” እንሰራለን ብለዋል።












