የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር በመጠጥ ድግስ ተገኝተዋል በሚል ቁጣ በረታባቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በመላው ዩናይትድ ኪንግደም የኮቪድ እንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎ በነበረበት ወቅት ቦሪስ ጆንሰን በአንድ የመጠጥ ድግስ ላይ ተገኝተዋል በሚል ክፉኛ እየተብጠለጠሉ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ወቀሳ እያዘነቡ ያሉት የሌበርና በገዛ ፓርቲያቸው በኮንሰርቫቲቭ እንደራሴዎች ጭምር ነው።
ቦሪስ ወይ ፈጣን ምላሽ ይስጡ ወይም ሥልጣን በአስቸኳይ ይልቀቁ ሲሉ በርካታ የፓርቲ ተወካዮች ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ይህ የመጠጥ ድግስ ተደርጓል የተባለው ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ዳውኒንግ ጎዳና በሚገኘው መናፈሻ ነው።
ዳውኒንግ ስትሪት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋዊ መኖርያ እና ጽ/ቤት የሚገኝበት መንገድ ነው።
ወትሮም የጋለ ክርክርና ሙግት የማይጠፋበት የዩኬ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ድግስና የቦሪስ ጆንሰን በድግሱ ተገኝተዋል በሚለው ነጥብ ዙርያ ለቀናት ሲናጥ ነው ቆይቷል።
የሌበር ፓርቲ ምክትል አንጌላ ራይነር፣ 'የቦሪስ ጉድ ለጊዜው ተሸሽጎ ሊሆን ይችላል፣ ተደብቆ ግን አይዘልቅም፣ እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል' ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የመጠጥ ፌሽታ ድግስ ተደረገ የሚባለው እንደነርሱ አቆጣጠር በግንቦት፣ 2020 ዓ/ም ሲሆን ይህ ጊዜ ደግሞ ዩኬ በጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ የነበረችበት ወቅት ነው።
የስኮቲሽ ወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪ ዳግላስ ሮስ በበኩላቸው ቦሪስ ጆንሰን እንደሚባለው በወቅቱ የኮቪድ እንቅስቃሴ ገደብ ጥሰው ከነበረ ያለምንም ማወላወል ሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እስከአሁን በዚህ ድግስ ስለመገኘት አለመገኘታቸው ትንፍሽ አላሉም።
ሆኖም የዚህን ዜና ሾልኮ መውጣት ተከትሎ የተቆጡት እንደራሴዎች ዛሬ ረቡዕ በጥያቄና መልስ ሸንጎ ላይ የሚገኙትን ቦሪስ ጆንሰንን ፊት ለፊት ያፋጠጧቸዋል፣ መፈናፈኛም ያሳጧቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰኞ ዕለት አይቲቪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና የግል ጸሐፊያቸውን ማርቲን ሬይኖልድስ 100 የሚሆኑ ሰዎችን በቦሪስ መኖርያ በሚገኝ መናፈሻ ለመጠጥ ድግስ ጥሪ ያደረጉበትን ኢሜይል አሾልኮ በማውጣት ለሕዝብ ይፋ አድርጎታል።
ይህን ተከትሎ ነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሥልጣን ይልቀቁ ጥያቄ የበረታው።
የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት በወቅቱ በዚህ የመጠጥ ድግስ ላይ ቦሪስ ጆንሰን እና ባለቤታቸው ኬሪ ጆንሰን ተገኝተውም ተዝናንተውም ነበር።
የወግ አጥባቂው ፓርቲ የቀድሞ ሚኒስትር ጆኒ ሜርሰር በትዊተር ሰሌዳቸው፤ "ይህ እጅግ አሳፋሪ ነገር ነው፤ የቦሪስ ድርጊት የፓርቲያችንን አገርንና ሕዝብን ምሳሌ ሆኖ በመምራት ላይ የተመሠረተ ባሕል አይወክልም።" ሲሉ ጽፈዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታ ብቻ ሳይሆን የእርሳቸው ቃል አቀባይም ምላሽ አለመስጠት በዩኬ ነገሩን አነጋጋሪ አድርጎታል።












