በኦሃዮ ግዛት ፖሊስ የ16 አመት ጥቁር ታዳጊ ሴትን በጥይት ገደለ

በአሜሪካዋ ኦሃዮ ግዛት ፖሊስ የ16 አመት ጥቁር ታዳጊ ሴት በጥይት ተኩሶ መግደሉ ተዘግቧል።
ፖሊስ በአካባቢው የቢላ መውጋት ሙከራ ተደርጓል በሚል አስቸኳይ የስልክ ጥሪ ደርሶት ነው ወደ አካባቢው የደረሰው ተብሏል።
ከፖሊስ በተተኮሰባት ጥይት የተገደለችው ታዳጊ ማኪያ ብሪያንት ትባላለች።
በኦሃዮ፣ የየኮሎምበስ ፖሊስ በበኩሉ ታዳጊዋ ላይ ጥይት ከመተኮሱ በፊት ሌሎች ሰዎች ላይ በቢላ ጥቃት ለማድረስ እየሞከረች አለኝ በማለት እንደ ማስረጃነት ከመኪና የተቀረፀ ቪዲዮ አሳይቷል።
በአሁኑ ወቅት በግድያው ላይ ምርመራ የተከፈተ ሲሆን ባለስልጣናቱም የአካባቢውን ነዋሪ ተረጋጋጉ በማለት በመጠየቅ ላይ ናቸው።
በግድያው ላይ ተሳትፏል የተባለው ፖሊስ ከደመወዙ ጋር እረፍት እንዲወስድ ተደርጓል።
በኦሃዮ ግዛት በምትገኘው ኮሎምበስ ከተማ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ በአንድ ሰፈር አካባቢ ረብሻ በመነሳቱ ፖሊስ እንዲደርስ ጥሪ የቀረበለት ከሰዓት 10፡45 አካባቢ ነበር።
ከፖሊስ መኪና የተቀረፀው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ከአንድ ቤት ውጭ በተሰበሰቡ ግለሰቦች መሃል ጭቅጭቅ መነሳቱንና ማኪያ ብሪያንት የተባለችው ታዳጊ በአንደኛው ቡድን አባል የጩቤ ጥቃት ስትሰነዝር ያሳያል።
ፖሊስ ቡድኑን ተጠግቶ መሬት ላይ ተንበርከኩ በማለት በርካታ ጥይት ተኩሶ ታዳጊዋንም ክፉኛ ተኩሶ አቁስሏታል።
በቪዲዮውም ላይ ፖሊሱ "ቢላ ይዛለች፤ ተኩስ" የሚለው ድምፁ የሚሰማ ሲሆን በአካባቢው ሁኔታውን ሲታዘብ የነበረ ግለሰብ ህፃን ልጅ ናት ሲል ይሰማል።
ባለስልጣናቱ ፖሊስ ታዳጊዋ ላይ የተኮሰባት የሌሎቹን ታዳጊዎች ህይወት ለማዳን ነው ብለዋል። የማኪያ አክስት በበኩሏ ለአካባቢው ሚዲያ እንደተናገረች የእህቷ ልጅ ጥቃት ደርሶባት ራሷን እየተከላከለች ነበር ብላለች።
ሃዜል ብሪያንት የተባለችው የታዳጊዋ አክስት ለአንደኛው ቴሌቪዥን እንደተናገረችው "በጣም ጥሩ ልጅ ነበረች። አዎ እንደ ሁሉም ታዳጊ ልጆች ረባሽ ልትሆን ትችላለች ነገር ግን እንደ ውሻ በጎዳና ላይ መሞት አይገባትም" ብላለች።
የማኪያ እናት ፓውላ ብሪያንት በበኩላቸው "ተጎድቻለሁ፣ ተሰብሬያለሁ" በማለት በልጃቸው ሞት ሃዘናቸውን የገለፁ ሲሆን ልጃቸው "ሰው ወዳጅ ነበረች" ብለዋል።
"ይሄ መፈጠር አልነበረበትም፤ መልሶች እፈልጋለሁ" በማለት በኃዘን በተሰበረ ድምፃቸው ተናግረዋል።












