የናይሮቢው የትግበራ ዝርዝር ሰነድ ምን አካቷል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነትን ተከትሎ በናይሮቢ ለቀናት የተካሄደው ውይይት ኅዳር 03/2015 ዓ.ም. በፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ አዛዦች መካከል የስምምነቱ የትግበራ ሰነድ በመፈረም ተጠናቋል።
የፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የተደረሰውን ጦርነት በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ላይ ተወያይተው የተስማሙበትም ሰነድም ይፋ ሆኗል።
ውይይቱ በናይሮቢ፣ ካረን ሞራን ማዕከል ከሰኞ ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በዝግ የተካሄደ ነው። ውይይቱ ለሦስት ቀናት ይቆያል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ለተጨማሪ ቀናት ተራዝሞ ቅዳሜ ኅዳር 03/2015 ዓ.ም. ተጠናቋል።
ይህ የትግበራ ሰነድ ስድስት ጉዳዮችን የጠቀሰ ሲሆን፤ እነዚህም ግጭቶችን በዘላቂነት ማቆም፣ ትጥቅ ማስፈታት፣ ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት፣ ሰላማዊ ነዋሪዎችን መጠበቅ፣ ሚዲያን በኃላፊነት መጠቀም እና የስምምነቱን አፈጻጸም ክትትል እና ማረጋገጥ የሚሉ ይገኙበታል።
ይህንንም ስምምነት አስመልክቶ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖችም ናይሮቢ ውስጥ በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ “ሁለቱም አካላት በትግራይ እና በአጎራባች ክልሎች እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሰብአዊ እርዳታን ለማመቻቸት ተስማምተዋል” ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓትን እያሸማገሉ ያሉት የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው መሰል አሰቃቂ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ አካላት ላይ “ከባድ ማዕቀብ” እንደሚጣልባቸው በዚህ ወቅት አስጠንቅቀዋል።
ነገር ግን ኡሁሩ እንዳሉት ቅድሚያ የሚሰጠው ጠመንጃን ጸጥ ማሰኘት፣ ለነዋሪዎች እርዳታ ማድረስ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመለስ ነው ብለዋል።
የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄራል ታደሰ ወረደም “ባለፉት ሁለት ዓመታት ያልተነገረ ሰቆቃ ደርሶብናል አሁንም እየተሰቃየን ነው” ብለዋል።
“ስለዚህ ዛሬ እየገባን ያለነው ቁርጠኝነት የሕዝባችን ስቃይ በቅርቡ እንደሚቆም ተስፋ በማድረግ ነው” ብለዋል።
ለመሆኑ የትግበራው ዝርዝር ሰነድ ምን ይዟል?
ግጭቶችን በዘላቂነት ማቆም
- ከማንኛውም ወታደራዊ ግጭቶች መታቀብና ማቆም
- የዚህን ስምምነት አፈጻጸም አጠቃላይ ዓላማ ለማሳካት አስፈላጊ እርምጃዎች መወሰዱን ማረጋገጥ
የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት
በፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 6 መሰረት መሰረት ትጥቅ ማስፈታት ተፈጻሚ እንደሚሆን በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።
- ከፍተኛ የሠራዊቶቹ አዛዦች ኅዳር 06/2015 ዓ.ም. ወደ መደበኛ ቦታቸው ከደረሱ በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ለሠራዊታቸው አባላት ገለጻ ያደርጋሉ።
- ገለጻ በተደረገ በአራት ቀናት ውስጥ ወታደሮች ከጦርነት ቀጠና እንዲርቁ ያደርጋሉ።
- ወታደሮች ከጦርነት ቀጣው ከራቁ በኋላ፣ የፌደራል ባለሥልጣናት በሕገ መንግሥቱ መሠረት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ የፌደራል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ።
- የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ አገር እና የፌደራሉ መከላከያ ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከክልሉ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ ነው።
- በዚህ ሰነድ በተፈረመበት ዕለትም የቀላል መሳሪያ ትጥቅ መፍታትን በተመለከተ ዝርዝር የአፈጻጸም ዕቅድ አውጥቶ በአስራ አራት ቀናት ውስጥ ሪፖርት የሚያቀርብ የጋራ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ተጠቅሷል።
- ኮሚቴው ከእያንዳንዱ ተፋላሚ ወገኖች ሁለት አባላትን፣ እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት የክትትልና ማረጋገጫ ቡድን አንድ ተወካይንም ያቀፈ ይሆናል።
በዚህ የአፈጻጸም ሰነድ ላይ ከትግራይ ክልል ይወጣሉ የተባሉት የውጭ አገር እና የፌደራሉ መከላከያ ያልሆኑ የተባሉት የክልል ኃይሎች በስም አልተጠቀሱም።
ከኢትዮጵያ መንግሥት አጋር በመሆን በጦርነቱ እየተሳተፈች ያለችው ጎረቤት አገር ኤርትራ የድርድሩ አካል አልነበረችም።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው ግጭት የማቆም ስምምነት ኤርትራን በቀጥታ ያልጠቀሳት ሲሆን፣ ምዕራባውያን አገራትና ተቋማት ኤርትራ ጦሯን ከትግራይ በተደጋጋጋሚ እንድታስወጣም ሲጠይቁ ይሰማል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰላማዊ ነዋሪዎች ጥበቃ
በስምምነቱ አንቀጽ 4 መሠረት በሕገ መንግሥቱ መሰረት የፌደራል የፀጥታ አካላት እና የክልል የፀጥታ አካላት ሰላማዊ ዜጎችን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳላቸው ጠቅሶ በዚህ ረገድ ሁለቱ አካላት
- በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መከላከል
- የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማረጋገጥ
- የሲቪል ተቋማትን እና የመሠረተ ልማትን ደኅንነት ማረጋገጥ
- ሴቶችን እና ህጻናትን ጨምሮ የተጋላጭ ቡድኖችን ደኅንነት ማረጋገጥ
- ሰላማዊ ዜጎችን ከፀጥታ ኃይሎች ከሚደርስ ጥቃት መከላከል
