ከአምስት አስርት ዓመታት በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ በሂሩት አባቷ ማነው? ስንመለከት

የሒሩት አባቷ ማነው ፖስተር

የፎቶው ባለመብት, Menelik Mered

"በመጀመሪያ መፃሕፍት፣ ጋዜጦችና ሬዲዮ ብቻ ነበር። ቀጥሎ ቴሌቪዥን መጣ። ሰሞኑን ደግሞ፤ በሐገር ፊልምና ማስታወቂያ ማኅበር የተዘጋጀው ተንቀሳቃሽ ፊልም አደባባይ መጥቷል። የማስታወቂያ ሚኒስቴር ካሁን በፊት ካዘጋጃቸዉ ትምሕርትና ታሪክ ነክ ፊልሞች ሌላ 'ሒሩት አባቷ ማነዉ?' የሚል የመጀመሪያ ፊልም መጥቷል። የመጀመሪያው ሙከራ በመሆኑ፤ ሙከራውን ማደፋፈር ተገቢ መሆኑ ይሰማናል።"

ይህ ጽሁፍ ነሐሴ 23/1957 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከታተመው ሒሩት አባትዋ ማነው? ፊልም ምረቃን አስመልክቶ ሐያሲው ብርሃኑ ዘሪሁን ከጻፉት የተወሰደ ነው።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ባለ 35 ሚሊ ሜትር ተንቀሳቃሽ ልብወለድ ፊልም "ሒሩት አባትዋ ማነው?" ለዕይታ ከበቃ ከ57 ዓመታት በኋላ በሸራተን ሆቴል ጥር 05/2014 ዓ.ም በዲጂታል መልኩ ተቀይሮ በርካቶች አይተውታል።

መቼቱን በአዲስ አበባ፣ ቆቃ፣ አሥመራ ያደረገው ሒሩት አባቷ ማነው? ታሪኩ የሚጀምረው በናዝሬት [አዳማ] ከተማ ውስጥ ነው።

የባላባት (ባለጸጋ) ልጅ የሆነችው ሒሩት በአንድ አጋጣሚ ናዝሬት ውስጥ ባለ ማዘጋጃ ትያትር ቤት ከቤተሰቦቿ ጋር ሆና ሙዚቃዊ ትያትር ልትመለከት በምትሄድበት ወቅት ጉግሳ ከሚባል ዘፋኝ ጋር ትተዋወቃለች።

ጉግሳና ሒሩት በፍቅር ትንሽ ወቅት እንዳሳለፉ ጉግሳ ታሰረ፣ በወቅቱም ሒሩት አርግዛ ነበር።

በ1950ዎቹ ከጋብቻ ውጪ ማርገዝ እንደ ከፍተኛ ነውር በሚታይባት ኢትዮጵያ ለሒሩት የታያት አማራጭ ጓዟን ጠቅልላ ወደ አዲስ አበባ፣ መርካቶ ማቅናት ነበር።

በአዲስ አበባም ቡና ቤት ተቀጥራ በወሲብ ንግድ ተሰማርታ የምታየውን ውጣ ውረድ 57 ዓመታትን ያስቆጠረው ፊልም ያስቃኛል።

የምረቃው ወቅት ነሐሴ 21/1957 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትያትር ቤት (ብሔራዊ ትያትር ቤት) ከአመሻሹ ሲሆን፣ በወቅቱም አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ አልጋ ወራሽ መርዕድ ወሰን፣ የንጉሣውያን ቤተሰቦችና ሚኒስትሮችም ተገኝተው እንደነበር በፊልሙ ላይ ጥናት የሰራውና የአላቲኖስ ፊልም ሰሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ምኒልክ መርዕድ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ፊልሙ በተመረቀበት ወቅት የፊልሙ ፀሐፊ ኢላላ ኢብሳ ባደረጉት ንግግር አፄ ኃይለሥላሴ በመጀመሪያው ተንቀሳቃሽ ፊልም ምረቃ ላይ በመገኘታቸው ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

"የፊልም ራ ዋናዉ ተግባሩም ከፊት መስታት ጋር ሊመሳሰል ይችላልበፊት መስታት አማካይነት አንድ ሰ ወይም አንድ ሕዝብ ሞራሉን መንፈሱንና ን በጠቅላላ አኗኗሩን ተመልክቶና ተመራምሮ ሥህተቱን በማረም ኑሮዉን ለማቃናት ይችላልስህተቱን ብቻ ሳይሆን የራሱን ጥበብና ሙያ በመመልከት ሊደሰትና ጠንካራ ሞራል ሊያገኝ ይችላልበፊልም አማካይነት ሕዝቡን በማስተማር በሚጠቅመ መንገድ ለመምራትና መንፈሱን ማጠናከር ይችላል"ማለታቸው በምኒልክ ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ ሰፍሯል።

የሂሩት አባትዋ ማነው ውልደት?

