ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ የተገደሉባት የቻድ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

Chad's President Idriss Deby Itno (file photo)

የፎቶው ባለመብት, EPA

የሟቹ የቻድ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ መጨረሻ አነሳሳቸውን የሚያስታውስ ነው። ዴቢ በ1990 (እአአ) በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ነበር ስልጣን ከሄስኔ ሃበሬ የቀሙት።

በተመሳሳይም ፕሬዝዳንት ዴቢ ከስልጣን ሊያወርዷቸው በሚፈልጉት አማጽያን ጉዳት ደርሶባቸው ህይወታቸው አለፈ።

ከስልጣን ሊያወርዷቸው በሚታገሉት አማጽያን እጅ ሞትን ተቀበሉ።

ዴቢ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም ጦር ሜዳ እየተገኙ ወታደሮቻቸውን ይጎበኛሉ። "ተዋጊው መሪ" በመባል የሚታወቁት ዴቢ ነሐሴ 2020 ከገዢው ከፓትሪዮቲክ ሳልቬሽን ሙቭመንት ፓርቲ 'ማርሻል ኦፍ ቻድ' የሚል ማዕረግ ተሰጣቸው።

ሠራዊቱ በመንግሥታዊው 'ቴሌ ቻድ' ቴሌቪዥን በሰጠው መግለጫ ዴቢ "በመጨረሻ በጦር ሜዳ ተገኝተው የአገሪቱን አንድነት ሲያስጠብቁ አልፈዋል" ብሏል።

"በጦር ሜዳ ላይ የደረሰባቸውን ጉዳት ተከትሎ የቻድ ማርሻል ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ህይወታቸው ማሉን ለቻዳውያን ስናሳውቅ በታላቅ ሀዘን ነው።"

ዴቢ "ከሊቢያ ከመጡ አሸባሪ ቡድኖች ጋር የተካሄደ ውጊያ በጀግንነት ሲመሩ እንደነበር" እና ወደ ዋና ከተማዋ ንጃሜና ህክምና ሲያቀኑ ህይወታቸው ማለፉን አክሏል።

ቱቡ ሚዲያ በትዊተር ገጹ እንደዘገበው ዴቢ በሰሜን ንጃሜና በምትገኘው ካኔም ግዛት ከፍሮንት ቼንጅ ኤንድ ኮንኮርድ ኢን ቻድ (ፋክት) ጋር በነበረ ግጭት ነው የቆሰሉት።

ኢድሪስ ዴቢ (በግራ በኩል) በሄሴኔ ሃብሬ ላይ አማጺያንን መርተው ከ21 ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን በመጡበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኢድሪስ ዴቢ (በግራ በኩል) በሄሴኔ ሃብሬ ላይ አማጺያንን መርተው ከ21 ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን በመጡበት ጊዜ

ወታደር ስልጣኑን ይቆጣጠራል

ዴቢ አገሪቱን በኃይል መርተዋል። ተቺዎቻቸውን እና ተቀናቃኞቻቸውን ያለ ርህራሄ አፍነዋል። ለምሳሌ ቻድ በ2018 ከተሞከረው የመፈንቅለ መንግሥት ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር አልነበራትም።

ታኅሣሥ 2020 ይፋ የተደረገው አዲስ ሕገ-መንግሥት የምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታን ቢፈጥርም ዴቢ እስከተገደሉበት ጊዜ ማንም አልተሾመበትም።

የቅርቡ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የተቃናቃኞቻቸውን ጥያቄ "የዲሞክራሲ ሥርዓት ማለት ሥርዓት አልበኝነት አይደለም" በማለት ዴቢ ውድቅ አደርገዋል።

ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ላይ ዘመዶቻቸውን እና የሚቀርቧቸውን በመሾም ስልጣን ዘመናቸውነ ሲያራዝሙ ቆዩ። ልጃቸው ጄኔራል ማሐማት ኢድሪስ ዴቢ የፕሬዚዳንታዊው ጥበቃ ኃላፊ ነበሩ።

