የዘመኑን የጦርነት ገጽታ ቀይረዋል የሚባሉትን የቱርክ ድሮኖች የሚያመርቱት ወንድማማቾች

በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት የሩሲያ ሠራዊትን ግስጋሴ በመግታት በኩል የዩክሬን ኃይሎች የታጠቋቸው ቱርክ ሰራሾቹ ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።
ነገር ግን ኢራን ሰራሽ ድሮኖችን መጠቀም የጀመረችው ሩሲያ ደግሞ አሁን በጦርነቱ ላይ የበላይነትን እየያዘች ነው። ሩሲያ ሻሂድ-136 የሚባሉትን የኢራን ድሮኖችን በጦርነቱ ውስጥ ጥቅም ላይ እያዋለች መሆኑ በስፋት ይነገራል።
ባለንበት ዘመን የሚካሄዱ ጦርነቶችን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ከቀየሩት የጦር መሳሪያዎች መካከል ትንንሾቹ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ዝነኛው ቱርክ ሰራሹ ባይራክታር ቲቢ2 የተባለው ድሮን የጦርነትን ገጽታ በመቀየር በኩል ጉልህ ሚና እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይህ ድሮን ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚያስወጣ ሲሆን መጠኑም አነስ ያለ አውሮፕናን የሚያክል ሆኖ፣ በጨረር የሚመራ በረት ለበስ የሆኑ ነገሮችን የሚያወድም ሚሳኤል ይታጠቃል።
የድሮኑ አምራቾች የሆኑት ቱርካውያኑ ወንድማማቾች ሴልቹክ እና ሃሉክ ባይራክታር የጦርነትን አስቀያሚነት ቢያምኑም እነዚህ ጦር መሳሪያዎች ግን አስፈላጊ የሚሆኑበት ጊዜ እንዳለ ይናገራሉ።
“ጦርነት ሰዎች የሚሞቱበት በጣም መራራ ነገር ነው፤ እነዚህን የታጠቁ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ባናመርት ምኞቴ ነበር። ነገር ግን ከባድ ጥቃት ሲያጋጥም እራስን ለመከላከል እነዚህን ዘመናዊ መሳሪያዎች መታጠቅ ያስፈልጋል” ይላል ይላል ታላቅየው ሃሉክ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቤተሰብ የሚመረተው ድሮን
ከኢስታምቡል ወጣ ብሎ በሚገኘው ስፍራ ላይ ያለውና የቤተሰብ ንብረት የሆነው ድሮኖችን የሚያመርተው ተቋም ከውጪ ሲታይ የዩኒቨርስቲ ጊቢ ወይም አንድ የቴክኖሎጂ ተቋም ነው የሚመስለው።
ባይራክታር ቴክኖሎጂ የቱርክ ትልቁ የመከላከያ ተቋም ባይሆንም፣ ነገር ግን ከእውቅና አንጻር ከቀዳሚዎቹ መካከል የሚጠቀስ ነው።
የሚያመርታቸው ድሮኖች ከሁለት ዓመት በፊት አዘርባጃን የአርሜኒያን ብረት ለበስ ጦር አሸንፋ ከአወዛጋቢው የናጎርኖ ካራብህ ግዛት ሰፊውን ቦታ መልሳ እንድትይዝ አስችሏታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ነበር የባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች ከቱርክ ውጪ እውቅና ማግኘት እና በበርካታ ስፍራዎች መነጋገሪያ የሆኑት።
“ድሮኖቹ አዘርባጃንና በአርሜኒያ ጦርነት፣ ቱርክ በሽብርተኝነት ላይ በምታደርገው ዘመቻ፣ በሶሪያ ውስጥ በተካሄዱ ዘመቻዎች እንዲሁም በሊቢያ ጦርነት ውስጥ ወሳኝ ሚና ነበራቸው” ይላል ሃሉክ።
አምራቹ ድርጅት ከቱርክ ጦር ሠራዊት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያለው ሲሆን፣ በመጀመሪያ ያመረታቸውን ድሮኖቹንም የገዛው የአገሪቱ ጦር ኃይል ነበር።
የቱርክ ሠራዊት በድንበሩ ውስጥ እና ከድንበር ባሻገር የሚንቀሳቀሱትን የኩርድ ታጣቂዎችን ለመምታት ድሮኖቹን ተጠቅሞባቸዋል።
የባይራክታር ቲቢ2 አምራች ተቋም ባለቤት የሆኑት ሁለቱ ወንድማማቾች እንደሚሉት አስካሁን ድሮኖቹን ለ24 አገራት አቅርበዋል።
ይህም ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን አገራቸው በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ እንዲሁም በማዕከላዊ እስያ ውስጥ ዋነኛ የድሮን አቅራቢ እንድትሆን ካላቸው ዓላማ ጋር የተሳሰረ ነው።