የልብ ወለድ ፊልሞች በአዲስ አበባ በ50ዎቹና 60ዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ በመዝናኛነት የሚታዩበት ወቅት ነበር።

በወቅቱ የነበሩ ዓለም አቀፍ ፊልም አከፋፋዮች የአሜሪካ፣ የጣልያን፣ የአረብ፣ የፈረንሳይና እና የሕንድ ፊልሞችን ለኢትዮጵያ ሲኒማ ቤቶች ማቅረብ እንደጀመሩም በተባባሪ ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ Ethiopian Cinema: The Socio-economic and Political Impacts of Imperial Era on the Development of Screen Media የሚለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው ያስረዳል።

በፊልሙ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስመ ጥር ከሆነው ከዋርነር ብራዘርስ ሰበን አርትስ እንዲሁም 20 ሴንቸሪ ፎክስ በአዲስ አበባ ከነበሩት አምባሳደር፣ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቲያትር፣ አድዋ፣ ድራይቭ ኢን ቲያትር እና ሲኒማ ራስ ሲኒማ ቤቶች ጋር ፊልሞችን ለማቅረብ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ፊልሞቹ ለአገሪቱ ባህል ይመጥናሉ ወይ የሚለውን በሚገምግመው አካል ይሁንታ ካገኙ በኋላ ለዕይታ የሚቀርቡ ሲሆን፣ በወቅቱም ከፍተኛ ዝናን ካተረፉት መካከል የሕንዱ ማዘር ኢንዲያ፣ የሆሊውዶቹ ካዛ ብላንካና ታርዛን ይጠቀሳሉ።

የሆሊውድ ፊልሞች በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት እንደነበራቸው በሚገልጸው የአቦነህ ፅሁፍ አንቶኒ ኩዊን፣ ቻርሊ ቻፕሊን፣ ክሊንት ኢስትውድ፣ ፍራንክ ሴናትራን የመሳሰሉ ተዋንያንም በዚያን ወቅት በነበረው ወጣት አለባበስ፣ አነጋገር፣ ሙዚቃ፣ የህይወት ዘዬ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ማሳደራቸውም ይጠቀሳል።

በሲኒማ ቤቶችና ትያትር ሄደው ማየት ለማይችሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወጥ ፊልሞችን እንዲሁም ተከታታይ ፊልሞችን ማሳየት መጀመሩ በከተሜው ዘንድ ተደራሽነቱን ከፍ አድርጎትም ነበር።

በወቅቱ የነበረው የሲኒማ ባህል መዳበር የኢትዮጵያውያንን ትኩረት ስቦ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ልብ ወለድ ተንቀሳቃሽ ፊልም ለመሰራት እንዲሁም የፊልም ፕሮዳክሽን ኩባንያ ለመመስረት ምክንያት ሆነ።

ሒሩት አባቷ ማነውን? የጻፉት ኢላላ ኢብሳ በሙያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እንደሆኑ ምኒልክ ይናገራል። ፊልሙን ዳይሬክት ያደረጉት ደግሞ ግሪካዊው ላምብሮስ ዩካሪስ ናቸው።

በኢላላ ኢብሳና በላምብሮስ ዩካሪስ አሰባሳቢነት 14 አባላት ያሉት የሃገር ፊልምና ማስታወቂያ ማኅበር የተሰኘ አንድ ትልቅ ኩባንያ ያቋቋሙ ሲሆን ኢላላ ኢብሳም ሥራ አስኪያጅ ሆኑ።

ኩባንያው በመጀመሪያ ሊሰራ አቅዶ የነበረው በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትር መኮንን እንዳልካቸው የተጻፈው 'ሳልሳዊ ዳዊት' የተሰኘ ፊልም ሲሆን ለተወሰኑ ወራትም ሲለማመዱ ቢቆዩም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሥራው ቀጥ ማለቱን ከአቦነህ አሻግሬ ፅሁፍ መረዳት ይቻላል።

