የሜክሲኮ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን ፖሊስን በድሮን ደበደበ

የፀጥታ ኃይሎች መንገድ ዘግተው

የፎቶው ባለመብት, Michoacán State Security Department

ሜክሲኮ ውስወጥ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ፖሊስ ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን [ድሮን] ጥቃት ፈፅመዋል።

ሰው አልባዎቹ አነስተኛ አውሮፕላኖች ፖሊስ ላይ በጣሉት ፈንጂ ምክንያት ሁለት መኮንኖች መጎዳታቸው ተሰምቷል።

አመፀኛው ያሊስኮ ኒው ጄኔሬሽን የተሰኘው ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን ሳይሆን አይቀርም ጥቃቱን የፈፀመው ይላሉ የአካባቢው ባለሥልጣናት።

አመፀኞች ማክሰኞ ዕለት ፖሊስን በድሮን የደበደቡት በደቡባዊቷ የሜክሲኮ ግዛት ሚኮካን ነው።

ባለፈው ነሐሴ ሁለት ድሮኖች የዚህ አመፀኛ ቡድን ንብረት በሆነች መኪና ውስጥ ተገኝቶ ነበር።

በዕፅ አዘዋዋሪዎችና በፖሊስ መካከል ጥል የማይጠፋት ሜክሲኮ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቅም ላይ መዋል የጀመረባት በቅርቡ ነው።

ምንም እንኳ ስለጥቃቱ ዝርዝር መረጃ ባይወጣም ቡድኑ ሁለት ድሮኖችን እንደተጠቀመ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ጥቃት የተፈፀመባቸው ድሮኖች ነሐሴ ላይ መኪና ውስጥ ከተገኙት ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ተነግሯል።

ባለፈው ነሐሴ የተገኙት ድሮኖች በውስጣቸው የሚፈነዱ ፕላስቲኮችና ክብ ቅርፅ ያላቸው ጠጠሮች ይዘው ነበር።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ድሮኖቹ እስከሞት የሚያደርስ ጥቃት አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

በማክሰኞው ጥቃት የደረሰባቸው ፖሊስ ወደ ሚኮካን ግዛቷ አጉዊሊላ ከተማ ያቀኑት ቡድኑ የዘጋውን መንገድ ለማስከፈት ነበር።

ያሊስኮ ኒው ጀኔሬሽንና ካርቴሌስ ዩኒዶስ የተሰኙት ቡድኖች ከተማዋን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን የእርስ በርስ ውጊያ በመፍራት የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ጥለው እየወጡ ነው።

ባፈለው ወር በሁለቱ አመፀኛ ቡድኖች መካከል ውጊያ ከተደረገ በኋላ ሰውነታቸው የተተለተለ ስምንት ሰዎች ሬሳ ተገኝቶ ነበር።

አጉዊሊላ፤ የያሊስኮ ኒው ጄኔሬሽን አለቃ ኔሜሲዮ ሴርቫንቴስ [ኤል ሜንቾ] የተወለደባት ከተማ ናት።

ኤል ሜንቾ ሜክሲኮ ውስጥ በጥብቅ ከሚፈለጉ ሰዎች መካከል ሲሆን የአሜሪካው ዕፅ ዝውውር ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ሰውዬው ያለበትን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ብሏል።

የሰውዬው ቡድን ሃገሪቱ ውስጥ ካሉ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ጉልበተኛውና የፖሊስ ኃይሎች ላይ ለደረሱ በርካታ ጥቃቶች ተጠያቂው ነው ይባላል።

በፈረንጆቹ 2015 ያሊስኮ ውስጥ ቡድኑ በፈፀመው ጥቃት 15 የፖሊስ መኮንኖች መሞታቸው ይታወሳል።

በያሊስኮ ከተማ የተመሠረተው ይህ ቡድን አሁን መሠረቱን በመላው ሃገሪቱ ክፍሎች ጥሏል።

የፀጥታ ኃይሎች እንደሚሉት ቡድኑ የሜክሲኮ ፖሊስ ኃላፊ የሆኑት ኦማር ጋርሲያ ሃርፉች ላይ የግድያ ሙከራም አድርጓል።

ቡድኑ ፖሊሶች ላይ ጥቃት የሚያደርሰው የኤል ሜንቾ ልጅ ሩበን ኦሴጉዌራ ጎንዛሌዝ ወይም ሜንቾ ትንሹ በዕፅ ዝውውር ተጠርጥሮ ለአሜሪካ ተላልፎ በመሰጠቱ ነው።