ተዋናይ ታሪኩ ብርሃኑ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

የፎቶው ባለመብት, ETHIOGIRUM
በበርካታ ፊልሞች በመተወን በኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ዝናን ያተረፈው አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
የተለያዩ የኃገር ውስጥ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ተዋናዩ በህመም ላይ እንደነበረና ለሳምንታትም በህክምና ሲረዳ እንደቆየም ነው።
በቅጽል ስሙ ባባ በሚል የሚታወቀው አርቲስቱ ህመሙ ምን እንደነበር አልተገለጸም።
ከአርባ ያህል ፊልሞች የተወነው ታሪኩ ወንድሜ ያዕቆብ፣ ላውንድሪ ቦይ፣ ማርትሬዛ፣ ይመችሽ-የአራዳ ልጅ 2፣ ሞኙ የአራዳ ልጅ 4 በፊልም ታዳሚያን ዘንድ ተወዳጅነትን ካተረፈባቸው መካከል የተወሰኑት ናቸው።
በተጫማሪም አንድ ሁለት፣ ብር ርርር፣ ወደው አይሰርቁ፣ ወፌ ቆመች፣ እንደ ቀልድ፣ ወጥቶ አደር፣ አባት ሀገር የሚሉት ፊልሞችም አርቲስቱ ከተወነባቸው ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, BENYAM
አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ የአንድ ልጅ አባት እንደነበርም ተዘግቧል።
በርካቶች የአርቲስቱ አድናቂዎች ኃዘናቸውን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየገለጹ ሲሆን “ገና መስራት በሚችልበት በለጋ እድሜው በመቀጠፉም አዝነናል” ብለዋል።