የሒሩት አባቷ ማነው የቴክኒክ ባለሙያዎች በሙሉ አውሮፓውያን ነበሩ። የአርትዖቱም ሆነ ፊልሙን የማጠብ ሥራ የተሰራው ጣልያን በሚገኝ የፊልም ላብራቶሪ ሲሆን በ25 ቅጅዎችም ነበር የተዘጋጀው።

ፊልሙ ምን ያህል እንደፈጀ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም ምኒልክ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የወጣ ፅሁፍን ዋቢ በማድረግ የሃገር ፊልምና ማስታወቂያ ኩባንያ 200 ሺህ ብር ከልማት ባንክ ለፊልሙ መስሪያ ብሎ ብድር እንደወሰደ ይናገራል። በአቦነህ ፅሁፍ ላይ ደግሞ ፊልሙ 140 ሺህ ብር (በወቅቱ በነበረው ምንዛሪ 70 ሺህ ዶላር) ፈጅቷል።

ስክሪን ሾት

የፎቶው ባለመብት, Hirut Abatwa manew film

ፊልሙ በዘመኑ እንዴት ታ?

ሒሩት አባቷ ማን ነው በከተሜው በተለይም ጥብብ መድረስ በቻለበት በልሂቁ ዘንድ እንዴት ታየ የሚለውን ለማወቅ የወቅቱን ፖለቲካዊ. ማኅበራዊና የዓለም አቀፉን ሁኔታን መረዳት መልካም ነው።

1950ዎቹና 60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መፋፋም የታየበት፣ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት የወጡበት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት፣ ባህልና ጥበብ በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋበት፣ እንዲሁም በውጭ አገራት የተማሩ ወደ አገራቸው የተመለሱበት ዘመን ነበር።

የዘመናዊነት ፅንሰ ሃሳብ በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋበትና ኢትዮጵያን የማዘመን እቅዶች፣ የአገሪቱ እንዲሁም የየምጣኔ ሀብት ግንባታ እንዴት ይካሄድ በሚል በእነ መነን፣ አዲስ ሪፖርተር፣ አዲስ ሪቪው፣ አዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይጻፉ የነበረ ወቅት ነው።

በሥነ ፅሁፉ፣ በትያትር፣ በፊልሙ፣ በሙዚቃም ሆነ ሥነ-ጥበቡን ይመሩ የነበሩት የዘመኑ አቅኝዎች ዘመናዊነትን በኢትዮጵያ ለማስፈን ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩት በርካታዎቹ በውጭ አገራት ተምረው መምጣታቸውን ታሪክ ያስረዳል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያን ከድህነት ማላቀቅም ሆነ ዘመናዊነትን ማምጣት ዋነኛ አላማቸው ቢሆንም፣ እንደ ገዢ ኃሳብ የሚታየውን የምዕራባውያንን ጫና መቋቋምም ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑንም በጥበብ ሥራዎቻቸው አንጸባርቀዋል። በዚያን ወቅትም ነበረ ሒሩት አባቷ ማነው የተመረቀው።

አቦነህ አሻግሬ የመጀመሪያው ባለ 35 ሚሊሜትር ባለቀለም ፊልም ጉማ ዳይሬክተር ፓፓቲከስን ዋቢ አድርጎ እንዳሰፈረው አፄ ኃይለሥላሴ ፊልሙን አቋርጠው ወጥተዋል።

"ኢትዮጵያ ብዙ ቁም ነገር ያለው ታሪክ እያላት እንዴት የሴተኛ አዳሪ [በወሲብ ንግድ የምትተዳደር] ታሪክ ይሰራል" ብለው አስተያየታቸውን መስጠታቸውም በፅሁፉ ሰፍሯል።

ይህም ሆኖ አፄ ኃይለሥላሴ የፊልሙ ተዋናይ የሆነችውን አስካለ አመነሸዋን በቤተ መንግሥታቸው ተቀብለው ላሳየችው ምርጥ የትወና ብቃት የገንዘብና የወርቅ ሃብል አበርክተውላታል።

ፊልሙ መውጣቱን ተከትሎም በፊልም ሐያሲው ብርሃኑ ዘሪሁንና በፀሐፊው ኢላላ ኢብሳ መካከልም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ጠንከር ያሉ ምልልሶች ነበሩ።

