የቻዱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ከአማጺያን ጋር በተደረገ ውጊያ መሞታቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቻዱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ አማጺያንን የሚዋጉ ወታደሮቻቸውን ለመጎብኘት ወደ በጦር ግንባር በሄዱበት ወቅት በደረሰባቸው ጉዳት ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።
ፕሬዝዳንቱ በጦር ግንባር ሳሉ ተመተው መሞታቸውን የገለጸው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ነው።
ፕሬዝዳንት ዴቢ ለህልፈት የተዳረጉት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ከአማጺያን ኃይሎች ጋር ባለፈው ሳምንት ማብቂያ በተደረገ ውጊያ ላይ በድንገት እንደነበር ሠራዊቱ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ላይ አስታውቋል።
የቻድ ጦር ሠራዊት በአሁኑ ጊዜ በዋና ከተማዋ ንጃሚና ላይ ጥቃት የከፈቱትን አማጺ ኃይሎችን እየተዋጋ እንደሚገኝ ተነግሯል።
የፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ሞት የተነገረው ሰሞኑን ቻድ ውስጥ የተደረገው ምርጫ ላይ የ80 በመቶውን መራጭ ድምጽ በማግኘት ለስድስተኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት ለመቆየት የሚያስችል ጊዜያዊነት ውጤት እንዳገኙ ከተገለጸ በኋላ ነው።
ምርጫው በጣሙን አወዛጋቢ የነበረ ሲሆን ዋነኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲ ፓርቲ ዕጩዎች በመንግሥት ኃይሎች ደረሰብን ያሉትን ጥቃት ምክንያት አድርገው ከውድድሩ መውጣታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ዴቢ በምርጫ ማሸናፋቸውን አስመልክተው የሚያደርጉትን የድል ንግግራቸውን ወደ ሌላ ቀን አስተላልፈው ነበር ወታደሮቻቸውን ለመጎብኘት ወደ ጦር ግንባር ያመሩት።
ፕሬዝዳንት ዴቢ በአገራቸው ባለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ የተነሳ ሲተቹ የቆዩ ሲሆን፤ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱትን ከአልቃኢዳና ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ቦኮ ሐራምንና ሌሎች ቡድኖችን ለመዋጋት የተሰለፈችውን የፈረንሳይና የሌሎች አገራት ቁልፍ አጋር ናቸው።
የፕሬዝዳንቱን ሞት ተከትሎ የቻድ መንግሥትና ፓርላማ የተበተነ ሲሆን ወታደራዊ ምክር ቤት አገሪቱን ለቀጣይ 18 ወራት እንደሚያስተዳድር ተነግሯል።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ሊቢያ ውስጥ መሽገው መንግሥታቸውን ለመጣል ከዋጉት አማጺያን ጋር የሚፋለሙትን ወታደሮቻቸውን ለመጎብኘት ነበር የተጓዙት።
አገሪቱ በቴሌቪዥን ላይ በተነበበው መግለጫ ላይ የጦር ሠራዊቱ ቃል አቀባይ ጄነራል አዜም ቤርማንዶዋ አጉና ፕሬዝዳንት ዴቢ "አስከ መጨረሻ አስትንፋሳቸው ድረስ የአገራቸውን ሉአላዊነት ሲከላለኩ ነበር" ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱን ሞት መታወጅ ተከትሎ ከምስት 12 ሰዓት አስከ ንጋት አስራ አንድ ሰዓት የሚቆይ የሰዓት እላፊ ገደብ የተጣለ ሲሆን የአገሪቱ የየብስ ድንበሮች መዘጋታቸው ተነግሯል።
በሟቹ ፕሬዝዳንት ልጅ ማሐማት ኢድሪስ ዴቢ ሚመራ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት የተቋቋመ ሲሆን አገሪቱን ለ18 ወራት ይመራታል ተብሏል።
ኢድሪስ ዴቢ ወደ በፕሬዝዳንትነት ቻድን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የመሩ ሲሆን ስድስተኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን በቅርቡ ይጀምሩ ነበር።
ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ቻድን መምራት የጀመሩት እአአ ከ1990 ጀምሮ ነበር።














