በአሜሪካ - አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ምን አይነት ጉዳዮች ይነሳሉ?

የፎቶው ባለመብት, US State Department
የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የ49 አገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ሁለተኛው የአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. ይጀመራል።
ከማክሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ዓለማችንን እየፈተኗት ያሉ ተግዳሮቶች የአየር ንብረት ቀውስ፣ መልካም አስተዳደር፣ የምግብ ዋስትና እና የዓለም ጤናን የሚጨምር ሲሆን፣ እንዲሁም የአሜሪካ-አፍሪካ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጠናከር ላይ ያተኩራል።
“ጉባዔው… አፍሪካ ቁልፍ የጂኦፖለቲካል ተጫዋች እንደሆነች ዕውቅና በመስጠት ላይ የተመሠረተ ነው። አህጉሪቱ የአፍሪካን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የአለምን የወደፊት ሁኔታ ትቀርፃለች” ሲሉ የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ሰኞ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መናገራቸው ተዘግቧል።
በጉባኤው አርባ ዘጠኝ የአፍሪካ መሪዎች እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ተጋብዘዋል ሲሉ ሱሊቫን በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
በዚህ ሳምንት በሚካሄደው የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ፕሬዝዳንት ባይደን በቡድን 20 ውስጥ የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ቦታ እንዲያገኝ ድጋፍ እንደሚሰጡ ይጠበቃል ተብሏል።
በተጫማሪም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ከአፍሪካ አገራት መካከል “ቋሚ አባል እንዲያካትት” ድጋፍ መስጠትን ጨምሮ ማሻሻያ እንዲያደርግ ፕሬዝዳንት ባይደን ቁርጠኛ ናቸው በማለት ሱሊቫን ተናግረዋል።
የአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳዎች
የመሪዎቹ የመክፈቻ ጉባኤ የአፍሪካውያን እና የዲያስፖራ ወጣት መሪዎች ላይ የሚያጠነጥን ይሆናል።
“ድምጾችን ማጉላት፡ ዘላቂ የሆነ ሽርክና መፍጠር” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ፣ ከአህጉሪቱ ጋር የጠበቀ ትስስር ያላቸው አፍሪካውያን እና ዲያስፖራዎች ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክር እንደሆነም ተገልጿል።
የአሜሪካ-አፍሪካ ስትራቴጂያቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ፕሬዝዳንት ባይደን እንዳስታወቁት “የአፍሪካ ዲያስፖራች የጥንካሬያችን ምንጭ ናቸው” ብለዋል።
አህጉሪቷን በመገንባት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱትን በባርነት ከአህጉሪቷ ተግዛው አሜሪካ የደረሱ አፍሪካውያን የልጅ ልጆች፣ ከአፍሪካ ጋር የጠበቀ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ያላቸው ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካውያን ስደተኞችን ያጠቃልላል።
የአፍሪካ እና የዲያስፖራ ወጣት መሪዎች ጉባኤ፣ በፈጠራ ኢንዱስትሪዎች እና በአካባቢ ፍትሃዊነት ላይ ያተኮረ እንደሆነም ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው ማስረጃ ያስረዳል።
የአጎዋ የንግድ ሚኒስትሮች ጉባኤ
አሜሪካ ለአፍሪካውያን አገራት ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ዕድል (አጎዋ) ጋር በተያያዘ ከተጠቃሚ አገራቱ ንግድ ሚኒስትሮች ጋር የሚካሄደው ጉባኤም በዛሬው ዕለት ቀጠሮ ተይዞለታል። ።
የአሜሪካ የንግድ ፖሊሲ ከፍተኛ ባለሥልጣን በሆኑት በአምባሳደር ካትሪን ታይ የሚመራው ይህ ጉባኤ፣ የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት፣ የአሜሪካ መንግሥት እና የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት፣ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና ክልላዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችን የሚያሳትፍ ነው።
በዚህ ጉባኤም በዋነኝነት የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር፣ የሁለትዮሽ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን መደገፍ እና የአሜሪካ-አፍሪካ ንግድን በሚመለከቱ ሌሎች የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች እና አጎዋ ትግበራ ላይ ይወያያል።
አሜሪካ ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል በሚል አጎዋ ከተሰኘው የቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያ መታገዷ ይታወሳል። ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ከሰብዓዊ መብት እና ከዲሞክራሲ ስጋቶች ጋር በተያያዘም ማሊ እና ጊኒም እንዲወገዱ ተደርገዋል።