የአገሪቱ አመራር ቦታ በፕሬዚዳንቱ ዘመዶች በመታጠሩ ለዴቢ የሚሆን የፖለቲካ ተተኪ የለም ማለት ነው።

የዴቢን ሞት ተከትሎ ሠራዊቱ ስልጣኑን መቆጣጠሩ አያስደንቅም።

ሠራዊቱ እንደገለጸው ፓርላማውና መንግሥት አስተዳደሩ መበተኑንና በመሐማት ዴቢ የሚመራ 15 አባላት ያሉት የሽግግር ወታደራዊ ምክር ቤት "የአገሪቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ" መሾሙን አስታውቋል። አዲስ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ወታደራዊው ቡድን ጁንታ ለ18 ወራት አገሪቱን ያስተዳድራል።

ሕገ መንግሥቱ ተሰርዞ በመሐማት ዴቢ በሚተላለፍ የሽግግር ቻርተር ይተካል። ወታደራዊ ኃይል በአገር አቀፍ ደረጃ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ንጋት 11 ሰዓት የሚቆይ የሰዓት እላፊ ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል።

ማሐማት ዴቢ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ማሐማት ዴቢ

ማት ኢድሪስ ዴቢ

ማሐማት ከ2014 ጀምሮ የፕሬዚዳንታዊ ጥበቃ ኃላፊ፣ የመንግሥት ተቋማት የደኅንነት አገልግሎቶች ዋና ዳይሬክቶሬት ሆነው አገልግለዋል።

በ2013 በማሊ የቻድ ኃይሎች ምክትል ኃላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን አዲሱን ኃላፊነት በመረከብ ወደ አገራቸው ከመመለሳቸው በፊት ከፈረንሳይ ኃይሎች ጎን በተለያዩ ተልዕኮዎች ላይ ተሳትፈዋል ተብሏል።

ማሐማት ከአማጽያን ጋር በምዕራባዊው የካኔም ግዛት በተደረገው ፍልሚያ አባታቸው ሲቆስሉ አብረዋቸው ነበሩ።

"ጄኔራል ካካ" በመባል የሚታወቁት ማሐማትም ከአንዳንድ ወንድሞቹ በተቃራኒ ብልህነት እና ታዋቂነትን በማሳየት ዝና አላቸው። ልክ እንደ አባታቸው በጦርነት ከጥቃት የተረፉ ወታደር ናቸው።

"ፕሬዚዳንቱ [ኢድሪስ ዴቢ] ከታዋቂ ቻዳውያን እና ከሚግቧቧቸው መንግሥታት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ጋር ማሐማት እንዲገናኙ አድርገዋል። ለሥልጣን አንዲበቁም በአባታቸው በሚሰጣቸው መንገድ ነበር" ሲል ጁን እፍሪክ ዘግቧል።

ሟቹ ዴቢ ብዙ ወንድ ልጆች ነበሯቸው። አንዳንዶቹም በመንግሥታቸው ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። በማሐማት እና በአንዳንድ ወንድሞቹ መካከል ውዝግብ ሊፈጠር ይችላል።

ተቃዋሚዎች የሽግግር ወታደራዊ ምክር ቤቱን ውድቅ አድርገዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሌህ ኬብዛቦ እና የተቃዋሚ ፓርቲው ፍሪደምስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት መሐመድ አህመድ አልሃቦ በበኩላቸው የሽግግር መንግሥቱ በብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዲመራ መጠየቃቸውን 'ሌ ጆርናል ደ ቻድ' ዘግቧል።

ተቃዋሚዎች የተዳከሙ እና የተከፋፈሉ በመሆናቸው ለወታደራዊው ጁንታ ከፍተኛ ተግዳሮት የመሆን ዕድል የላቸውም።

ፕሬዝዳንት ዴቢ (ከግራ ሁለተኛ) ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን (ከቀኝ ሁለተኛ) ከሌሎች መሪዎች ጋር በመሆን ስለቀጣናዊ ደኅንንት ባለፈው ዓመት በተወያዩበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዴቢ (ከግራ ሁለተኛ) ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን (ከቀኝ ሁለተኛ) ከሌሎች መሪዎች ጋር በመሆን ስለቀጣናዊ ደኅንንት ባለፈው ዓመት በተወያዩበት ወቅት

