የፌደራሉ መከላከያና የህወሓት ወታደራዊ አመራሮች የፊታችን ሰኞ በናይሮቢ እንደሚነጋገሩ ተገለጸ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን

የፎቶው ባለመብት, Ministry Of Foreign Affairs

 የፌደራሉ መከላከያና የህወሓት ወታደራዊ አመራሮች ሰኞ ጥቅምት 28፣ 2015 ዓ.ም በናይሮቢ እንደሚነጋገሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን ገለጹ።

አምባሳደር ሬድዋን ይህንን የተናገሩት በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ለውጭ ዲፕሎማቶችና ለአለም አቀፉ ማህበረሰቡ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ጥቅምት 26፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን ከስምምነቶቹ መካከል አንዳንዶቹ በአስቸኳይ መተግበር የሚጠበቅባቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል በወታደራዊ አመራሮች መካከል የንግግር መድረክ ማመቻቸት አንዱ ነው ብለዋል። 

የሁለቱወገኖች ወታደራዊ አመራሮች ከወዲሁ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን መግለፃቸውን የጠቆመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ወታደራዊ አመራሮቹ በቀጣይ ስለሚከናወኑ ሂደቶች የፊታችን ሰኞ በአካል ተገናኝተው እንደሚወያዩም በኃገርውስጥ መገናኛ ብዙኃን በተላለፈው ንግግራቸው ጠቅሰዋል።

የፌደራሉ መከላከያና የህወሓት ወታደራዊ አመራሮች በአካል ተገናኝተው ስለ ትጥቅ መፍታት እንደሚነገጋሩ የተናገሩት አማካሪው “ትጥቅ ለሚፈቱት የህወሓት ታጣቂዎች ሁኔታዎችን ማመቻቸት የሚለው” ሌላ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

አምባሳደር ሬድዋን “የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ ከፈቱ በኋላም” የትግራይ ክልል እንደ ሌሎች ክልሎች በቂ የሚባል ልዩ ኃይል እንደሚደራጅለትም አስረድተዋል።

“ህወሓትን ትጥቅ ማስፈታት ብለን የጸጥታ ኃይል በክልሉ እንደሚደራጅ ስንናገር አንዳንድ አጋሮች በዚህ ግርታ ሊገባቸው ይችላል። ክልሎች የራሳቸው የጸጥታ ኃይሎች አላቸው። የትግራይ ክልል የራሱ የጸጥታ ኃይል እንዲኖረው ያለውን መብት አንክድም” ብለዋል።

የትግራይ ክልል ፖሊስና "የተመጠነ የጸጥታ ኃይል አደረጃጀት እንደሚኖሩት" ጠቅሰው "የሚደራጀው ኃይል ተጠሪነቱ ለትግራይ ክልላዊ መንግሥት እንጂ የአንድ ፓርቲ አይሆንም" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አምባሳደሩ አስር ቀናት ስለፈጀውና በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት፣ የስምምነቱ አፈጻጸም ቀጣይ እርምጃዎችና ከአጋር አገራት ስለሚጠበቁ ሁኔታዎችም አስረድተዋል።

በዚህም የሰላም ስምምነት አፋጣኝ እርምጃ የሚፈልጉ ያሏቸውን ስምምነት የጠቀሱት አምባሳደር ሬድዋን ከሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች መካከል የውይይት መድረክ ከመክፈት በተጨማሪ ጦርነቱን በአስቸኳይና በዘላቂነት ማቆም የሚለው ቀዳሚ ነው ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪም ግጭት ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳዎችና ትርክቶችም መቆም አለባቸው ብለዋል። 

በስምምነቱላይ የህወሓት ኃይሎች “ከቀላል ጦር መሳሪያዎች” ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቃቸውን እንደሚፈቱ ቀነ ገደብ ቢያስቀምጥም ለሁለት ዓመታት ያህል ስልክ፣ ባንክ፣ መብራትና መሰረታዊ አገልግሎቶች በተነፈጉባት ትግራይ ክልል መቼ እንደሚጀምርም ሆነ ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሁም ተፈናቃዮችን በመመለሱ ሁኔታ በተመለከተ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ባለሥልጣናት ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ጦርነት ለማብቃት ቋሚ ግጭት የማስወገድ እና ትጥቅ የመፍታት ስምምነት ተፈራርመዋል።

ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ረቡዕ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም፣ የእርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማስጀመርና የአገሪቱ ድንበርና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕግ እንዲከበር የማድረግ አላማ እንዳለው ተጠቅሷል።

ለአስር ቀናት የቆየውና በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት ተወካዮች መካከል ሲካሄድ የቆየው ንግግር ማብቂያ ላይ፣ ሁለቱም ወገኖች የደረሱበትን 12 ነጥቦችን የያዘ ባለ ሁለት ገጽ ስምምነት በጋራ አቅርበዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የስምምነቱን ዝርዝር አፈጻጸምና ከሁለቱም ወገኖች ስለሚጠበቁ ግዴታዎች በዝርዝር የሚያብራራ በሁለቱም ወገኖችና በአደራዳሪዎች የተፈረመበት ሰነድ ተሰራጭቷል። 

ሆኖም በአንዳንድ ትግራይ አካባቢዎች ጦርነት መቀጠሉ እንዲሁም የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸው እየተዘገበ ይገኛል።

የህወሃት አመራር የሆኑት ፕሮፈሰር ክንደያ ገብረሕይወት ጦርነቱ መቀጠሉን አረጋግጠው “የኤርትራ ጦር አድዋ ላይ ቤት ለቤት ለቤት ፈትሸዋል፤ዝርፊያም ፈጽመዋል “ ብለዋል በትዊተር ባሰፈሩት ጽሁፋቸው።

የግጭት ማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላም በትግራይ ውጊያ መቀጠሉ እንዳሳሰባቸው የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ብራድ ሸርማን ገልጸዋል።

“የሰላም ስምምነቱ መከበር እና ሁሉም ግጭቶች መቆም አለባቸው” ያሉት የምክር ቤት አባሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሁሉን ያሳተፈ እና ፍትህ መኖር አለበት ብለዋል።

ለተፈጸሙት መጠነ ሰፊ ጥሰቶች ዘርን ማጽዳት፣ ረሃብን የጦር መሳሪያ መጠቀም፣ መደፈርና የትግራይ ዜጎች የጅምላ እስርና ለመሳሰሉት ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባም በትዊተር ገጻቸው ሰፍሯል።