ለኢትዮጵያ ተዋጊ ድሮኖችን የሚያቀርቡት እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
- ፀሐፊ, በፒተር ምዋይ
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ሪያሊቲ ቼክ
ባለፉት ጥቂት ወራት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ሳቢያ በርካቶች ተገድለዋል።
ከእነዚህ የአየር ጥቃቶች መካከል የተወሰኑት በተዋጊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) የተፈጸሙ ናቸው። በዚህ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ወይም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሚሆን ስጋት አለ።
ከዓመት በላይ ከትግራይ አማጽያን ጋር በጦርነት ውስጥ የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ማንኛውንም ዓይነት መሣሪያ ጥቅም ላይ የማዋል መብት እንዳለው ገልጿል።
መንግሥት ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እንዳላደረገም ተናግሯል።
በተፈናቃዮች ካምፕየደረሰው የአየር ጥቃት
ታኅሣሥ 30/2014 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ ደደቢት በሚገኝ የተፈናቃዮች ካምፕ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በመቶዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በጥቃቱ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ምስሎች በእርዳታ ሠራተኞች ለፖለቲኮ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ተሰጥተዋል። እነዚህ ምስሎች የአየር ጥቃቱ ላይ ምርመራ እንዲደረግ መነሻ ሆነዋል።
ይህ ምርመራ፤ ለአየር ጥቃቱ ከዋሉ መሣሪያዎች አንዱ ከቱርክ ሠራሹ ባይራክታር ቲቢ2 ሰው አልባ አውሮፕላን ላይ የተወነጨፈ ሚሳኤል እንደሆነ ይጠቁማል።
መቀመጫውን ኔዘርላንድስ ባደረገው ፓክስ ፒስ ግሩፕ ውስጥ የሚሠሩ መርማሪዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳሉት፤ ወድቀው ከተገኙ ፍንጣሪዎችና ስብርባሪዎች በእነዚህ ድሮኖች ላይ የሚገጠሙ መሆናቸውን አመልቷል።

የቱርክ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑ ይፋ የተደረገው በታኅሣሥ ወር በፓክስ በሚሠሩት መርማሪ ዊም ዝዊጅንበርግ አማካይነት ነው።
ከትግራይ ክልል በስተደቡብ በሚገኝ የመንግሥት አየር ኃይል ውስጥ የቱርክ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንዳሉ የሳተላይት ምስል አሳይቷል።
እነዚህን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለማነጻጸር ቅርጻቸውን፣ ርዝመታቸውንና ክንፋቸውን በሳተላይት ምስል መመልከት ይቻላል።
በደደቢት በደረሰው የአየር ጥቃት እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን በተመለከተ የሚታወቅ ነገር የለም። የኢትዮጵያ መንግሥትም ማረጋገጫ አልሰጠም።
ባለፈው ዓመት ቱርክ እና ኢትዮጵያ የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የስምምነቱ ዝርዝር ግን ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም።
ሮይተርስ ታኅሣሥ ወር ላይ ያወጣው ዘገባ እንደሚጠቁመው፤ ቱርክ ለኢትዮጵያ ሰው አልባ አውሮፕላን መሸጧ እንዳሳሰባት አሜሪካ ገልጻለች።
በኦሮሞ አማጽያን የደረሰው የአየር ጥቃት
ከትግራይ አማጺያን ጋር የጋራ አላማ እንዳለው በመግለጽ ከስምምነት በደረሰው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ላይ በታኅሣሥ ወር ማብቂያ የአየር ጥቃት ተፈጽሟል።
ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም ተፈጸመ ስለተባለው የአየር ጥቃት ብዙም መረጃ አልወጣም። በሰው ላይ ጉዳት ስለመድረሱም አልታወቀም።
በጊዳሚ ስለደረሰው የአየር ጥቃት የሚጠቁሙ የሚሳኤል ስብርባሪዎች ተገኝተዋል። አንድ ምርመራ እንዳመለከተው እነዚህ ስብርባሪዎች የኢራን መሣሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቁመዋል።

