የኢትዮጵያና የቱርክ የወታደራዊ ድሮኖች አቅርቦት ስምምነትና የግብፅ ተቃውሞ

ቱርክ ሰራሹ ባይራክታር ቲቢ2 ሰው አልባ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቱርክ ሰራሹ ባይራክታር ቲቢ2 ሰው አልባ አውሮፕላን

ኢትዮጵያ ቱርክ ሰራሹን ባይራክታር ቲቢ2 የተሰኘ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውል ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ከቱርክ ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቧን ሮይተርስ የዜና ወኪል ምንጮቹን ጠቅሶ ዘገበ።

ቱርክ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ድሮኖችን ስለመሸጧ ሮይተርስ ዘግቧል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ዲፕሎማት ሞሮኮ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ያዘዘቻቸው የመጀሪያ ዙር ድሮኖችን መረከቧን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ያዘዘችው ድሮንን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ባይኖርም ቱርክ ሰራሽ ድሮኖች ባለቤት የመሆን እቅድ አላት ብለዋል።

የዚህ ድሮን የሽያጭ ስምምነት የመለዋወጫ አቅርቦት እና የሰው ኃይል ስልጠናን እንደሚጨመር፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከቱርክ ለመግዛት ያሰበቻቸው ድሮኖች ብዛት እና ዋጋቸውን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ምንጮቹ እንዳልገለጹለት ሮይተርስ አመልክቷል።

የድሮን ሽያጭ ውሉን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ሞሮኮ እና ቱርክ በይፋ ያሉት ነገር የለም። በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡም ለሦስቱ መንግሥታት ከሮይተርስ ጥያቄ ቀርቦላቸውም ምላሽ አልሰጡም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቱርክ ይፋዊ የውጭ ሽያጭ አሃዞች እንደሚያሳዩት ቱርክ ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ የምትልካቸው የአቪዬሽን እና የመከላከያ ቁሳቁሶች መጠን ጭማሪ አሳይቷል። ነገር ግን እነዚህ ይፋዊ መረጃዎች የድሮን ሸያጭ ስለመሆናቸው ግን አላመለከቱም።

ከቱርክ ዕቃ ላኪዎች ጉባኤ የተገኘው አሃዝ እንደሚያሳየው ከሆነ ኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ወደ አገር ውስጥ ያስገባቻቸው የመከላከያ እና አቪዬሽን ቁሶች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ203 ሺህ ዶላር ወደ 51 ሚሊዮን ዶላር አድርጓል።

የካይሮ ቁጣ

ኢትዮጵያ ከቱርክ ለጦር አገልግሎት የሚውል ድሮን ለመግዛት ማቀዷ በግብፅ ዘንድ ቁጣን መቀስቀሱን ሮይተርስ ጨምሮ ዘግቧል።

ሁለት ግብፃውያን የደኅንነት ምንጮች ነገሩኝ ብሎ ሮይተርስ እንደዘገበው፤ ኢትዮጵያ እና ቱርክ ሊደርሱ የሚችሉት አንዳች ስምምነት እንዳይፈጸም አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ጣልቃ እንዲገቡ ካይሮ ጠይቃለች።

ሦስተኛ ግብጻዊው የሮይተርስ ምንጭ እንደሚሉት ከሆነ ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር የትኛውንም አይነት ስምምነት ከመድረሷ በፊት ካይሮ እና አንካራ በጉዳዩ ላይ መምከር አለባቸው የሚል አቋም ይዛለች።

ግብፅ አባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ውጥረት ውስጥ የገባች ሲሆን፤ በሊቢያ እና በምሥራቅ ሜድትራኒያን ባህር ጉዳዮች ደግሞ ከቱርክ ጋር ያላት ግንኙነት የሻከረ ሆኗል።

ፕሬዝደንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ድንገት ሕዝባዊ አመጾችን ተከትሎ የግብፅ ፕሬዝደንት ከሆኑ በኋላ በግብጽ እና በቱርክ መካከል ያለው ወዳጅነት ላልቷል።

ግብፅ እና ቱርክን በተለያዩ ጎራ ጽንፍ ከሳያዙባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሊቢያ ጉዳይ ነው። ቱርክ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠውን የሊቢያን መንግሥት ትደግፋለች።

ግብፅ በበኩሏ በተመድ እውቅና የተሰጠውን መንግሥት ለመገልበጥ ብረት ያነሱትን የጦር አበጋዝ ጀነራል ከሊፍ ኻፍጣርን ትደግፋለች።

የቱርክ ፓርላማ በተመድ እውቅና የተሰጠውን መንግሥት ለመደገፍ ወታደር ወደ ሊቢያ መላኳ በካይሮ እና አንካራ መካከል ያለውን ግንኙነት ውጥረት እንዲያይል አድርጎታል።

