ፕሬዝዳንት አል ሲሲ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ከስምምነት እንዲደረስ ጥሪ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቅን ልቦና በሚካሄድ ንግግር ከስምምነት እንዲደረስ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት ሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የቻይና-አረብ አገራት ጉባኤ ላይ ባደረጉት አገራቸውን እና የአረቡን ዓለም በሚመለከተው ንግግራቸው ነው።
ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌትና የሥራ ሂደት በሚመለከት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ድርድር ቢያደርጉም ከስምምነት ላይ ሳይደርሱ መቅረታቸው ይታወሳል።
ግድቡ ከዓባይ ወንዝ የማገኘውን የውሃ መጠን ይቀንስብኛል የሚል ስጋት ያላባት ግብፅ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ በተለያዩ መድረኮች እንደሚያደርጉት ሁሉ አሁንም ከኢትዮጵያ ጋር ከስምምነት መድረስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
አል ሲሲ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የአረብ አገራት መሪዎች በታደሙበት ስብሰባ ላይ ባድረጉት ንግግር፣ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን አስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት እንዲደረስ ጠይቀዋል።
“ለአሁኑ እና ለመጪው ትውልድ የመልማት መብትን የሚያረጋግጥ እና ትብብራቸውን፣ መረጋጋታቸውን እንዲሁም ደኅንነታቸውን ከስጋት የሚጠብቅ በቅን ልቦና ላይ የተመሠረተ ንግግር በማድረግ አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ በድጋሚ ጥሪዬን አቅርባለሁ” ብለዋል ፕሬዝዳንት አል ሲሲ።
በተያያዘ ዜና የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት እንዳሳወቀው ከቻይና-አረብ አገራት ጉባኤ ጎን ለጎን አል ሲሲ የስብሰባው ተሳታፊ ከሆኑት የሱዳን የሽግግር ሉአላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ጋር ተወያይተዋል።
በሁለቱ መሪዎች ንግግር ወቅት ውሃ የሕዝባቸው ብሔራዊ ደኅንነት ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፣ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት መድረስ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው አል ቡርሐን የሱዳንን አቋም ማንጸባረቃቸው ተመልክቷል።
ይህ የፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጥሪ ከዚህ ቀደምም በራሳቸውን በበርካታ የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አማካይነት ሲቀርብ የቆየ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የግድቡ ጉዳይ አስከ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ድረስ ቀርቦ ነበር።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ላይ ከስምምነት እንዲደርሱ ለማድረግ በአሜሪካ መንግሥት እና በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ተከታታይ ድርድሮች ሲካሄዱ ቢቆዩም፣ በግብፅ በኩል አስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት እንዲደረስ ያለው ፍላጎት በዓባይ ውሃ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብቴን የሚጋፋ ነው በሚል ኢትዮጵያ ሳትቀበለው ቆይታለች።
ግንባታው አሥር ዓመታትን ያስቆጠረውና ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢትዮጵያን ያስወጣው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከስምምነት ሳይደረስ እንዳይካሄድ ከግብፅና ከሱዳን ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥመውም ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ እንዲይዝ ተደርጓል።
በአፍሪካ ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጭት ከተገነቡ ግድቦች ሁሉ ግዙፉ እንደሆነ የሚነገረው ይህ የኢትዮጵያ ግድብ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወቃል።
ቢሆንም ግን ግብፅ አሁንም ከወንዙ የምታገኘውን የውሃ መጠን ለማስጠበቅ የሚያስችላትን በግድቡ አጠቃላይ የሥራ ሂደት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ሕጋዊ ስምምነት እንዲደረግ ትፈልጋለች።
አል ሲሲ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻይና እና በአረብ አገራት መካከል በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ባድረጉት ንግግር ላይ የውሃ ደኅንነት ጉዳይ ከአገራቸው በተጨማሪ ሌሎች የአረብ አገራትንም የሚመለከት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ወደፊት በቻይና እና በአረብ አገራት መካከል በሚኖረው ትብብር ውስጥ የአረብ አገራት የውሃ ደኅንነት ጉዳይ ቅድሚያ ከሚሰጠቸው ጉዳዮች መካከል ከፊት ሊሆን እንደሚገባው አል ሲሲ ተናግረዋል።
የግብፁ ፕሬዝዳንት ንግግር ያደረጉበት በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የሚካሄደው የቻይና እና የአረብ አገራት ጉባኤ፣ ቻይና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ካሉ አገራት ጋር ያለትን ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ትስስሯን ለማጠናከር ከምታካሂደው ዘመቻ ጋር የተያያዘ ነው።