ምኒልክ የአዲስ ዘመን የ1957 ዓ.ም የነሐሴ ፅሁፍን ባካተተበት የጥናት ሥራው ብርሃኑ ፊልሙ አዲስና ወጥ ታሪክ ይዞ እንዳልመጣና ለተመልካቹ የሚሰጠው መልዕክትና ጭብጥ ግልፅነት የጎደለው ሲሉ ይከራከራሉ።

"የታሪኩ ጠቅላላ መልዕክት ግልጥ አይደለም። ታሪኩ፤ የሚሰለች ባይመስልም ያው የተለመደው ነው። ልጅቷ በድንገተኛ ፍቅር ተታላ ክብርናዋን ታስረክብና፤ ታረግዛለች። ወደ ጥንታዊው ሙያ ወደ ሽርሙጥና [ወሲብ ንግድ] ትመለሳለች። የፊልሙ ግማሽ ያህል /በይበልጥ/ የውቤ በርሐ ጭፈራና ግርግር ነው" በማለት ተስፋዬ ገሰሰ የሺ፣ ጌታቸው ደባልቄ፣ ወንደላጤ፣ እናኑ አጎናፍር፣ በሴተኛ አዳሪ፣ ጳውሎስ ኞኞ በሴቶች አምባ የወሲብን ንግድ አስመልክቶ የጻፉት የተሻለ ነው በማለት ይተቻሉ።

ሒሩት ከመጠጥ አሻሻጭነት የራሷን መጠጥ ቤት መክፈቷ እንዲሁም 'ከዚህ ህይወት መውጣት አለብኝ' የምትለው ንግግር ከአንገት በላይ መሆኑ፣ ሀብት ንብረት ማፍራቷን በመጥቀስም "በአቋራጭ ለማደግ በርካታ ሴቶችን የሚያስጎመጅም ነው" ሲሉ ይተቹታል።

በዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት በወቅቱ የነበሩ ፀሐፊዎችም ሆኑ የጥበብ ባለሙያዎች ጭቆናዎችን ቢረዱም የሴት ሚናንም በተመለከተ ውስን ዕይታ እንደነበራቸው በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ተንታኞች ያስረዳሉ።

በርካቶቹ በተማሩባቸው አገራት የሴቶች የመብት እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ሁኔታ ያንሰራራበት ቢሆንም ፅሁፋቸው ይህንን እንደማያንጸባርቅ ዶክተር ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ Gender and Representation in Ethiopian Art and Media በሚልም ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ ያስረዳሉ።

በወቅቱ ይጻፉ ከነበሩ መካከልም ሴቶች ቢሮ ሥራ ላይ ጥቅም ይሰጣሉ ወይ፣ አለባበሳቸው ላይ የሞራል ጥያቄ የሚነሳበት፣ ሚናቸውን በቤት አያያዝ፣ ባልና እጮኛን በማክበር፣ ቤተሰብ አስተዳደር፣ ንፅህና አጠባበቅ ላይ የተወሰነ ነበር።

የብርሃኑ ዘሪሁንን ፅሁፍ በምናይበት ወቅት "ፊልሙ ሴቶችን የሚያስጎመጅ ነው" ማለታቸው ሴቶች እራሳቸው መወሰንና መወከል የማይችሉ እንደ ህፃናት የሚመከሩበት፣ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው እንዲሁም የሞራልም ሆነ የባህል ጥያቄዎች ማዕከል ከመሆን ጋር ተያይዞም ሴቶች በፊልሙ ተነሳሳተው ወደዚህ ሙያ ይገባሉ የሚለውም አስተያየት ከዚህ የመነጨ ይመስላል።

ኢላላ ኢብሳ በበኩላቸው በሰጡት መልስ የታሪኩ መልዕክት ግልፅ አይደለም፣ ፊልሙ የወሲብ ንግድን ሙያን ያደፋፍራል፣ ሒሩት ስለ ወሲብ ሥራ ያላት ጥላቻና አስተያየት ከአንገት በላይ ነው፣ የሒሩት እድል ብዙዎችን ያስጎመጃል መባሉን በተመለከተ ሲሞግቱ እንዲህ ፅፈዋል።

