የዘመናዊውን ዓለም የጦርነት ገጽታን የቀየሩት ድሮኖች

የአሜሪካው ኤምኪው-9 ሪፐር ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ኤምኪው-9 ሪፐር ድሮን

በአንድ ወቅት በኃያላን አገራት እጅ ብቻ ነበሩት ሰው አልባ ወታደራዊ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) አሁን በሁሉም አጅ ገብተዋል ማለት ከሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

ድሮኖች ከትናንሽ መንግሥታት አንስቶ አስከ አማጺያን ድረስ የሚጠቀሙባቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች በመሆን የጦርነት ገጽታን ቀይረውታል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከባድ ብረት ለበስ ታንኮች በምድር ውጊያው ላይ ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው ሁሉ፣ ባለንበት ዘመን ድሮኖች በጦር ሜዳዎች ላይ ተጠቃሽ ወሳኝ የጦር መሳሪያዎች ሆነዋል።

ከዓመታት በፊት አሜሪካ በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅና በሌሎችም ስፍራዎች አማጺያንን ለማደን ስትል በመጀመሪያ ጥቅም ላይ ያዋለችው ኤምኪው-1 ፕሬዴተር የተሰኘው ሰው አልባ በራሪ የወቅቱ ዘመናዊ መሳሪያ ሆኖ ነበር።

በመጀመሪያ ላይ ሸማቂዎችን ለማደን በአየር ላይ ቅኝት ለማድረግ የተሰሩት እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ደረጃቸውና ተፈላጊነታቸው ከፍ ያለው 'ሄልፋየር' የተባለው ሚሳኤል ተገጥሞላቸው ጥቃት ለመፈጸም ከተሰማሩ በኋላ ነው።

በማስከተልም ተፈላጊዎችን አድኖ ጥቃት ለመፈጸም ዲዛይን የተደረገው 'ሪፐር' የተባለው ድሮን ወደ ጦር ሜዳ ተሰማራ። ይህ ድሮን ከቀደመው የሚለየው ክብደት ያለው ጦር መሳሪያ በመሸከምና በሚያደርሰው ከፍተኛ ጉዳት ነው።

ጄነራል ቃሲም ሶሌይማኒ በድሮን ጥቃት ከተገደሉ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄነራል ቃሲም ሶሌይማኒ በድሮን ጥቃት ከተገደሉ በኋላ

በዚህም አሜሪካ ልታጠፋቸው የምትፈልጋቸውን ጠላቶቿን በየትኛውም ቦታና ጊዜ ባልተጠበቀ ሁኔታ ኢላማ ለማድረግ አስችሏታል። ከሁለት ዓመት በፊት ባግዳድ ውስጥ የተገደሉት የኢራኑ ጄነራል ቃሲም ሶሊማኒ ላይ ጥቃት የተፈጸመው በዚህ 'ሪፐር' በተባለው ድሮን እንደሆነ ይታመናል።

ለተወሰነ ጊዜ ድሮኖችን በመጠቀም እንዲህ አይነት አድኖ የማጥፋት ጥቃቶች በአብዛኛው ሲፈጸሙ የነበሩት በአሜሪካና በአስራኤል የነበረ ሲሆን በዚህም ወቅቱ የውጊያ ድሮኖችን የመጠቀም የመጀመሪያው ዘመን ሊባል ይቻላል።

ነገር ግን ሁኔታዎች በሚያስደንቅ ፍጥነት ተለውጠው በርካታ ወገኖች ድሮኖችን ለጦርነት በማዋል አዲስ የዘመናዊ ጦር መሳሪያ ዘመን ተጀመረ።

በዚህም ለፀረ ሽብር እና ሽምቅ ተዋጊዎችን ለማደን ይውሉ የነበሩት ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) አገልግሎታቸው ሰፍቶ በመደበኛ ጦርነቶች ላይም መሳተፍ ጀመሩ።