ወንድማማቾቹ ድሮቹን ሲያመርቱ የቱርክ መንግሥት ባለሥልጣናት ደግሞ፣ በሰው አልባ አውሮፕላኖቹ አማካይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም የሚለውን ጨምሮ የአጠቃቀም ደንቦችን በማስቀመጥ ወደ ውጪ አገር እንዲላኩ ፈቃድ ይሰጣሉ።
ነገር ግን ምርቶቹ የሚሸጡት ለመንግሥታት ብቻ መሆኑን ሃሉክ ይናገራል። “እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎች ለመንግሥት ተቋማት ብቻ የሚሸጡ ናቸው። ከአገራት ወታደራዊ ተቋማት ውጪ ለማንም አይሸጡም።”

ከመኪና መለዋወጫ እስከ ድሮን ማምረት
በዚህ ወቅት በሚካሄዱ ጦርነቶች ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) መካከል አንዱ የሆነውና በበርካታ የጦር ሜዳዎች ከፍተኛ ተጽእኖን በመፍጠር የሚታወቀው ቱርክ ሰራሹ ባይራክታር ቲቢ2 እንዴት ሥራ ጀመረ?
የቤተሰብ ተቋም የሆነው ድሮን አምራቹ ተቋም የተመሰረተው የወንድማማቾቹ አባት በሆኑት ኦዝዴሚር ባይራክታር አማካይነት በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ሲሆን፣ በቀዳሚነት ያመርት የነበረው ግን የመኪኖች መለዋወጫ ነበር።
ኢንጂነር የነበሩት የድሮን አምራቹ ድርጅት መስራች ኦዝዴሚር ባይራክታር የተቋማቸው ስም ጦርነት ባለባቸው የዓለም አካባቢዎች እየናኘ ባለበት ወቅት ነበር ባለፈው ዓመት ያረፉት።
አባት በወቅቱ የኢስታምቡል ከተማ ከንቲባ ከነበሩት የአሁኑ የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር በመሆን ከእስልምና እምነት ጋር ግንኙነት ባለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ይሳተፉ ነበር።
ሁለቱም የቱርክ መንግሥት የሚታወቅበትን ዓለማዊ የፖለቲካ ሥርዓት ሲቃወሙ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም የእስልምና እምነት ወደ ሕዝባዊው መድረክ እንዲወጣ ፍላጎት ነበራቸው።
በ2016 (እአአ) ሴልቹክ የፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ሴት ልጅ የሆነችውን ሱመዬን ሲያገባ የቤተሰቡ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ ሄዷል።
ቤተሰቡ ባይቀበለውም በርካታ ተቺዎች የድሮን አምራቹ ባይራክታር ስኬት የሚመነጨው ከፕሬዝዳንቱ ጋር ባላቸው የቀረበ ትውውቅ ምክንያት ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቱርክ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ስኬት
ይህ ሰው አልባ አውሮፕላን በአሁኑ ወቅት ከቱርክ ወታደራዊ ምርቶች ሁሉ በዓለም ዙሪያ የሚታወቅና ለአገሪቱ ወታደራዊ ኢንዱስትሪ ስኬት እንደማሳያ የሚቆጠር ሆኗል።
“ባይራክታር ቲቢ2 ለመጀመሪያ ጊዜ ሚሳኤል በተከሶበት ወቅት፣ በመላዋ ቱርክ ባሉ ጋዜጦች ላይ የፊት ገጽ ዋነኛ ዜና ሆኖ ነበር” ይላል የድሮን ግንባታ ፕሮግራሙ ዋነኛ መሪ ነው በመባል የሚታወቀው ሴልቹክ።
“ይህም አገራችን በሌሎች ስር ጥገኛ እንዳትሆን ከማድረግ አንጻር በጣም ጠቃሚ ነገር ነው። በወቅቱ አላገባሁም ነበር፤ ካገባሁ በኋላ ግን አሉታዊ ዜናዎች በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ላይ መውጣት ጀመሩ” ይላል።
ምንም እንኳን ምዕራባውያኑ አገራት የተለያዩ አይነት ድሮኖች ቢያመርቱም ቴክኖሎጂውን ለሌሎች አገራት በማጋራቱ በኩል ቁጥብ ናቸው።
በዚህም ምክንያት ነው ቱርክ ሰራሾቹ ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ መንግሥታትን ትኩረት ያገኙት። ይህም የድሮቹን ተፈላጊነት እና ዝናን ከፍ እንዲል አድርጎታል።