ታኅሳስ ላይ የተገኙ የሳተላይት ምስሎች በሐረር ሜዳ አውሮፕላን ማረፊያ ኢራን ሠራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ታይተዋል። የእነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ቅርጻቸው እና ሌሎች ገጽታዎቻቸው የኢራን እንደሆኑ አመልክቷል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ከኢራን ወደ ሐረር ሜዳ እንዲሁም ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያዎች 15 የጭነት በረራዎች መደረጋቸው የአውሮፕላኖች የበረራ መስመሮችን የሚከታተል መርማሪ አመልክቷ። ነገር ግን አውሮፕላኖቹ ምን እንደጫኑ አልታወቀም።
ባለፈው ጥቅምት የአሜሪካ ባለሥልጣኖች ኢራን ወደ ተለያዩ አገሮች ሰው አልባ አውሮፕላኖች መላኳን በይፋ ኮንነዋል። የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተልከውላቸዋል ከተባሉ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
በአላማጣ የደረሰው የአየር ጥቃት
ታኅሳስ መጀመሪያ ላይ በተፈጸሙ ተከታታይ የአየር ጥቃቶች ሳቢያ በደቡባዊ ትግራይ በሚገኝ የገበያ ስፍራ 28 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
የትግራይ አማጺ ቡድን ህወሓትም ለጥቃቱ የመንግሥት ጀቶችና ድሮኖችን ተጠያቂ አድርጓል።
ታኅሳስ መጀመሪያ ላይ በአላማጣ በተፈጸመው የአየር ጥቃት ጥቅም ላይ የዋለ ሚሳኤል ቁርጥራጮችን የትግራይ ቴሌቭዥን ባስተላለፈው ቪድዮ ላይ አሳይቷል።

ይፋ በተደረጉ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ የተሠራ አንድ ምርመራ እንደሚያሳየው፤ በቪድዮው ላይ የታዩት የሚሳኤል ስብርባሪዎች ከቻይና ሠራሹ ብሉ አሮ 7 ሚሳኤለ (Blue Arrow 7 missile) ጋር ይመሳሰላሉ።
ይህ ሚሳኤል ከሰው አልባ አውሮፕላን ላይ የሚወነጨፍ ነው።
ቻይና ሠራሽ ዊንግ ሉንግ (Wing Loong) ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሐረር ሜዳ አየር ኃይል ውስጥ ሳሉ የሳተላይት ምስሎች አሳይተዋል።
እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሐረር ሜደ የታዩት ከአላማጣው ጥቃት አንድ ቀን በፊት ታኅሣሥ 06/2014 ዓ.ም ነበር።
ይፋ የተደረጉ መረጃዎችን ተጠቅመው ምርምር የሠሩ አካላት እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የታዩት ዊንግ ሉንግ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መነሻቸው ቻይና ናት።
እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መጀመሪያ ላይ የደኅንነት ቅኝት ለማድረግ የታለሙ ነበሩ።

የበረራ መከታተያ መተግበሪያዎች መስከረም ወር ላይ ከቻይናዋ ቺንግዱ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ የጭነት በረራዎች መደረጋቸውን ይጠቁማሉ።
ቺንግዱ ከተማ በቻይና መንግሥት የሚተዳደው ሰው አልባ አውሮፕላን አምራች ቺንግዱ ኤርክራፍት ኢንዱስትሪ የሚገኝባት ናት።
ስቶኮልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች የተባለው ተቋም በሰበሰበው መረጃ መሠረት፤ ዊንግ ሉንግ ሰው አልባ አውሮፕላን እና ብሉ አሮ ሚሳኤልን የምታመርተው ቻይና ብቻ ሳትሆን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም ጭምር ናቸው።
ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደግሞ ከዚህ ቀደም መሣሪያ ለኢትዮጵያ ልካለች።
ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወታደራዊ አውሮፕላን ማረፊያዎች ወደ ሐረር ሜዳ አየር ኃይል እና ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ 119 የካርጎ በረራዎች መካሄዳቸውን የበረራ መረጃ ይጠቁማል።
እነዚህ በረራዎች ወደ ኢትዮጵያ የተደረጉት ምን ጭነው እንደሆነ ግን አይታወቅም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ
የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ ስለተጠቀሱት የአየር ጥቃቶች ዝርዝር መረጃ ባይናገሩም "መንግሥት በተለያየ ጊዜ እና ቦታ ድሮኖችን ተጠቅሟል። ቦታዎቹ የት እንደሆኑ ግን አልገልጽም" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ መንግሥት ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እንዳላደረገም ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።
ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለኢትዮጵያ የቀረቡበትን ትክክለኛ ጊዜ አናውቅም።
ለኢትዮጵያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እያቀረቡ ነው ከሚባሉትን አገራት ቢቢሲ አስተያየት ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጡም።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የተጣለ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የተለም። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ሕጎችን ስንመለከትም ስለ ተዋጊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ይህ ነው የሚባል ግልጽ አሠራር አልተቀመጠም።
በዓለም ዙሪያ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰው አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ የማዋሉ ሁኔታ እጨመረ መጥቷል።
በፓክስ ቡድን ውስጥ በሚሠሩት መርማሪ ዊም ዝዊጅንበርግ እንደሚያምኑት ከኢትዮጵያ አንጻር "ዓለም አቀፍ ሕግጋት ተጥሰዋል የሚል በርካታ ክስ በሚሰማበት ሁኔታ ጠንከር ያለ ጥያቄን ያጭራል" ይላሉ።