ቴክኖሎጂው እየረቀቀ በሚሄድበት በዚህ ዘመን ድሮኖችም ከዚሁ ጋር በሚራመድ መልኩ እየዘመኑ ጥቅም ላይ ከመዋሉ ላቸው ባሻገር ከሌሎች ጦር መሳሪያዎች ጋር በመቀናጀት ውጤታማነታቸው እያደገ ነው። ወደፊትም ከዚህ በላቀ ሁኔታ እረቀቁ መሄዳቸው አይቀሬ ነው።

Presentational grey line

ኤምኪው-9 ሪፐር ድሮን

ኤምኪው-9 ሪፐር ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  • ከፊት ለፊት ካሜራ፣ በታችኛው የአካሉ ክፍል ላይ ካሜራና የእንቅስቃሴ መለያ
  • በአየር ላይ ሚዛኑን እንዲጠብቅ የሚያስችል ባላ መሳይ ጭራ
  • ኢላማውን በትክክል ለመምታት እንዲችል በጂፒኤስ ወይም በጨረር የሚመሩ ሚሳኤሎችን እና ቦምቦችን ይታጠቃል
  • ርዝመት፡ 10.97 ሜትር
  • ቁመት/ከፍታ፡ 3.66 ሜትር
  • የክንፉ ስፋት፡ 21.12 ሜትር
  • ከፍተኛው ፍጥነት: በሰዓት 463 ኪሎ ሜትር
Presentational grey line

የድሮን ጥቃቶች ውጤታማነት ከታዩባቸው የቅርብ ጊዜ ጦርነቶች መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት በህወሓት አማጺያን ተከፍቶበት ከነበረው ጥቃት አንጻር ባካሄደው ዘመቻ ላይ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ ድሮኖችን ከቱርክና ከኢራን መግዛቱ የተነገረ ሲሆን በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አማካይነትም የቻይናውን ዊንግ ሉንግ 2 የተባለውን ሰው አልባ አውሮፕላን ማግኘቷ ተዘግቧል።

በተመሳሳይ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በደም አፋሳሹ የሊቢያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን ወዳጇን ጄኔራል ኻሊፍ ሃፍታርን ቻይና ሰራሽ የሆኑትን ድሮኖች አስታጥቃለች።

በዚህ ዘመን በተካሄዱ ጦርነቶች ውስጥ ተዋጊ ድሮኖች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ሊቢያና አዘርባጃን ተጠቃሽ ናቸው።

በዓለም አቀፉ ማኅበረሰሰብ ዘንድ ድጋፍ ያለውን ትሪፖሊ የሚገኘውን የሊቢያ መንግሥት ከውድቀት ለማትረፍ ድሮኖች ሚና ነበራቸው።

በተጨማሪም ባለፈው ዓመት በአርሜንያና በአዘርባጃን መካከል በናጎርኖካራባህ ይገባኛል ምክንያት በተካሄደው ጦርነት ቱርክ ለአዘርባጃን ባስታጠቀቻት ድሮን አማካይነት የበላይነትን አግኝታለች።

በድሮኖች አማካይነት የሚፈጸሙ ጥቃቶች ውስብስብ ሕጋዊና የሞራል ጥያቄዎችን ይነሳባቸዋል። ድሮኖች የሚፈጽሙት ጥቃት ውጤታማነት የሚመረኮዘውም በሚቀርብላቸው መረጃ ትክክለኛነት ላይ ነው።

የድሮኖችን አጠቃቀም ለመቆጣጠር የሚያስችል ስምምነት የመደረጉ ሁኔታ በቅርብ የመፈጸም ባይሆንም፤ አሜሪካ ግን እጅ ዘመናዊ የሚባሉትን ወታደራዊ ድሮኖቿን ለቅርብ ወዳጆቸወ ካልሆነ ለሌሎች አሳልፋ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለችም።

ሌሎች የድሮን አምራች አገራት ግን ምርታቸውን ለሌሎች ለማቅረብ እንዲህ አይነት ልዩነትን አያስቀምጡም።

ኢትዮጵያ ውስጥ በድሮን የወደመ ታንክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያ ውስጥ በድሮን የወደመ ታንክ

