“የኤርትራ ወታደሮች አጎቴን ገደሉት” - የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, EPA

የመንግሥታቱ ድርጅት የኅብረተሰብ ጤና ተቋምን የሚመሩት ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም የኤርትራ ወታደሮች አጎታቸውን በትግራይ ክልል በምትገኝ መንደር እንደገደሉባቸው ተናገሩ።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ከሳቸው አጎት በተጨማሪ ከ50 በላይ የመንደሯ ነዋሪዎች በዘፈቀደ በኤርትራ ወታደሮች ተገድለዋል ብለዋል።

“በጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበርኩም” ያሉት የትግራይ ተወላጁ ዶክተር ቴድሮስ በሐዘን በተሰበረ ሁኔታ ነበር።

ኤርትራ በቀረበባት ክስ ላይ እስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጠችም።

ዶክተር ቴድሮስ በጄኔቫ ረቡዕ ዕለት በነበረው የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ወረርሽን በተመለከተ ስላሉ አዳዲስ መረጃዎች መግለጫ በሰጡበትም ዕለት ነው “ቅዳሜ ዕለት አጎቴ በኤርትር ጦር መገደሉን ተረዳሁኝ” ሲሉ መርዶውን እንዴት እንደሰሙ የተናገሩት።

“እናቴን አነጋገርኳት። የቤተሰባቸው የመጨረሻ ታናሽ ስለነበር ልቧ በሐዘን ተሰብሯል። በዕድሜም እኩዮች ነበርን” በማለት የ57 ዓመቱ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።

ጥቃቱ ስለተፈጸመበት ጊዜም ሆነ የመንደሯን ስም በተመለከተ ዶ/ር ቴድሮስ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ጥቅምት መጨረሻ የተደረሰው ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ይጸናል የሚል ተስፋን ያሳደሩት ዶክተር ቴድሮስ “ይህ እብደት ይቆማል” የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በተወሰነ መልኩ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሆነ የሚገልጹት የትግራይ አመራሮች፣ የኤርትራ መንግሥት ሂደቱን እያደናቀፈ ነው በማለት ሲከሱም ይሰማሉ።

የኤርትራ ጦር በተቆጣጠረባቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ግድያዎችን እና ዝርፊያዎችንም እየፈጸሙ እንደሆነ በተለያዩ መግለጫዎቻቸው አስታውቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እና በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት 65 በመቶ የሚሆኑት የትግራይ ኃይሎች ከውጊያ ቀጠናዎች እንዲወጡ መደረጋቸውን የትግራይ ኃይሎች አሳውቀው ነበር።

የትግራይን ኃይሎችን ከውጊያ ቀጠና የማራቅ ሂደቱ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ለማጠናቀቅ በክልሉ ውስጥ ካሉ የውጭ እና የውስጥ ኃይሎች “ስጋት” ጋር የተያያዘ እንደሆነም የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ መናገራቸው ይታወሳል።

ነገር ግን በጦርነቱ ተሳታፊ የሆነችው ኤርትራም ሆነ አጎራባች የአማራ ክልል የስምምነቱ አካል አልነበሩም።

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሣሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በዚህ የአፈጻጸም ሰነድ ላይ ከትግራይ ክልል ይወጣሉ የተባሉት የውጭ አገር እና የፌደራሉ መከላከያ ያልሆኑ የተባሉት የክልል ኃይሎች በስም አልተጠቀሱም።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው ግጭት የማቆም ስምምነት ኤርትራን በቀጥታ ያልጠቀሳት ሲሆን፣ ምዕራባውያን አገራትና ተቋማት ኤርትራ ጦሯን ከትግራይ በተደጋጋጋሚ እንድታስወጣም ሲጠይቁ ይሰማል።

በአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል በፍጥነት መውጣት ላይ ከውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ጋር ተነጋግረዋል።

የፌደራል መንግሥት እነዚህን ኃይሎች የመውጣታቸውን ጉዳይ በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

“የውጭና የውስጥ ኃይሎችን ከትግራይ የማስወጣት እንዲሁም በሕዝብ ላይ እየፈጸሙ ያሉትን መቆጣጠርም ኃላፊነቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ነው” ያሉት ጄኔራል ታደሰ መከላከያ ኃይሎቹን የማስወጣት ተግባር ፈጥኖ ይጀምራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል። 

ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለቀጠፈውና በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ የማይነገር ሰቆቃ ላደረሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ባለፈው ወር መደረሱ ይታወቃል።

በዚህም የሰላም ስምምነት መሠረት ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው መሠረታዊ አገልግሎት እንዲመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን በመፍታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ ነው።