ከትግራይ ኃይሎች ስልሳ አምስት በመቶ የሚሆኑቱ ከውጊያ ቀጠናዎች መራቃቸው ተነገረ

ጄኔራል ታደሰ ወረደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሰረት 65 በመቶ የሚሆኑት የትግራይ ኃይሎች ከውጊያ ቀጠናዎች እንዲርቁ መደረጋቸውን ጄኔራል ታደሰ ወረደ አስታወቁ።

ሰራዊቱን ከጦርነት ግንባሮች የማራቅ ሂደቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ቅዳሜ ህዳር 24፣ 2015 ዓ.ም ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ገልጸዋል።

የትግራይ ኃይሎች ከዛላምበሳ፣ ማይቅነጣል፣ ሕጉምብርዳ፣ ነበለት፣ በሪ፣ ተክላይ አበርገሌና የጨርጨር ጦር ግንባሮች መውጣታቸው ተጠቅሷል።

የተንቀሳቀሰው የሰራዊቱ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ባይጠቀስም ከፍተኛ ኃይል መሆኑን ለትግራይ ቴሌቪዥን የተናገሩት ጄኔራሉ ከጦር ግንባሮች በመኪናና በእግር ማንቀሳቀስ መቻሉንም አስረድተዋል።

ከጦርነት ቀጠናዎች ከማራቅ በተጨማሪ ወደተመደበላቸው ቦታዎችም መስፈራቸውም በዚህ ቆይታ ተጠቅሷል።

የትግራይን ኃይሎችን ከውጊያ ቀጠና የማራቅ ሂደቱ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ለማጠናቀቅ በክልሉ ውስጥ ያሉ የውጭና የውስጥ ኃይሎች "ስጋት" ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረድተዋል።

“ለሰላም እንቅፋት ሆነው የቀጠሉ ኃይሎች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚፈጽሙት ግፍ በፈጠረው ስጋት ምክንያት ሰራዊቱ ከጦርነት ቀጠናዎች መራቅ ያልቻለባቸው አካባቢዎች አሉ” ብለዋል።

የውጭና የውስጥ ኃይሎች በያዟቸው አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች በሳሳ መልኩ እንዲቆዩ ተደርጓል ብለዋል።

ቸግሩ ሲቀረፍ ሰራዊቱ መቶ በመቶ ከውጊያ ቀጠናዎች ሙሉ በሙሉ እንዲርቅ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

"የጸጥታ ስምምነት ያደረግነው የሁለቱ ሰራዊት ኃላፊዎች ጥሩ ለመሄድ እየሞከርን ነው።እስካሁንም ድረስ ደህና ርቀት ሄደናል። በርካታ ተግባራት ገና ይጠበቅብናል።። በተለይም የውጭና የውስጥ ኃይሎች እስካልወጡ ድረስ ሂደቱን ያወሳስበዋል፤ ስምምነቱም ላይ አደጋ ደቅኗል” በማለት አስረድተዋል። 

በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በዚህ የአፈጻጸም ሰነድ ላይ ከትግራይ ክልል ይወጣሉ የተባሉት የውጭ አገር እና የፌደራሉ መከላከያ ያልሆኑ የተባሉት የክልል ኃይሎች በስም አልተጠቀሱም።

ከኢትዮጵያ መንግሥት አጋር በመሆን በጦርነቱ እየተሳተፈች ያለችው ጎረቤት አገር ኤርትራ የድርድሩ አካል አልነበረችም።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው ግጭት የማቆም ስምምነት ኤርትራን በቀጥታ ያልጠቀሳት ሲሆን፣ ምዕራባውያን አገራትና ተቋማት ኤርትራ ጦሯን ከትግራይ በተደጋጋጋሚ እንድታስወጣም ሲጠይቁ ይሰማል።

የፌደራል መንግሥት እነዚህን ኃይሎች የመውጣታቸውን ጉዳይ በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