ቱርክ ሰራሹ ባይራክታር ቲቢ2

የፎቶው ባለመብት, BAYKARDEFENCE

የምስሉ መግለጫ, ቱርክ ሰራሹ ባይራክታር ቲቢ2

ባይራክታር ቲቢ2

ምንጮች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ለመግዛት የጠየቀችው እና ሞሮኮ ደግሞ የተረከበችው ቱርክ ሰራሹን ባይራክታር ቲቢ2 የተባለውን ሰው አልባ አውሮፕላን ነው።

ባይራክተር ቲቢ2 ከዋጋ አንጻር በሌሎች አገራት ከሚመረቱ ድሮኖች በአፈጻጸማቸው እጅግ የተሻሉ ናቸው ይባልል።

ይህ ድሮን የሚመረተው ባይራክታር በተሰኘ ኩባንያ ሲሆን ባይራክተር ቲቢ2 የሚሰኘው ድሮን ደግሞ ዲዛይን የተደረገው የፕሬዝደንት ኤርዶሃን አማች በሆነ ግለሰብ ነው።

ባይራክታር ቲቢ2 የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራትን ጨምሮ በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ገዝተው ታጥቀውታል። አልያም የራሳቸው ለማድረግ ከቱርክ ጋር ውል ይዘዋል።

ድሮን አምራቹ ባይካር ዲፌንስ በአሁኑ ወቅት ወደ 160 ባይራከታር ቲቢ2 ድሮኖች በቱርክ፣ በኳታር፣ በዩክሬን እና በአዘርባጃን አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው ይላል።

ባለፈው ግንቦት ወር ላይ የኔቶ አባል የሆነችው ፖላንድ 24 የሚደርሱ እነዚህን ድሮኖች ለመግዛት ከስምምነት ደርሳለች።

የፖላንድ መከላከያ ሚንስትር ባይራከታር ቲቢ2 ድሮኖች "ብቃታቸውን በጦርነት ውስጥ አስመስክረዋል" ሲሉ ለአገሪቱ ራዲዮ ጣቢያ ስለመናገራቸው ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።

የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ሳዑዲ አረቢያ የቱርክን ድሮን የመግዛት ፍላጎት እንዳላት እንዲሁ ገልጸዋል።

ባይራከታር ቲቢ2 በጦር ቀጣና ውስጥ

ባይራከታር ቲቢ2 ለስለላ ወይም የጥቃት ተልዕኮዎችን እንዲወጣ ተደርጎ የተሰራ ነው።

እስከ 150 ኪሎ ግራም ክብደት ይዞ መብረር የሚችለውን ይህ ድሮን እስከ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ሆኖ ድሮኑን መቆጣጠር ይቻላል።

በአምራቹ ድረ ገጽ ላይ እንደሰፈረው የዚህ ድሮን ክንፍ ርዝመት 12 ሜትር፣ ቁመቱ 2.2 ሜትር፣ ርዝመቱ 6.5 ሜትር ሲሆን 300 ሊትር ነዳጅ የመያዝ አቅም አለው።

ይህ ድሮን የሰው ቁጥጥር ሳይደረግበት በራሱ ሥርዓት መነሳት እና ማረፍ የሚችል ሲሆን ከ18 ሺህ አስከ 27 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ተልዕኮውን ይወጣል።

ይህ ድሮን 4 ሮኬት/ቦምብ ወይም ሚሳኤል መታጠቅ ይችላል።

በቅርቡ በአዘርባጃን እና በአርሜኒያ መካከል በተከሰተው ጦርነት አዘርባጃን በድል እንድትወጣ ይህ የቱርክ ድሮን ጥቅም ከፍ ያለ እንደነበር በስፋት ተዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም ቱርክ ድሮኖቿን በሶሪያ እና በሊቢያ ጦርነቶች ላይ ጥቅም ላይ አውላለች።

ድሮን በትግራዩ ጦርነት

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ የፌደራሉ መንግሥት በህወሓት አማጺያን ላይ ድሮኖችን ስለመጠቀሙ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች በስፋት ሲወጡ ቆይተዋል።

ምንም እንኳን ቢቢሲ በዚህ ግጭት የትኞቹ ድሮችን ለየትኛው ወታደራዊ ተልዕኮ ጥቅም ላይ ውለዋል የሚለውን ማረጋገጥ ባይችልም፣ ጠቅላይ ሚንሰትር ዐቢይ አሕመድ ግን ድሮን በዚህ ግጭት ጥቅም ላይ ስለመዋሉ አመላክተው ነበር።