በስምምነቱ መሠረት ከፌደራል መንግሥቱ እና ከህወሓት ምን ይጠበቃል? ትጥቅ መፍታቱስ እንዴት ይከናወናል?

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ባለሥልጣናት ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ጦርነት ለማብቃት ቋሚ ግጭት የማስወገድ እና ትጥቅ የመፍታት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ረቡዕ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም፣ የእርዳታ እና መሠረታዊ አገለግሎቶች ለማስጀመርና የአገሪቱ ድንበርና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕግ እንዲከበር የማድረግ አላማ አለው።
ለአስር ቀናት የቆየውና በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት ተወካዮች መካከል ሲካሄድ የቆየው ንግግር ማብቂያ ላይ፣ ሁለቱም ወገኖች የደረሱበትን 12 ነጥቦችን የያዘ ባለ ሁለት ገጽ ስምምነት በጋራ አቅርበዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የስምምነቱን ዝርዝር አፈጻጸምና ከሁለቱም ወገኖች ስለሚጠበቁ ግዴታዎች በዝርዝር የሚያብራራ በሁለቱም ወገኖችና በአደራዳሪዎች የተፈረመበት ሰነድ ተሰራጭቷል።
አሶሺየትድ ፕሬስ ለሰላም ንግግሩ ቅርበት ያላቸውን አንድ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ከደቡብ አፍሪካ እንደዘገበው የስምምነቱን አፈጻጸም በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘው ሰነድ በሁለቱም ወገኖች የተፈረመ መሆኑን አመልክቷል።
በስምምነቱ ላይ የህወሓት ኃይሎች “ከቀላል ጦር መሳሪያዎች” ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቃቸውን ይፈታሉ።
የኢትዮጵያ ፌደራል የፀጥታ ኃይሎች “በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም የፌደራሉን ተቋማትና አየር ማረፊያዎችንና አውራ ጎዳናዎችን ጨምሮ ዋነኛ መሠረተ ልማቶችን” ሙሉ ለሙሉ እንደሚቆጣጠሩ ተጠቅሷል።
ከሁለቱ ወገን ምን ይጠበቃል
ህወሓት
ህወሓት በሕገመንግሥቱ መሰረት የተቋቋሙ የፌደራል ተቋማትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የተስማማ ሲሆን፣ይህም የፌደራል መንግሥቱ የፌደራል ተቋማትን ንብረት፣ የአገሪቱን ዓለም አቀፍ ድንበርን የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ይሆናል።
ህወሓት በየትኛውም የአገሪ ቱ ክፍል ውስጥ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አማፂ ቡድኖችን ከመደገፍም ሆነ አብሮ ከመስራት ለመታቀብ ተስማምቷል።
የፌደራል መንግሥቱ የአገር መከላከያ ሠራዊትን፣ የደኅንነት አካላትን እና ሕግ አስከባሪ አካላትን ሕገመንግሥታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሲያሰማራ አክብሮ ለመንቀሳቀስ ተስማምቷል።
ህወሓት ለግጭት እና አመጽ የሚደረጉ ምልመላዎች፣ ሥልጠናዎች ወይም ዝግጅቶችን ከማድረግ ይታቀባል።
ህወሓት ያለ ፌደራል መንግሥቱ እውቅና ከማንኛውም የውጭ አካል ጋር ግንኙነት ማድረግ ያቆማል።
የኢትዮጵያ መንግሥት
የህወሓት ታጣቂዎች ላይ የሚያደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ ያቆማል።
በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ቀድሞ ወደ ነበረበት ይመልሳል።
ህወሓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ዝርዝር እንዲካተት የተደረገው ውሳኔ እንዲነሳ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።
የትግራይ አካባቢዎች የማኅበራዊ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ ሁኔታዎች ያመቻቻል፤ ተግባራዊነታቸውንም ያረጋግጣል።
በትግራይ እና ሌሎች ክልሎች በጦርነቱ ለተጎዱ ሕዝቦች እርዳታ እንዲደርስ ያመቻቻል፣ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መኖሩን ያረጋግጣል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎችን ደኅንነትና ሰላም የሚያረጋግጥ ስምሪት የሚያደርግ ይሆናል።
መከላከያ ሠራዊቱ በማንኛውም የትግራይ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ሕግ የማስከበር ሥልጣኑን ይረከባል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ሌሎች የፌደራል የፀጥታ መዋቅሮች የአገሪቱን አየር ክልል፣ አቪየሽን ደኅንነት፣ የፌደራል ተቋማትን፣ በትግራይ የሚገኙ አየር ማረፊያዎችንና ዋና ዋና መንገዶችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነትን ይረከባል።
ትጥቅ ማስፈታት
በስምምነቱ ላይ ዋነኛ ጉዳይ የሆነውን ትጥቅ ማስፈታትን በተመለከተ ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የመከላከያ ኃይል ብቻ እንዳለ ከስምምነት ደርሰዋል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሰረት የህወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ መበተን እና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ ለመቀላቀል የሚያስችል ዕቅድ ተነድፎ ተግባራዊ የሚሆንበትን ዝርዝር ይዘጋጃል።
ይህ ስምምነት በተፈረም በ24 ሰዓታት ውስጥ የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገናኝተው ይነጋገራሉ።
በአምስት ቀናት ወስጥ ደግሞ በክልሉ ካለው ተጨባጭ ፀጥታ ሁኔታ በመነሳት ትጥቅ የማስፈታቱን ሂደት ዝርዝር ያወጣሉ።
በሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ ጦር መሪዎች መካከል በሚደረስ ስምምነት መሰረት ከባድ የጦር መሳርያዎችን ለመከላከያ ለማስረከብ ተስማምተዋል።
ከፍተኛ ጦር መኮንኖቹ ተገናኝተው ከተነጋገሩ እና ስምምነት ከደረሱ በኋላ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ የከባድ መሳርያ ትጥቅ የመፍታቱ ሂደት ይጠናቀቃል።
እንዲሁም የተቀመጠው አስር ቀናት ጊዜ ገደብ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በሚሰጡት ሀሳብ እና በሁለቱ ወገኖች አጽዳቂነት ሊራዘም ይችላል።
ከዚህ ስምምነት በኋላ ባሉት 30 ቀናት ቀላል የጦር መሳርያዎችን ጨምሮ ትጥቅ የመፍታት ሂደቱ ሙሉ ሙሉ ይጠናቀቃል።
ታጣቂዎቹን የማሰናበት እና መልሶ ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ ሂደት የክልሉን ሕግ እና ፍላጎት መሠረት ያደረገ ይሆናል።
ሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሻሽ ጦርነት ለማብቃት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል በተደረሰው ስምምነት “የጥይት ድምጽ በዘላቂነት እንዳይሰማ” በመስማማት፣ ጦርነቱ እንዲያበቃ የሚያስችል ዘላቂ የግጭት ማስወገድ ስምምነት ተፈርሟል።
ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ለመፍታት በትግራይ ክልል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና ከዚህ በተጨማሪም በግጭቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ሁለቱ ወገኖች መስማማታቸው ተገልጿል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ለሁለት ዓመታት ሲፋለሙ የቆዩት ሁለቱ ኃይሎች ግጭት ለማቆም ፣ የተስማሙ ሲሆን፤ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እና የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ማረጋጋጥ በሚሉት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።