በአሁኑ ጊዜ ከ100 በላይ የሚሆኑ አገራት እና ቡድኖች ድሮኖች እንዳሏቸው ሲነገር፣ ሌሎቹ ደግሞ የታጠቁ ድሮኖችን የማግኘት ዕድል አላቸው። በኒው አሜሪካን ሴኪዩሪቲ ሴንተር ውስጥ የጥናቶች ዳይሬክተር የሆኑት ፖል ሻሬ እንደሚሉት ድሮኖች በበርካታ ተጠቃሚዎች እጅ የመግባታቸው ሁኔታ የሚቀጥል ይመስላል።

"ቻይና በዓለም አቀፍ ደረጃ ድሮኖችን በመሸጥ በኩል ቀዳሚዋ ናት። በአሁኑ ጊዜ ድሮኖች በዋነኛ ወታደራዊ ኃያል አገራት ብቻ የሚመረቱ አይደሉም። ከዚያ ይልቅ ኢራንና ቱርክን የመሰሉ መካከለኛ አገራት ጭምር ድሮኖችን በማምረት ለሌሎች አገራት እያቀረቡ ይገኛሉ" ብለዋል።

ጨምረውም "ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ የድሮን ቴክኖሎጂዎች በቀላሉ የሚገኙ ሲሆን፣ ማንም ሰው መቶዎችን ዶላሮች በማውጣት እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ተራ የጥቃት ድሮኖችን መስራት ይችላል። የሽብር ቡድኖችም ይህንን ይጠቀማሉ።"

ሰው አልባ አውሮፕላኖች አገራት በርካሽ ወጪ የአየር ኃይል እንዲኖራቸው በማድረግ ከዚህ በፊት ነበረውን ሁኔታ ለውጠውታል። በዚህም መንግሥታትና ቡድኖች በቀላል ወጪ የአየር ውጊ አቅም እንዲኖራቸው አስችለዋል።

"በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቅኝትን ለማድረግ እንዲሁም በትክክል ኢላማን በመምታት በኩል ድሮኖች በምድር ላይ ለሚንቀሳቀስ ወታደራዊ ኃይል ከባድ አደጋ ናቸው" ይላሉ ፖል ሻሬ።

"ሶሪያ ውስጥ የሩሲያ ድሮኖች በቅኝትና መረጃ በመሰብሰብ ተልዕኮ አማካይነት በሚያስተላልፏቸው የተቀነጁ መልዕክቶች የሩሲያ ከባድ መሳሪያዎች ኢላማቸውን በትክክል እንዲመቱም አስችለዋል" ሲሉ የሩሲያ ጉዳዮች ተንታኙ ሳሙኤል ቤንዴት ይናገራሉ።

በአሁኑ ዘመን የጦርነት ሜዳ ላይ ድሮኖች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸው ይታመናል። ታዲያ ስለምን ድሮኖችን ለመቋቋም አስቸጋሪ ሆነ ?

"አብዛኞቹ ድሮኖች ከዚህ ቀደም ከሚታወቁት ተዋጊ አውሮፕላኖች ጋር ሲነጻጸሩ በጣም ያነሱ በመሆናቸው በአየር መቃዋሚ ለመቆጣጠር የተለየ መሳሪያ ያስፈልጋቸዋል" ይላሉ ሻሬ።

አክለውም "ድሮኖች ወደ መሬት ዝቅ ብለው በዝግታ ስለሚበሩ አብዛኞቹ የአየር መቃወሚያ ሥርዓቶች ለእንደዚህ አይነት በራሪ አካላት የተሰሩ ባለመሆናቸው መትቶ ለማጠል አስቸጋሪ ናቸው።"

በአሁኑ ወቅት በርካታ አገራት የድሮን መከላከያ መሳሪያ ለመስራት እየጣሩ በመሆናቸው ውጤታማ ፀረ ድሮን ተወንጫሪዎች በቅርቡ ሊኖሩ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን ከድሮኖች ዋጋ ርካሽነት አንጻር በብዛት ለጥቃት የሚሰማሩ ድሮኖችን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

በዚህም በቁጥር የበዙ ድሮኖች በአንድ ጊዜ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰማርተው ተከታታይ ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አጅግ አዳጋች ይሆናል።