ሴኔጋል፣ ኔዘርላንድ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ወደ ቀጣዩ የጥሎ ማለፍ ዙር ማለፋቸውን አረጋገጡ

የአሸናፊዋ የአሜሪካ እና ከውድድሩ የተሰናበተችው ኢራን ተጫዋች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሸናፊዋ የአሜሪካ እና ከውድድሩ የተሰናበተችው ኢራን ተጫዋች

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ወደ ጥሎ ማለፉ የተሸጋገሩ የምድብ አንድ እና ሁለት ቡድኖች ትላንት ማክሰኞ ምሽት በተደረጉ ጨዋታዎች ተለዩ።

ሴኔጋል፣ ኔዘርላንድ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ለቀጣዩ ዙር መብቃታቸውን አረጋገጠዋል።

ሴኔጋል ለሁለተኛ ጊዜ ለጥሎ ማለፉ መብቃቷን ያረጋገጠችው ኢኳዶርን በካሊፋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም 2 ለ 1 በማሸነፍ ነው።

ኢስማሊአ ሳር ከፍጹም ቅጣት ምት አገሩን ቀዳሚ ያደረገች ኳስ በ44ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳረፈ።

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ኢኳዶሮች በሞይሰስ ካሲዬዶ አማካይንት አቻ ለመሆን በቅተዋል።

ከሦስት ደቂቃ በኋላ የሴኔጋሉ አምበል ካሊዱ ኩሊባሊ ሁለተኛዋን ጎል በማስቆጠር አገሩን ቀዳሚ አደረገ።

ጨዋታው በዚሁ በመጠናቀቁ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሴኔጋል ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አገር ሆናለች።

በዚሁ ምድብ አስተናጋጇ ኳታር እና ኔዘርላንድም በአል ባይት ስታዲየም ተገናኝተዋል።

ቀድማ ከውድድሩ ውጪ መሆኗን ያረጋገጠችው ኳታር ሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታዋን ተሸንፋለች።

ኔዘርላንድ 2 ለ 0 ስታሸንፍ ጎሎቹን ኮዲ ጋክፖ እና ፍራንኪ ዲ ዮንግ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

በዚህም ኔዘርላንድ ምድቧን በቀዳሚነት ስታጠናቅቅ ሴኔጋል ሁለተኛ ለመሆን በቅታለች።

ምሽት ላይ ደግሞ የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ተከናውነዋል።

ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የዩናይትድ ስቴትስ እና የኢራን ጨዋታ ነበር።

ጨዋታውን ዩናይትድ ስቴትስ 1 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችላለች።

ብቸኛዋን ጎል ክርስቲያን ፑሊሲች አስቆጥሯል።

አቻ መውጣት ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፋት ኢራን ዕድሉን ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

በዚሁ ምድብ በተደረገ ሌላ ጨዋታ እንግሊዝ ዌልስን 3 ለ 0 አሸንፋለች።

ማርከስ ራሽፎርድ ለእንግሊዝ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር፣ ቀሪዋን ፊል ፎደን ከመረብ አሳርፏል።

በዚህም እንግሊዝ በሰባት ነጥብ ምድቧን በመምራት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች።

አሜሪካ በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ሆናለች።

በጥሎ ማለፉ እንግሊዝ ከሴኔጋል ትጫወታለች። አሜሪካ ደግሞ ኔዘርላንድን ትገጥማለች።

የዓለም ዋንጫው የምድብ ሦስት እና አራት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይከናወናሉ።

በምድብ አራት ቱኒዝያ እና ፈረንሳይ እንዲሁም አውስትራሊያ እና ዴንማርክ ምሽት 12 ሰዓት ይጫወታሉ።

ከምድብ አራት ፈረንሳይ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች። ቀሪዎቹ ሦስት አገራት ለጥሎ ማለፉ መብቃት ዕድል አላቸው።

አውስትራሊያ ሦስት ነጥብ ሲኖራት፣ ዴንማር እና ቱኒዝያ በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ምድብ ሦስት የሚገኙት ፖላንድ እና አርጀንቲና እንዲሁም ሳዑዲ አረቢያ እና ሜክሲኮ ምሽት አራት ሰዓት ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

በምድብ ሦስት የሚገኙ ሁሉም አገራት የማለፍ ዕድል አላቸው።

ፖላንድ ምድቡን በአራት ነጥብ ትመራለች። አርጀንቲና እና ሳዑዲ አረቢያ እኩል ሦስት ነጥብ ይዘዋል። ሜክሲኮ በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።