በትግራይ በተፈፀሙ የአየር ጥቃቶች 108 ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል - የተባበሩት መንግሥታት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በትግራይ ክልል በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች ሳቢያ ከ100 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደልና የንብረት ውድመትን በተመለከተ የደረሱት ሪፓርቶች እንዳሳሰበው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፈጸመው በተባሉ የአየር ጥቃቶች ቢያንስ 108 ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውንና እና 75 ሰዎች መቁሰላቸውን ቃል አቀባይዋ ሊዝ ትሮሴል ገልጸዋል።
ጥቃቶቹ የደረሱት ባለፉት ሁለት ሳምንታት (ከፈረንጆቹ ጥር 1 ማለትም ታኅሣሥ 23 ጀምሮ ሲሆን) ተደጋጋሚና ክፉኛ የሚረብሹ ሪፖርቶችም ደርሰውናል ብለዋል።
በዚህ ሳምንት ረቡዕ ዕለት በተፈጸመ የአየር ጥቃት አንድ የ72 ዓመት አዛውንት ተገድለዋል ብሏል።
ማክሰኞ ጥር 03/2014 ዓ.ም የመንግሥት ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ማሰልጠኛ ተቋም ላይ በደረሰ ጥቃት ሦስት ወንዶች ሲገደሉ 21 ሰዎች መቁሰላቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን አብዛኞቹ የቆሰሉት ሴቶች ናቸው።
ሰኞ ዕለት ጥር 02፣ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ወፍጮ ቤት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በአካባቢው ተሰበስበው ከነበሩት መካከል 17 ሰዎች ሲገደሉ 21 ሰዎች ቆስለዋል፣ አብዛኛዎቹም ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።
ከሁሉ የከፋው የአየር ጥቃት የደረሰው የገና ዕለት ታኅሣሥ 29 ሲሆን በደደቢት የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ በተፈጸመው ጥቃት 56 ሰዎች ሲገደሉ 30 ሰዎች ቆስለዋል።
ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸውና ሆስፒታል በህክምና ላይ ከነበሩት መካከል ሦስቱ መሞታቸውን የገለጹት ቃለ አቀባይዋ የሟቾችም ቁጥር 59 ደርሷል ብለዋል።
ባለፈው ሳምንትም እንዲሁ በርካታ የአየር ጥቃት መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን እነዚህም ጥቃቶች ከአዲየት ወደ አክሱም ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ፣ ሺሬ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የማይ አይኒ ስደተኞች ካምፕ ይገኙበታል ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ባወጣው መግለጫ ከታኅሣሥ 10 አስከ 15 ድረስ በትግራይ ውስጥ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት መደረጉን አስፍሯል።
ኦቻ ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ከጥቅምት ወር ወዲህ ከተከሰቱት በጣም አስከፊና በርካታ ሞቶች ሪፖርት የተደረጉበት ተከተታይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን አመልክቷል።
በርካታዎቹ ጥቃቶች ሪፖርት የተደረጉት በደቡብ ትግራይ ከተሞች በአላማጣ፣ ኮረም፣ ማይጨው፣ መኮኒ እና ሚላዛት መሆኑን ጠቅሷል።
ነገር ግን በአካባቢው ባለው ውስን ተደራሽነት እና የፀጥታ ችግር ምክንያት የሰብአዊ አጋሮች የሟቾችን ትክክለኛ ቁጥር እስካሁን ማረጋገጥ እንዳልቻሉም ጠቅሷል።
ከሰሞኑም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ሦስት ኤርትራውያን በማይ አይኒ የስደተኞች ጣቢያ በአየር ጥቃት መገደላቸውን አስታውቋል።
ከሦስቱ ኤርትራዊያን ስደተኞች መካከል ሁለቱ ሕፃናት መሆናቸውን ኮሚሽኑ በኦፊሴላዊ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባደረጉት ውይይት በትግራይ በቅርቡ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች በሲቪል ዜጎች ላይ ስላደረሰው ሞት ያደረባቸውን ስጋት ተናግረዋል።
ከሰሞኑ ተፈጽመው በርካታ ሰዎችን ለሞት የደረጉትን የአየር ጥቃቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት አስካሁን ያለው ነገር የለም።
ቃለ አቀባይዋ በዚሁ መግለጫቸው ላይ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና አጋሮቻቸው በዓለም አቀፉ ሕግ በተጣለባቸው ግዴታዎች መሰረት ሲቪል ዜጎችንና ንብረታቸውን ጥበቃ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን ብለዋል።
"የአየር ጥቃትን ጨምሮ ማንኛውም ጥቃት ልዩነት ባለው መልኩ፣ በተመጣጠነና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ባከበረ መልኩ መሆን አለበት" ብለዋል።
የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ኢላማው ወታደራዊ መሆኑን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ ሁሉ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል ያሉት ቃለ አቀባይዋ ዒላማው ወታደራዊ ካልሆነ ወይም ጥቃቱ ተመጣጣኝ እንደማይሆን ካወቁ ሊያቆሙ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ልዩነቶችን ባላከበረ መልኩና ተመጣጣኝነት በሌለው መልኩ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር በተያያዘ የቀጠለው የዘፈቀደ እስራት እንዳሳሰባቸውም ጨምረው ተናግረዋል። በቅርቡ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከእስር መፈታታት እንደ መልካም እመርታ ቢታይም በርካቶች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በአስከፊ ሁኔታ በእስር ላይ መቆየታቸው ያሳስበናል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።












