ትግራይ ውስጥ ሰኞ በተፈጸመ የአየር ጥቃት 17 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

በአየር ድበደባ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/STRINGER

የምስሉ መግለጫ, በአየር ድበደባ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች

ሰኞ ዕለት ትግራይ ውስጥ በተፈጸመ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ቢያንስ 17 ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን ሮይተርስ የእርዳታ ሠራተኞችን ጠቅሶ ዘገበ።

በጥቃቱ ከተጎዱት መካከል አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውን የአካባቢውን ባለሥልጣናትና የአይን እማኞችን ጠቅሰው የእርዳታ ሠራተኞቹ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በአካባቢው የመገናኛ አገልግሎት ስለሌለ ስለጥቃቱና ስለደረሰው ጉዳት ለማረጋገጥ እንዳልቻለ አመልክቷል።

ቢቢሲ ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

ይህ ጥቃት የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት በተፈናቃይ መጠለያዎች ከ50 በላይ ሰዎችን ገድለዋል የተባሉትን የአየር ጥቃቶችን ተከትሎ ነው።

ባለፉት ሳምንታት በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎችን ለማሰብ የትግራይ ክልል ከጥር 05 አስከ 07/2014 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የሐዘን ጊዜን አውጇል።

ቀደም ሲል የመንግሥታቱ ድርጅት ግጭት እንዲቆምና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመሮች ክፍት እንዲሆኑ የጠየቀ ሲሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባላፈው እሁድ ከጠቅላይ ነሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ላይ የአየር ጥቃቶቹ እንዳሳሰቧቸው ማንሳታቸው ተግለጾ ነበር።

ባለፈው ሳምንት የተፈጸሙት ጥቃቶች በስደተኞችና በተፈናቃዮች መጠለያዎች ላይ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን የሰኞ እለቱ ደግሞ ማይ ጸብሪ በሚባለው ስፍራ አንድ ወፍጮ ቤት አቅራቢያ መሆኑ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያነበሩ የአማራና የአፋር ክልሎች ቦታዎችን መልሶ ከያዘ በኋላ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ጋብ ቢልም የአየር ጥቃቶች ግን ቀጥለዋል።

በዚህም ሳቢያ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሥራቸውን ማቋረጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ማሳወቁ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር ሄንሪታ ፎር ባለፈው ሳምንት የተፈጸሙትን ጥቃቶች ተከትሎ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ተጠልለው በሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያ ላይ የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸው የሚመሩትን ድርጅት እንዳሳዘነ ገልጸዋል።

ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው እና ለተፈናቃዮች መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን አለማክበር እና ከጥቃት አለመጠበቅ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ ጥሰት ጋር ሊስተካከል ይችላልም ብለው ነበር።

ባለፈው ሳምንት አርብ ሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ባለች ደደቢት ከተማ በሚገኝ የተፈኛቃዮች መጠለያ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት 56 ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ ደግሞ ማይ አይኒ በተባለ የስደተኞች መጠለያ ላይ በተፈጸመ አየር ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) አስታውቆ ነበር።

ባለፈው ሳምንትና በዚህ ሳምንት ውስጥ ተፈጽመው በርካታ ሰዎችን ለሞት የደረጉትን የአየር ጥቃቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት አስካሁን ያለው ነገር የለም።