ዴሪክ ሾቪን በጆርጅ ፍሎይድ የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ

የቀድሞ የፖሊስ አባል ዴሪክ ሾቪን በጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጥፋተኛ ነው ሲል የዳኞች ቡድን ብይን ሰጠ።
የ45 ዓመቱ ዴሪክ ሾቪን ከወራት በፊት ጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ የተጠርጣሪው አንገት ላይ ከ9 ደቂቃዎች በላይ በጉልፈቱ አፍኖ ሲቆይ በተንቀሳቃሽ ምስል ተቀርጾ ነበር።
ይህ የቀድሞ የፖሊስ አባል ተግባር በርካቶችን አስቆጥቶ የነበረ ሲሆን፤ የፖሊስ አባሉ አላስፈላጊ ኃይል ተጠቅሟል በሚል እና ዘረኝነትን በመቃወም በመላው ዓለም የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደው ነበር።
ሾቪን በአገሪቱ የወንጀል ሕግ፤ በሦስት የግድያ ወንጀል ክሶች ነው ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው።
የቀድሞ የፖሊስ አባል የእስር ፍርድ እስኪሰጠው ድረስ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይቆያል። ሾቪን ምናልባትም አስርት ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ ሊፈረድበት ይችላል።
12 አባላት ያሉት የዳኞች ቡድን የቀድሞ የፖሊስ አባሉን ጥፋተኛ ለማለት ከአንድ ቀን ያነሰ ጊዜ ብቻ ነበር ያስፈለጋቸው።
ዳኞቹ ከዚህ ብይን ከመድረሳቸው በፊት የ45 ምስክሮችን ቃል ያደመጡ ሲሆን በርካታ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንም ተመልከተዋል።
የተከሳሽ ጠበቆች እና ከሳሽ ዐቃቤ ሕግም ለሦስት ሳምንታት የዘለቀ ክርክር አድርገው ነበር።
የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኛቸው አካሉ ግዙፍ የሆነ እና ከሦስት የፖሊስ አባላት ጋር ሲታገል የነበረን ተጠርጣሪ በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ የወሰደውን እርምጃ የትኛውም የፖሊስ አባል ሊያደርገው የሚችለው ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
ጠበቆች ደንበኛቸውም የሚወስደው ተግባር በሙሉ በተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚቀረጽ ስለሚያውቅ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ሆነ ብሎ አይወስድም ብለዋል።
ከሳሾች በበኩላቸው ዴሪክ ሾቪን በጆርጅ ፍሎይድ አንገት ላይ ከ9 ደቂቃዎች በላይ በጉልበቱ ተጭኖ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል በማጣቀስ "የምታዩትን እመኑ። ያያችሁትን አይታችኋል" የሾቪን ተግባር የፖሊስ ሳይሆን ግድያ ነው ብለውም ተናግረዋል ከሳሹ።
ሁለቱ አካላት መከራከሪያቸውን ካቀረቡ በኋላ 12 አባላት ያሉት የዳኞች ቡድን ምስጢራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ ውሳኔያቸውን አስተላልፈዋል።
የዳኞቹ ውሳኔ እንደተሰማ ከፍርድ ቤቱ ውጪ ሆነው ዜናውን ሲጠባበቁ የነበሩት ሰዎች ደስታቸውን ገልጸዋል። የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ ጠበቃ፤ ይህ በአሜሪካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
ከውሳኔው በኋላ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ አባላት ጋር ስልክ ደውለዋል።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፤ ከቤተሰቡ ጋር በነበራቸው ንግግር፤ "ቢያንስ አሁን ፍትህ አለ" ሲሉ ተደምጠዋል።
ሾቪን ውሳኔውን በተመለከት ይግባኝ እንደሚለው የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በስፋት እየገለጹ ይገኛሉ።















