የቻድ ፕሬዝዳንት ለስድስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እየተሳተፉ ነው

ድምጽ የምትሰጥ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቻድ ዜጎች በአፍሪካ ታሪክ ለረጅም ዓመታት አገር የመሩት ፕሬዝዳንት ለስድስተኛ ጊዜ በሚወዳደሩበት ምርጫ ላይ ድምጻቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ በአውሮፓውያኑ 1990 ላይ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከያዙ በኋላ የምርጫ ድምጾችን ያፍናሉ የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል።

በርካታ ዋነኛ ተቀናቃኞቻቸው በደህንነት ኃይሎች ጥቃት እየተፈጸመብን ነው በማለት ከምርጫው እራሳቸውን አግልለዋል። ደጋፊዎቻቸውንም ምርጫውን እንዳያደርጉና ተቃውሞ እንዲያሰሙ ጠይቀዋል።

ዕሁድ ዕለት ምርጫ በሚካሄድበት አካባቢ እና በዋና ከተማዋ 'ንጃሜና' ጎዳናዎች ላይ በርካታ ወታደሮች ተሰማርተው የተስተዋሉ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች ምናልባት አመጸኞች እሳት ለማንደድ ሊጠቀሟቸው ይችላሉ ያሏቸውን ጎማዎች ሲሰበስቡ ነበር።

የአገሪቱ ሪፐብሊካን ጋርዶችም ፕሬዝዳንቱ መጥተው ድምጻቸውን በሰጡበት ማዕከላዊ የምርጫ ጣቢያ አካባቢ ተሰማርተዋል ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ከቦታው ዘግቧል።

ፕሬዝዳንቱ በምርጫ ጣቢያው ድምጻቸውን የሰጡ የመጀመሪያው ሰውም ናቸው።

'' ሁሉም የቻድ ዜጎች በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት የአገሪቱን ችግሮች መፍታት የሚችልና ድምጼ ይገባዋል የምትሉትን እጩ እንድትመርጡ አሳስባለሁ'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ።

ሂውማን ራይትስ ዋች ከምርጫው በፊት ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ከባድ ማስፈራራትና ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሏል። አክሎም በቅርቡ የተካሄዱ ጸረ መንግስት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች ያልተገባ ኃይል ተጠቅመዋል ሲል ሪፖርት አድርጓል።

ባሳለፍነው ወር የጸጥታ ኃይሎች ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ያያ ዲሎን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት አምስት የቤተሰቡ አባላት መገደላቸውን የሚወክሉት ፓርቲ ያስታወቀ ሲሆን መንግሥት ግን የሞቱት ሰዎች ሶስት ናቸው ብሏል።

በዚህ ምርጫ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ዋነኛው ተፎካካሪ እንደሆኑ ይታሰባል። ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የቆዩ ሲሆን በዚህኛው ዙር በአገሪቱ ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ሌሎች ስድስት ሰዎች በምርጫው ተፎካካሪ ሆነው ቀረቡ ሲሆን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አልበርት ፓሂሚ ፓዳኬ እና ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ፌሊክስ ኒያልቤ ሮማዶምጋር ዋነኞቹ ናቸው።

በዚህ ምርጫ ላይ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት እጩም ይፎካከራሉ። የቀድሞዋ የግብርና ሚኒስትር ሊይዲ ቤሳምዳ ምርጫውን የሚያሸንፉ ከሆነ በአገሪቱ ያለው የብሄር ክፍፍል ለማጥፋትና የሴቶችን እኩልንት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

መጀመሪያ ላይ 16 የነበሩት ተፎካካሪዎች መካከል አንዳንዶቹ እራሳቸውን በማግለላቸው ሌሎቹ ደግሞ ተገድደው በመውጣታቸው ምክንያት አሁን ላይ 6 ተፎካካሪዎች ብቻ ቀርተዋል።