ለአማያን የሞራል ማሻሻያ

በካኔም ጦርነት ከባድ ኪሳራ እንደደረሰባቸው የተዘገበው አማጽያኑ የዴቢ ሞት ሁኔታውን ሊያሳምርላቸው ይችላል። ሠራዊቱ ከአማጽያኑ ጋር በካኔም በተደረገው ውጊያ ከ300 በላይ አማጽያን የተገደሉ ሲሆን 150 ደግሞ ቆስለዋል።

የአማጽያኑ መሪ ማሐማት መሃዲ አሊ ከፈረንሳዩ አርኤፍአይ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የደረሰባቸው ኪሳራ እውነት መሆኑን አምነዋል።

"ያልተለመደው ዓይነት ግጭት ነበር። ከሁኔታዎች አንጻር ታክቲካዊ ማፈግፈግ አደረግን" ያሉት መሪው የቻድ ጦር በፈረንሣይ አየር ኃይል የተደገፈ መሆኑን ቢገልጹም ፓሪስ ውድቅ አደርጋዋለች።

አማጺው ከ2016 ጀምሮ ከደቡብ ሊቢያ እየተነሳ ጥቃት ያደርስ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ ወደ ንጃሜና ለማቅናት ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ቡድኑ በሁለት ቀናቱ የካኔም ውጊያ 15 ከፍተኛ የቻድ ወታደራዊ መኮንኖችን ገድያለሁ ወይም አቁስያለሁ ብሏል።

ኪሳራ ቢደርስበትም ከ1,500 በላይ ተዋጊዎችን እንዳሉት የሚዘገበው የፋክት አማጽያን ቻድ በዴቢ ሞት በምታዝነበት በዚህ ወቅት አዳዲስ ጥቃቶችን ሊያደርስ ይችላል።

የዴቢ ሞት ለቻድ ታጠቂ ቡድኖች የመሰባሰቢያ ጥሪ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።

ሌላኛው አማጺ ቡድን ከአገሪቱ ሠራዊት ጋር የሚፋለመውን አማጺ ያወደሰ ሲሆን ሁሉም የቻድ አማጺያን ቡድኖች በአንድ ተሰባስበው የዴቢን አገዛዝ እንዲከስልጣን እንዲያወርዱ ጠይቋል።

ኢድሪስ ዴቢ ከመሞታቸው በፊት በተካሄደው ምርጫ ላይ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኢድሪስ ዴቢ ከመሞታቸው በፊት በተካሄደው ምርጫ ላይ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ

ቀጣናዊ የፀረ-ሽምቅ አንቅስቃሴዎች

የዴቢ ሞት በሳሀል እና በቻድ ሐይቅ አካባቢ በጂሃዳዊ አማጽያን ላይ የቻድን መንግሥት ወታደራዊ ዘመቻ መቀጠል ጥርጣሬ ውስጥ ጥሎታል።

ቻድ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ በማሰማራት አገራቱን እና የፈረንሣይን በአልቃይዳ እና በኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ታጣቂዎች ላይ የምታደርገውን ውጊያ እየረዱ ነው።

የቻድ ወታደሮች ቦኮ ሃራምን እና ኢስላሚክ ስቴት በምዕራብ አፍሪካ በቻድ አቅራቢያ ከሚገኙት ናይጄሪያ፣ ኒጀር፣ ካሜሩን እና ቻድ ጋር በመተባበር ላይ ይገኛሉ።

ዴቢ በክልላዊ የፀረ-ሽምቅ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ የቻድን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ከፍ ያደረገ ሲሆን ከምዕራቡ ዓለም በተለይም ከፈረንሳይ፣ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍን እንድታገኝ አድርጓል።

ለምሳሌም 5,200 የወታደሮች በማሊ ቢሰማሩም የኦፕሬሽን ባርካኔ ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫው ቻድ ነው።

የፋክት አማጽያን ንጃሜናን ኢላማ ያደረጉ ሲሆን ዴቢንም ገድለዋል። ወታደራዊው ምክር ቤት በአገር ውስጥ በሚካሄደው አመጽ ላይ በማተኮር የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቀንስ ስለመሆኑ ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።

በነሐሴ ወር 2020 በማሊ የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በጭፍን መደገፏን ከሚገልጹ መረጃዎች አንፃር ፈረንሳይ ቻድ ውስጥ ለሠራዊቱ ስልጣን መያዝ የምትሰጠው ምላሽ ትኩረትን የሚስብ ነው።