የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ በሚፈቱበት ዕቅድ ላይ የጋራ ኮሚቴ ሽረ ላይ እየመከረ ነው

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ በሚፈቱበት ዝርዝር ዕቅድ ላይ የጋራ ኮሚቴ ትግራይ ውስጥ በሽረ ከተማ እየመከረ መሆኑ ተገለጸ።

የባለሙያዎቹ የጋራ ኮሚቴ ከፌደራል መንግሥቱ እና ከትግራይ ኃይሎች የተውጣጣ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 22/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እና በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የባለሙያዎቹ የጋራ ኮሚቴ በትጥቅ አፈታት ዙሪያ ዝርዝር ዕቅድ የማውጣቱን ሥራ ትናንት ረቡዕ ኅዳር 21/2015 ዓ.ም. ሽረ ላይ መጀመሩም ተገልጿል።

ኮሚቴው የሚያወጣው ዝርዝር ዕቅድ የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ካምፕ የማስገባት እና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመልስ እንደሆነም መግለጫው አክሏል።

በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ሆኖም በዚህ መግለጫ የውጭ አገር ተብሎ የተጠቀሰው ኃይልም ሆነ የክልል ኃይላት የተባሉት ከትግራይ መውጣታቸውን በተመለከተ የተባለ ነገር የለም።

ዝርዝር ዕቅዱን የማውጣት ተግባር በቴክኒክ ጉዳዮች ምክንያት ዘግይቷል ያለው መግለጫው፣ እነዚህ የቴክኒክ ጉዳዮች ያላቸውን አልጠቀሰም።

ከሰሞኑ የፌደራሉ መንግሥት መከላከያ እና የትግራይ ኃይል ተወካዮች በሽረ ሊገናኙ መሆኑን አምባሳደር ወንድሙ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የሁለቱ ጦር ሠራዊት ተወካዮች በአንዳንድ ቴክኒካል ጉዳዮች እንደሚወያዩ ለትግራይ ቴሌቪዥን የተናገሩት አምባሳደሩ ዝርዝር መረጃዎችን አልሰጡም።

በሁለቱ ሠራዊት መካከል ተስፋ የሚሰጥ ግንኙነት ነው እየተፈጠረ ያለው ያሉት አምባሳደሩ “ቀረ ማለት በማይቻል ደረጃ ሠራዊቱ ተግባብቶ እየሰራ ነው” ሲሉም በክልሉ ቴሌቪዥንም ተደምጠዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለቱ የጦር አዛዦች ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የተደረሰውን ጦርነት በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ተከትሎ በናይሮቢ ተገናኝተው በአፈጻጸሙ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ለሳምንት ያህል የቆየው ዝግ ውይይትም የስምምነቱ የትግበራ ሰነድ በመፈረም ተጠናቋል።

ይህ የትግበራ ሰነድ ስድስት ጉዳዮችን የጠቀሰ ሲሆን፤ እነዚህም ግጭቶችን በዘላቂነት ማቆም፣ ትጥቅ ማስፈታት፣ ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት፣ ሰላማዊ ነዋሪዎችን መጠበቅ፣ ሚዲያን በኃላፊነት መጠቀም እና የስምምነቱን አፈጻጸም ክትትል እና ማረጋገጥ የሚሉ ይገኙበታል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በጥሩ መልኩ እየሄደ ነው ያሉት አምባሳደር ወንድሙ፣ ሆኖም ሰብዓዊ እርዳታ በተፈለገው መጠን እየገባ እንዳልሆነና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዳልተመለሱ ጠቁመዋል።

ለዚህ የሰላም ስምምነት ዋነኛ ችግር ብለው የጠቀሱት የሰላም ስምምነቱን ማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች ብለው የጠሯቸውን ነው። በዚህም በዋነኝነትም የኤርትራ መንግሥት ነው ብለዋል።

“የኤርትራ መንግሥት መነካካት ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ እንዲጫር የሚያስችል ወንጀል እየሰራ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሕዝብ እያለቀ ነው። ከባለፈው ጥሰት በተጠናከረ መልኩ የአንድን ቀበሌ ሕዝብ ጠራርጎ ማስወጣት፣ መፍጀት። ንብረት መውደም ቀጥሏል” ብለዋል ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ።

ባለፈው ሳምንትም በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦቦሳንጆ ለተመራው የአፍሪካ ኅብረት ልዑካን መቀለ በነበራቸው ጉብኝት ይህንኑም ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በበኩላቸው፣ በፕሪቶሪያም ይሁን በናይሮቢ በተደረጉ ውይይቶች የውጭ አገር ወታደሮችን ጨምሮ ሌሎችንም ጉዳዮች መወያየታቸውን ጠቅሰው “የትኛውም አገር የውጭ አገር በመሬቱ ላይ መኖሩን መቀበል የለበትም” ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው ግጭት የማቆም ስምምነት ኤርትራን በቀጥታ ያልጠቀሳት ሲሆን፣ ምዕራባውያን አገራትና ተቋማት ኤርትራ ጦሯን ከትግራይ በተደጋጋጋሚ እንድታስወጣም ሲጠይቁ ይሰማል።

ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ የማታስወጣ ከሆነ ማዕቀብ ሊጣልባት እንደሚችል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ መናገራቸው ይታወሳል።

የፕሪቶሪያውን ግጭት በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነትን ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀለን የጎበኘው የልዑካኑ ቡድን፣ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ እና የኅብረቱ የፖለቲካ፣ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዮን ያካተተ ነበር።

የኅብረቱ ተወካዮች በአዲስ አበባ ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን አምባሳደር ወንድሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሆኖም ሰብዓዊ እርዳታ በተፈለገው መጠን እየገባ እንዳልሆነና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዳልተመለሱ ጠቅሰው በቅርቡም እንደሚስተካከል ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት የትግራይ ኃይሎች ተሰልፈውባቸው ከቆዩባቸው ግንባሮች የማስወጣት ሂደት (disengagement) በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እንደሚጀመር የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ተናግረዋል።

ከናይሮቢው የትግበራ ዝርዝር ስምምነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መግለጫ የሰጡት ጄኔራል ታደሰ የሰላም ስምምነት ለታጣቂዎቻቸው የማስረዳት ሥራዎች እየተገባደዱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ይሄንን ተከትሎ አሁን ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች መውጣት እንደሚጀምሩ አመልክተዋል።

“ስምምነት ተደርጓል፤ ከዚያ በኋላ ‘ዲስኢንጌጅ’ ማድረግ፣ ሠራዊቱ ተጓጉዞ ወደ ትክክለኛው ቦታ እንዲገባ የማድረግ ሥራዎች በሁለት እና ሦስት ቀናት ውስጥ ይጀመራል” ብለዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለቀጠፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ባለፈው ወር መደረሱ ይታወቃል።

በዚህም የሰላም ስምምነት መሰረት ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው መሰረታዊ አገልግሎት እንዲመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን በመፍታት ህገ መንግሥታዊ ስርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ ነው።