"የታሪኩ መልዕክት ሳያስቡ መስራትን፣ ድንቁርና ምን ያህል እንደሚጎዳ፣ በሴተኛ አዳሪነት የተገኘ ገንዘብ እንደማያስደስትና ክብርን እንደማያጎናፅፍ፣ መንፈስን እንደማያረካ፣ አካላትን የማያዝናና፣ ውርደት የማይለየዉ መሆኑን ማሳየት ነው። ይኸውም ሒሩት ሴተኛ አዳሪ በመሆኗ ብቻ የምትወደው ወዳጅዋ ከእሷ ጋር አደባባይ ለመታየት ማመንታቱን እያየች ስትሰቀቅ፤ ውበትና ሀብቷ በሰካራሞች እጅ ከመዋረድ ሳያድናት ሲቀር፤ በእኛ አስተያየት ይህ ከስድ ስድብና አነጋገር ይልቅ በዚህ ሙያ ላይ የሚገኙትን ሰዎች ቅስም ይሰብራል። ሰው ሠርቶ ማግኘቱ በደስታና በክብር ለመኖር ነው። ክብርና ደስታን የማያስከትል ሀብት ወይም ሥራ ማን ይፈልገዋል?''

ኢላላ የሒሩት ታሪክ የወሲብ ንግድን የማያበረታታና የበርካቶችንም ልብ የነካ ስለመሆኑ ማሳያቸው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትያትር የተገኘው ታዳሚ ነው ይላሉ።

"እኛ እንደሰማን ደረቅ መሐረብ ይዘዉ ከትያትር አዳራሽ የወጡ ሴቶች ጥቂቶች ናቸው። ታዲያ ይህ ዋይታ ልባቸው ቢነካ አይደለምን? ልብ የማይነካ አነጋገር ሰዉን ሊያስለቅስ አይችልም። ......ታዲያ በሰካራሞች መደብደብ፣ አብሮ አደባባይ ለመውጣት የሚያስት ወዳጅ ማጣት፣ ለጋብቻ አቻ ማጣት የሚያስጎመጅ ኑሮ ነዉን?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

በፊልሙ ላይ መሪ ገጸ ባህርይን ወክለው የተጫወቀቱት አበበች እጅጉና አለማየሁ አሰፋ በሰርጋቸው ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Menelik Mered

የምስሉ መግለጫ, በፊልሙ ላይ መሪ ገጸ ባህርይን ወክለው የተጫወቀቱት አበበች እጅጉና አለማየሁ አሰፋ በሰርጋቸው ወቅት

ጥቂት ስለ ተዋናዮቹ

ሒሩትን የወከለቻት አበበች እጅጉ የምትባል በ1950ዎቹ የሴቶች ቁንጅና ውድድር ላይ ያሸነፈች ግለሰብ እንደሆነች ምኒልክ ያስረዳል።

ጉግሳ የተባለውን ገጸ ባህርይ ወክሎ የተጫወተው አለማየሁ አሰፋ የሚባል ግለሰብ ሲሆን፣ አምስት አስርት ዓመታት ግድም በጀርመን ኑሯቸውን አድርገው በቅርብ ህይወታቸው አልፏል።

አቶ አለማየሁ በኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት በፓይለትነት እንዲሁም ወደ በሲቪል አቪዬሽን በመዛወር የበረራ ፈቃድ ሰጭ ተቋም ውስጥ አገልግለዋል።

ሁለቱ መሪ ተዋንያን በፊልሙ ተዋውቀው ለትዳር እንደበቁም ምኒልክ መነን መፅሄት ላይ የጋብቻ ባህል እየተቀየረ ይሆን? በሚል ርዕስ በወጣ ፅሁፍ ላይ ሒሩት አባትዋ ማነው ላይ ያሉት ተዋንያን ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ትዳር የሚመርጡበትን ሁኔታ ገሸሽ አድርገው ራሳቸው ተመራርጠው መጋባታቸው በ1958 ዓ.ም በወጣ ፅሁፍ ላይ ሰፍሯል።

አበበች እጅጉ ሒሩት አባትዋ ማነው በ1985 ዓ.ም በታየበት ወቅት ከጀርመን አገር መጥታ ፊልሙን በአዲስ አበባ ተመልክታለች።

በሙዚቃውም በአውሮፓውያኑ 1956 የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትያትር የሙዚቃ ዳይሬክተር የነበሩት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መዝሙርን ያዘጋጁት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ከፍተኛ ስፍራ ያላቸው አርመናዊው ነርሲስ ናልባንድያን መሳተፋቸውንም ምኒልክ ባደረገው ጥናት አግኝቷል።