በወቅቱም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለአሜሪካ ኮንግረስ በጻፉት ደብዳቤ ኢትዮጵያ “በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅማለች” ማለታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድል፣ አግዋ ማስወጣትም ከ200 ሺህ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ላይ ተፅእኖ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚነስቴር የገለጸ ሲሆን፣ በተለይም ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሴቶች ላይ ጉዳቱ ይበረታል ብሎ ነበር።
ከሰሞኑም ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ንግድ አጎዋ እንድትመለስ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለሚያጣረው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሰብዓዊ ባለሙያዎች ቡድን ፍቃድ ስትሰጥ መሆኑ ተዘግቧል።
ሪፖርተር እንግሊዝኛው ጋዜጣ እንደዘገበው የባለሙያዎቹ ቡድን ወደ አገር ውስጥ ገብተው መመርመር እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ባለሥልጣን መናገራቸውን ነው።
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ባወጣው የ19 ገጽ ሪፖርት የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መፈጸማቸውን አካቶ ጦርነቱ ወደተካሄደባቸው የትግራይ ክልል አካባባቢዎች እንዲሄዱ አለመፈቀዱን መግለጹ ይታወሳል።
የአሜሪካና የአፍሪካን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመው ጉባኤ
በተጨማሪም የሲቪል ማኅበረሰቦች፣ የአፍሪካ ጠፈር፣ የሰላም፣ የፀጥታ እና አስተዳደር፣ የጤና ትብብር ጉባኤዎች በዛሬው ዕለት ይካሄዳሉ።
ታኅሣሥ 05/2015 ዓ.ም. የሚካሄዱት ጉባኤዎች በአሜሪካ- አፍሪካ ቢዝነስ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ይሆናል። በዚህም ጉባኤ ላይ ፕሬዚዳንት ባይደን ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የአሜሪካ- የአፍሪካ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት የወደፊት ዕጣፈንታ፣ ለአፍሪካ መሠረተ ልማት እና የኃይል ሽግግርን ለመገንባት ሽርክናን መፍጠር፣ የምግብ ዋስትናን የማጠናከር አጋርነት፣ የዲጂታል ግንኙነትን ማሳደግ እና በቴክኖሎጂ ሁሉን አቀፍ ዕድገት የማስቻል ትብብር የሚሉ ውይይቶችንም ያካተተ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ-ገጹ አውጥቷል።
በማጠቃለው ሐሙስ ታኅሣሥ 06/2015 ዓ.ም. የመሪዎች ጉባኤ ይካሄዳል።
በዚህም “መልካም አስተዳደር፣ ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት፣ ፍትህ እና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት አፍሪካ”፤ “ሰላምና አስተማማኝ የሰፈነባት አፍሪካ”፤ “በአካታች ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ላይ በመመስረት የበለጸገች አፍሪካ” በሚልም በሦስት ክፍሎች ይካሄዳል።
ጉባኤው አሜሪካ እንደ ዋና ዓለም አቀፍ ተፎካካሪዋ የምትመለከታት ቻይና በአፍሪካ ያላት ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ ብልጫ ባለበት ወቅት ነው። ከቻይና በተጨማሪ ሩሲያ በዩክሬን እያደረገችው ያለውን ጦርነት አህጉሪቷ ድጋፍ እንድትሰጣት እየጣረች ትገኛለች።
በባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር የባይደን አስተዳደር ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራትን በተመለከተ አዲስ የስትራቴጂ ሰነድ አውጥቷል። ይህም ሰነድ የአህጉሪቷን ጠቃሚነት በማጉላት የአሜሪካን እሳቤ ከሚጋሩ አገራትም ጋር የመከላከያ ትብብርንም አስፈላጊነት ጠቅሷል።
ፕሬዝዳንት ባይደን አገራቸው የተባበሩት መንግሥታትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ ከሌሎች አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለመገንባት እየጣሩ ይገኛሉ።
በተለይም ከእሳቸው በፊት የነበሩት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ፖሊሲያቸው “ቀዳሚዋ አሜሪካ” በማለት ላይ የተመሠረተ እና የአፍሪካ አገራትንም በመዝለፍና በማንቋሸሽ ለአራት አመታት መስራታቸውንም ተከትሎ ፕሬዚዳንት ባይደን ይህንን ለማስተካከል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
የመጀመሪያው የአሜሪካ አፍሪካ ጉባኤ የተካሄደው በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመን ከስምንት ዓመታት በፊት ሲሆን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ አሜሪካ በአፍሪካ ውስጥ ያላት ሚና ማሽቆልቆሉም ተነግሯል።
የባይደን አስተዳደር ባለሥልጣናት በአፍሪካ ካሉ አገራት ጋር አሜሪካ ያላትን ግንኙነት ማጠናከርም እንደሚያስፈልግ ሲያሳስቡም ይሰማል።
“ከኮንግረሱ (ምክር ቤቱ) ጋር በቅርበት በመሥራት አሜሪካ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ 55 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ ትሰጣለች” ሲል ሱሊቫን ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።።