“የውጭና የውስጥ ኃይሎችን ከትግራይ የማስወጣት እንዲሁም በህዝብ ላይ እየፈጸሙ ያሉትን መቆጣጠርም ኃላፊነቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ነው” ያሉት ጄኔራሉ መከላከያ ኃይሎቹን የማስወጣት ተግባር ፈጥኖ ይጀምራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"የትግራይ የጸጥታና ደህንነት ስጋቶች ከውጭም ከውስጥም አሉ "ያሉት ዋና አዛዡ በቀጣይም የክልሉ ጸጥታ ኃይል የውስጥ ስጋቶችን ደህንነት የሚያረጋግጥ ሲሆን የውጭ ስጋቶችን መከላከል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኃላፊነት ይሆናልም ብለዋል።

በተያያያዘ ዜና የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ በሚፈቱበት ዝርዝር ዕቅድ ላይ የጋራ ኮሚቴ በሽረ እንዳስላሴ ሐሙስ ኅዳር 22፣ 2015 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ጄኔራል ታደሰ አስረድተዋል።

ከፌደራል መንግሥቱ እና ከትግራይ ኃይሎች የተውጣጣ አራት አባላት ያሉት የጋራ ኮሚቴ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በቀላል የጦር መሳሪያ ትጥቅ መፍታት ዙሪያ ዝርዝር የአፈጻጸም ዕቅድ አዘጋጅቶ ለሁለቱም ወገን ዋና የጦር አዛዦች ሪፖርት እንደሚያቀርብም ተገልጿል።

የጋራ ኮሚቴው በትግራይ ደህንነት ላይ ክፍተት በማይፈጥር መልኩ ተፈጻሚ በሚሆንበት አሰራር ላይ ዕቅድ ለመንደፍም ነው እየመከረ ነው የተባለው።

ትጥቅ አፈታቱ በራሱ የቆመ ሳይሆን ከትግራይ ህዝብ ደህንነትና ጸጥታ ጋር የተሳሰረ መሆኑን የገለጹት ጄኔራሉ ህዝብ ላይ ስጋት በማይፈጥር መልኩ እንዴት ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል የሚለውንም ባጠና መልኩ ዕቅድ ይነድፋልም ብለዋል ጄኔራሉ ።

የሁለቱም ተወካዮች ለፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦርና ለትግራይ ኃይሎች አዛዥ የተደረሰበትን የጋራ ዕቅድ በየፊናቸው የሚያቀርቡ ሲሆን ይህንንም አዛዦቹ የሚገመግሙት እንደሚሆንም አስረድተዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለቀጠፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ባለፈው ወር መደረሱ ይታወቃል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት አንድ ወር ቢሞላውም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ያልተገደበ እርዳታ ለማስገባት እንዳልተቻለ የዓለም ጤና ድርጅት አርብ ዕለት አስታውቋል።

“የሰላም ስምምነቱ የትግራይ ህዝብ የሚሻውን ያልተገደበ እርዳታ እንዲሁም መጠነ ሰፊ የጤና ድጋፍ ለማድረግ አላስቻለም” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋ ዳይሬክተር ማይክ ራያን ተናግረዋል።

በምዕራብ ትግራይ ባሉ አካባቢዎች ባሉ ሚሊሻዎችና የኤርትራ ወታደሮች በሚቆጣጠሩባቸው የክልሉ አካባቢዎች ጉልህ ችግሮች መኖራቸውን አስረድተዋል።

“በኤርትራ ቁጥጥር ስር ያሉ ሰፊ አካባቢዎች በእርዳታ መድረስ አልተቻለም። በህዝቡ ላይ እየደረሱ ያሉ በጣም የሚረብሹ ሪፖርቶች እየወጡ ነው ብለዋል”

በዚህም የሰላም ስምምነት መሰረት ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው መሰረታዊ አገልግሎት እንዲመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን በመፍታት ህገ መንግሥታዊ ስርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ ነው።