ከነርሲስ ናልባንድያን በተጨማሪ ሰላም ለኢትዮጵያ፣ ስፖርት ለጤንነት በሚባሉ ዘፈኖቹ የሚታወቀውና በጣልያን አገርም በሙዚቃው ስሙን መትከል የቻለው የተስፋዬ ገብሬንም ሙዚቃዎች ዋናው ገጸ ባህርይ ጉግሳ ሲጫወታቸው በፊልሙ ላይ ይደመጣል።

ፊልሙ ለአራት ዓመታት ያህል ከታየ በኋላ ኩባንያው ፊልሙን ለመስራት የወሰደውን ገንዘብ መክፈል ባለመቻሉም በዕዳ ተይዞ ለረጅም ዘመናት ቆይቷል።

ልማት ባንክ ይህንን የመጀመሪያ ተንቀሳቃሽ ልብወለድ ፊልም ለሕዝብ አገልግሎት ቢውል ታሪካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው በሚልም ዕዳውን ሰርዞ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በ2006 በስጦታ አበርክቷል።

ፀሐፊው ኢላላ ኢብሳ እንደ አድዋ፣ ማይጨው ታሪካዊ ጦርነቶችን በፊልም የመስራት እቅድ ነበራቸው ግን ሊያሳኩት አልቻሉም።

ምኒልክ ባደረገው ጥናት መሰረት ኩባንያው በ1961 ዓ.ም የንግሥተ ሳባን ጉዞን ለመስራት ወጋየሁ ንጋቱና ደበበ እሸቱ ትምህርታቸውን ከሚከታተሉበት ሃንጋሪ ዩኒቨርስቲ መጥተው ነበር። ሆኖም ጥቂት ጥረት ከተደረገ በኋላ እንደታሰበው አልሄደም።

ደርግ ሥልጣን ላይ መውጣቱን ተከትሎ የሃገር ፊልምና ማስታወቂያ ማኅበርም ፈረሰ።

በርካቶች በንባብና በጥናት የሚያውቁት ፊልም በቅርቡ በሸራተን የመታየት ዕድል ያገኘ ሲሆን ዲጂታል ኮፒ ሆኖ ከመምጣቱም ጋር የተወሰነ የጥራት መጓደል መታየቱን ምኒልክ ያስረዳል።

ምኒልክ ይህንንም ሲገልፅ ወደ ዲጂታል ሲለወጥ አብዛኛውን ጊዜ ውጭ አገር የሚገኙ ላብራቶሪዎችን መጠቀም ነው። በአሁኑ ወቅት በዲጂታል ኮፒ ያለውን የሒሩት አባቷ ማነው ፊልም ጥራት ዝቅ ማለትን አስመልክቶ ለአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ያላቸውን ቅሬታ የገለጹላቸው ሲሆን፣ ተገቢውንም ማስተካከያ እንደሚያደርጉ ምኒልክ ይተማመናል።

ፊልሙን በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች፣ ከአገር ውጭም በግሪክ እንዲሁም በአሜሪካ የማሳየት እቅድም አለ ይላል ምኒልክ።

የሒሩት አባቷ ማነው ፓስተር

የፎቶው ባለመብት, Menelik Mered

የሲኒማ ታሪክ አጀማመር ጥቂቱ

ኢትዮጵያ የሲኒማ ቴክኖሎጂን በመቀበል ፈር ቀዳጅ ከሆኑ አገራት አንዷ ናት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሲኒማ ፈጣሪ በሚባሉት በሉዊስ ሉሚየር ወንድማማቾች አማካኝነት በፈረንሳይ በአውሮፓውያኑ 1895 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲኒማ ከታየ ከሦስት ዓመታት በኋላም ነው ሲኒማ ኢትዮጵያ ውስጥ የተዋወቀው።

የ1896ቱን የአድዋን ድል ተከትሎ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያና የጀርመን ከምኒልክ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በበለጠ ለማጠናከር ፉክክር ላይ ነበሩ። በርካታ የውጭ አገርም ዜጎችም በግልም ሆነ በባለሥልጣን ደረጃ መጉረፍ እንደጀመሩ የታሪክ ጸሐፊያን ያስረዳሉ።

