ጠ/ሚ ዐቢይ እና ብሊንከን የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ መውጣትን በተመለከተ ተወያዩ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, @AbiyAhmedAli

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ተገናኝተው፣ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ክልል መውጣትን በተመለከተ መወያየታቸው ተገለጸ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እንዳሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን፣ የኤርትራ ጦር ከሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በፍጥነት መውጣት አስፈላጊነት ላይ ተነጋግረዋል።

ህወሓት እና የፌደራል መንግሥቱ በደቡብ አፍሪካ በደረሱት የሰላም ስምምነት መሠረት የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ የሚወጡት ከህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ መፍታት ጋር ጎን ለጎን ነው።

ስምምነቱ ይህንን ቢልም እስካሁን ድረስ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ስለመውጣቱም ይሁን የመውጣት ጅማሮ ስለመኖሩ በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

የውጭ ጉዳይ ኃላፊው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራ ጦር መውጣትን በተመለከተ መነጋገራቸው፤ የኤርትራ ኃይሎች አሁንም በትግራይ ክልል መኖራቸውን ያመላከተ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከብሊንከን ጋር ያደረጉትን ንግግር አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “ውጤታማ ውይይት አድርገናል። ሰላም ለማስፈን ለምናደርገው ጥረት አሜሪካ ስላደረገችው ትብብር አመስግኛለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።

የትግራይ አመራሮች ከሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ መሠረት፣ የትግራይ ሠራዊት 65 በመቶ ከውጊያ ቀጠናዎች ወጥቷል።

በአሜሪካ - አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጋር በሰሜን ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጉዳይ ላይ መወያየታቸውም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ብሊንከን ከከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው ጋር ዋሽንግተን ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, @AbiyAhmedAli

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ብሊንከን ከከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው ጋር ዋሽንግተን ውስጥ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ የደረሱት ስምምነት አፈጻጸምን አድንቀዋል።

“ይህ ስምምነት በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ቁልፍ ነው” ያሉት ደግሞ ኔድ ፕራይስ ናቸው።

ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ እንደሆነ አንቶኒ ብሊንከን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው መንግሥት እና ህወሓት የደረሱት ስምምነት በፍጥነት ተፈጻሚ እንዲሆን ያሳሰቡ ሲሆን፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብአዊ መብቶች ተቆጣጣሪዎች ግጭት በተከሰተባቸው ቦታዎች እንዲንቀሳቀሱም ጠይቀዋል።

አሜሪካ፣ በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራውን የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት እንዲሁም ስምምነቱ መተግበሩን ከሚያረጋግጠው ኅብረቱ ጎን ለመቆም ያላትን ቁርጠኝነት ገልጻለች።

በጦርነቱ ሳቢያ ተቋርጠው የነበሩ እንደ የኤሌክትሪክ፣ የባንክ፣ የስልክ እና የአየር በረራን የመሳሰሉ የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ከሰላም ስምምነቱ በፊት ተቋርጠው የነበሩ ሰብአዊ እርዳታዎችን በድጋሚ ቢጀምሩም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው የእርዳታ ፍላጎት አንጻር ድጋፉ ውስን መሆኑ በትግራይ አመራሮች እየተገለጸ ነው።

የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የ49 አገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ሁለተኛው የአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. ተጀምሯል።

ለሦስት ቀናት የሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ዓለማችንን እየፈተኗት ያሉ ተግዳሮቶች የአየር ንብረት ቀውስ፣ መልካም አስተዳደር፣ የምግብ ዋስትና እና የዓለም ጤናን የሚጨምር ሲሆን፣ እንዲሁም የአሜሪካ-አፍሪካ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጠናከር ላይ ያተኩራል።

በጉባኤው ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቡድን 20 ውስጥ የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ቦታ እንዲያገኝ ድጋፍ እንደሚሰጡ ይጠበቃል ተብሏል።