- ተፋላሚ ወገኖች ይህንን የስምምነቱን አንቀጽ አራት ከጣሱ ጠንካራ ውግዘት እና የቅጣት እርምጃም እንደሚጠብቃቸውም ያትታል።
ሰብዓዊ ረድዔትን በተመለከተ
በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 5 መሠረት ተፋላሚ ወገኖች የተስማሙባቸው
- ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ማመቻቸት
- ሁሉም የሰብዓዊ እርዳታዎች በፌደራል መንግሥት ቁጥጥር እና እንዲሁም በማሳወቅ እንዲያልፉ
- ለሰብዓዊ ረድዔት ሠራተኞች እና ድርጅቶች በጥያቄያቸው መሠረት መከላከያ የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጡ
- ሁለቱም ወገኖች የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ያለምንም እንቅፋት እንዲንቀሳቀሱ ማመቻቸት
- ሁለት የፍተሻ ጣቢያዎች ብቻ የሚኖሩ ሲሆን አንደኛው ከመነሻው ወይም ረድዔቱ ከሚጫንበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመድረሻ አካባቢዎች ላይ ይቋቋማል።
ክትትል እና ማረጋገጥ
ተፋላሚ ወገኖች በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 11 መሠረት በአፍሪካ ኅብረት በከፍተኛ ደረጃ ፓነል ከሚቋቋመው የክትትል እና ማረጋገጫ ቡድን ጋር ለመተባበር እንደተስማሙ ይጠቅሳል።
የዚህ ቡድን መግለጫ እና የማመሳከሪያ ውል ከተፋላሚ ወገኖች ጋር በመመካከር መዘጋጀት እንዳለበትም ይጠቁማል።
- ቡድኑ ይህ መግለጫ ከተፈረመ በአስር ቀናት ውስጥ ሥራውን ይጀምራል።
- ስምምነቱ ከተፈረመም በኋላ በአስር ቀናት ውስጥ በመከላከያ የደኅንነት ዋስትና ሊሰጠው እንደሚገባም በሰነዱ ላይ ተቀምጧል።
ሚዲያን በኃላፊነት መጠቀም
ሌላው በዚህ ሰነድ ላይ የተቀመጠው ተፋላሚ ወገኖች በምን መልኩ ሚዲያን መጠቀም እንዳለባቸው የሚጠቅሰው ነው።
ተፋላሚ ወገኖች በፕሮቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 12 መሠረት የሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች ገንቢ ሚና እንዲጫወቱና ይህን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ሊያረጋግጡ እንደሚገባም በግልጽ ያትታል።
ይህን ውይይት በአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ቡድን የናይጄሪያ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን አቦሳንጆ፣ የኬንያ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፣ የኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ጄኔራሎች መርተውታል።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) በዚህ ውይይት ላይ የታዛቢነት ስፍራ እንዳለውም ተገልጿል።
በስምምነቱ ላይ የታዛቢነት ድርሻ እንደነበራት የተገለጸው አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋ ማይክ ሐመር የተወከለች ሲሆን፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት እስኪተገበር ድረስ በቀጠናው እንደሚቆዩ እና ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃለ አቀባይ ኔድ ፕራይስ ከሰሞኑ ገልጸዋል።
ኔድ ፕራይስ ከሰሞኑ በስምምነቱ መሠረት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ማፋጠን እንዲሁም በትግራይና በአጎራባቾቹ የአፋር እና የአማራ ክልሎች ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ አንደኛው የናይሮቢ አጀንዳ እንደሆነ መጥቀሳቸው ይታወሳል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኅዳር 02/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሰላም ስምምነቱ በታቀደለት መንገድ እንዲፈጸም መንግሥት እየሠራ መሆኑን ገልጾ፤ ለዚህም በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ስር ባሉ አብዛኞቹ የትግራይ አካባቢዎች እርዳታ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንና መሠረታዊ አገልግሎቶች ቀስ በቀስ ሥራ እየጀመሩ ነው ብሏል።
የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው የእርዳታ ጭነቶች ወደ ጦርነት ቀጠና ለመግባት ፈቃድ እየተጠባበቁ እንዳሉ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ይጠቀማል ሲል የሚወቅስ ሲሆን፣ በተጣለው እገዳ ምክንያት 90 በመቶ የሚሆነው የትግራል ክልል ሕዝብ አደጋ ላይ ወድቋል።
የግጭት ማቆም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ ምግብም ሆነ መድኃኒት እየገባ እንዳልሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
ዶክተር ቴድሮስ በክልሉ የተቋረጡት የቴሌኮም፣ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱም ጠይቀዋል።
“ስድስት ሚሊዮን ሕዝቦች በሕይወት የሌሉ ይመስል ለሁለት ዓመታት ያህል ከዓለም ጋር እንዲቆራረጡ ተደርገዋል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የቴሌኮም፣ የመብራት እና የባንክ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መጀመር አለብን ለዚህም ጥረት እየተደረገ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ከዚህ በፊት ግን “ሕዝባችን መጀመሪያ ምግብ እና መድኃኒት ያስፈልገዋል፣ እሱንም ለማድረግ እየሞከርን ነው” ብለዋል።
“ምናልባት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ሳምንት አጋማሽ ላይ” ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲገባ ይፈቀዳል ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለጋዜጠኞች መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።