በወቅቱም በኢትዮጵያ ይኖር የነበረ ስቴቭኒን የተባለ ግለሰብ 'Al tempo di Menelik' በሚል በጻፈው የእጅ ማስታወሻ የመጀመሪያው ፊልም ሚያዝያ 01/1889 አንድ ግሪካዊ ባመወጣው ፕሪጀክተር ነበር የታየው።

የተመረጠውም ፊልም የእየሱስ ክርስቶስ ታሪክ ሲሆን ኢየሱስ በባሕር ላይ ሲጓዝም መኳንንቱና ቀሳውስቱ ተነስተው እንደሰገዱም አቦነህ በፅሁፋቸው አስፍረዋል።

እንዲህ አይነት እውቅና በንጉሡ ከተሰጠ በኋላ የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት በአዲስ አበባ ከአልጄሪያ በመጣ በአንድ ፈረንሳያዊ አማካኝነት በ1898 ተጀመረ። የሲኒማ ክፍሉም ከ'ሆቴል ደ ፍራንስ' ጋር የተያያዘ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1909 ሲኒማን የጀመሩት ሉሚየር ብራዘርስ የሰጡትን ካሜራ ይዞ ቻርለስ ማርቴል የተባለ ፈረንሳያዊ የጦሩ ጄኔራል ባልቻን በሐረር፣ በወቅቱ ታመው አልጋ ላይ የነበሩትን አፄ ምኒልክን፣ ዳንሰኞችንና አገልጋዮቻቸውን ቀርፆ 'L'Abyssinie au temps de Menelik' (አቢሲኒያ በምኒልክ ወቅት) በሚል የ24 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም መስራቱን ከአቦነህ የጥናት ፅሁፍ መረዳት ይቻላል።

ይህ ፊልምም በኢትዮጵያ መሬት ላይ የተቀረጸው የመጀመሪያ ፊልም መሆኑንም አቦነህ አስፍሯል። ከዚያም በኋላ በፈረንሳይ ፊልም ባለሙያዎች የተለያዩ ዘጋቢ ፊልሞች ተሰርተዋል።

ኢትዮጵያዊ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘጋቢ ፊልም የሰራው በአውሮፓውያኑ 1920 ነው። ተድላ ተሰማ የሚባል የመጀመሪያው ሲኒማቶግራፈር በ16 ሚሊሜትር ጥቁር ነጭ ፊልም የንግሥት ዘውዲቱን የንግሥና ታሪክ በፊልም ሰርቷል። ፊልሙ ድምፅ የሌለው እንደነበር አቦነህ መዝግቧል።

ጣልያን ኢትዮጵያን መቆጣጠሩን ተከትሎ በርካታ ሲኒማዎች መሰራት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞችም ተሰርተዋል።

ምዕራባውያን ፊልም ሰሪዎች አፍሪካውያንን ተገዢ ሠራተኞች፣ አረመኔ፣ ጨካኞችና ሰው በላ አንዳንዴም ሰው ያልሆኑ ብርቅና ድንቅ አድርገው ይስሏቸው ነበር። ባህልና ታሪከ የሌላቸው በአገሬው ተወላጆች እና ሰለጠነ በተባለው ነጭ መካከል ያለውን ልዩነት በማጉላት ላይ ያተኮሩ የቅኝ ግዛት ፕሮፓጋንዳዎች ነበሩ።

'አንደር ዘ ሳውዘርን ክሮስ' በ1930ዎቹ የተሰራ የጣልያን ድራማ ነው። ጣልያን "በአቢሲኒያ" ያገኘችውን ድል እንደሚያሳይ የፊልሙ ፅሁፍ ያስረዳል።

ጣልያን ኢትዮጵያን በተቆጣጠረችበት ወቅት የጣልያን የአፍሪካ ኢምፓየር መቼታቸውን አድርገው በፋሺስት ዘመን ከተዘጋጁት ስምንት ተከታታይ ፊልሞች ውስጥ አንዱ እንደነበር ታሪክ ይዳስሳል።

ፊልሙ የፋሺስት ፖሊሲን ለመደገፍ የተነደፈ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሲሆን በተለያዩ ዘሮች መካከል ስላለው የፍቅር ግንኙነትም ያሳያል።

በቱስካኒ በሚገኘው ቲሬኒያ ስቱዲዮ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ግልፅ ያለ ቦታ ባይጠቅስም በኦሮሚያ ውስጥ እንደተቀረጸ ተጠቅሷል።