በዚህ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላን ምርት የቱርክን ያህል ባይሆንም ኢራን የረሷን ድሮኖች በማምረት ሩሲያን ጨምሮ ለአንዳንድ አገራት እንደምታቀርብ ይታወቃል።
ኢራን ከምታመርታቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጋር ሲነጻጸሩ፣ ቱርክ ሰራሾቹ ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች “በዓለም ካሉት ሁሉ የላቁ ናቸው” በማለት ሴልቹክ ይከራከራል።
“የሌሎቹን ድሮኖች ቴክኒካዊ ይዞታን ባልመረምርም፣ ነገር ግን በተለያዩ የጦርነት ግንባሮች ውስጥ የባይራክታር ቲቢ2ን ያህል ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የሉም።”
በእርግጥም በበርካታ አገራት ውስጥ በተካሄዱ ጦርነቶች ውስጥ በመሳተፍ እና ውጤታማ በመሆን የሚጠቀሱት እነዚህ ድሮኖች ዝናቸው እየጎላ ነው።
በቅርቡም የኔቶ አባል አገር የሆነችው ፖላንድ ባይራክታር ቲቢ2 ድሮን በመግዛት፣ ከምዕራባውያኑ የጦር ቃልኪዳን አገራት መካከል አንዷ ሆናለች።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ከዩክሬን ጎን የቆመው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት አባል የሆነችው ቱርክ ከሩሲያ ጋር መልካም ግንኙነት አላት።
በዚህም ሳቢያ ምዕራባውያን ተንታኞች ቱርክን ከሁለቱም ጋር በመሆን ቁርጥ ያለ አቋም ባለመያዝ ይተቿታል።
ለዚህም እንደማሳያ በአንድ በኩል ለዩክሬን ወታደራዊ ድሮኖችን እየሸጠች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሏቸውን ማዕቀቦች አትቀበላቸውም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰሚ ያላገኘው የሩሲያ ፍላጎት
የድሮን አምራቹ ድርጅት ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ካለችው ዩክሬን ጋር የቆየ ግንኙነት እንዳለው ይነገራል።
ሃሉክ እንደሚለው ከዩክሬን ጋር እንደ አውሮፓውያኑ 2018 ላይ ስምምነት መፈረሙን እና በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የድሮን አቅርቦት ተጀምሯል።
በወቅቱ ዩክሬን ድሮኖችን ለማግኘት የተለያዩ አገራትን በትጠይቅም፣ ቱርክ ብቻ ነበረች ፈቃደኛ ሆና ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን እንድታገኝ ያደረገችው።
የቱርክ ወዳጅ የሆነችው ሩሲያ በዚህ የድሮን አቅርቦት ደስተኛ እንዳልሆነችና “የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ድሮኖቹ የሩሲያን የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን እያወደሙ ነው በማለት ስማችንን እያጠፉ ነው” ይላል ሃሉክ።
በአንድ ከፍተኛ የፓርቲ ስብሰባ ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን ድሮኖቹ እንዲኖሯቸው እንደሚፈልጉ በመግለጽ ጥያቄ እንዳቀረቡ ይነገራል።
ምንም እንኳን የድሮኖቹ አምራች ተቋም ባለቤቶች ከሆኑት ወንድማማቾች መካከል ታናሽየው እና የተቋሙ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ የሆነው ሴልቹክ ምንም ነገር ለመናገር ፈቃደኛ ባይሆንም ለዩክሬን ድጋፍ እንዳላቸው ይታመናል።
ከሃሉክ ንግግሮች መረዳት እንደሚቻለው ቢያንስ ቢያንስ በዩክሬን ላይ የተፈጸመው ወረራ እስኪያበቃ ድረስ፣ ከድሮን አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከሩሲያ ጋር ትብብር የሚኖር አይመስልም።












