ኪሊያን ምባፔን የምርጦች ምርጥ ያስባሉት ሰባት ነገሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA
በዚህ ሳምንት ማብቂያ ላይ ቅዳሜ ዕለት የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በጉጉት የሚጠብቁት የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ይካሄዳል።
በዚህም ጨዋታ ምርጦቹ የፈረንሳይ እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድኖች ይፋለማሉ።
የሁለቱ ቡድን ጨዋታ ታላቅ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ የፈረንሳዩ ድንቅ ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ ነው።
በእግር ኳስ አፍቃሪዎችም ዘንድ ምባፔ አይረሴ ኮከብ ነው።
የፓሪስ ሴንት ዠርሜይን አጥቂ ኪሊያን ምባፔ በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ምርጡ ተጫዋች ነው ቢባል ድፍረት አይሆንም።
ከሁለቱ አገራት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ጋር ተያይዞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ስሪ ላየንስ አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት እንዴት ምባፔን መግታት ይችላል የሚለው ከሰሞኑ ዋነኛ የእግር ኳስ መወያያ ርዕሶች አንዱ ሆኗል።
ቢቢሲ ስፖርት በአሁኑ ወቅት ምርጥ ስለሚባለው ምባፔ እና የእግር ኳስ ፈርጥ ስላስባለው ሰባት ጉዳዮች እንንገርዎ ይላል።
1. በታሪክ ሁለተኛው በጣም ውድ ተጫዋች
ኪሊያን ምባፔ አሁን ያለበትን ቡድኑን ፓሪስ ሴይን ዠርሜይንን የተቀላቀለው ከሞናኮ ክለብ በውሰት ነበር። ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 2017 ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ዝውውሩ በ180 ሚሊዮን ዩሮ ቋሚ ተጫዋች ሆነ።
ይህም በዓለማችን ላይ ሁለተኛው ውድ የእግር ኳስ ተጫዋች ዝውውር ነው። በአንደኛነት የተቀመጠውና ከምባፔ የሚበልጠው ብቸኛው ዝውውር የብራዚላዊው አጥቂ ኔይማር ነው።
ኔይማር ከባርሴሎና ወደ ፓሪስ ሴይንት ዠርሜይን የተዘዋወረው በ222 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፣ ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር።
ምባፔ ለፈረንሳይ የሻምፒዮና ውድድር በ237 ጨዋታዎች 190 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። በዚህም ክለብ ከታላላቆቹ ኔይማር እና አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ጋር ይጫወታል።
2. በተደጋጋሚ አሸናፊነቱን ያስመሰከረ
ፕሮፌሽናል ተጫዋች በሆነባቸው ሰባት ዓመታት ውስት ምባፔ ያሸነፋቸው ጨዋታዎች፡
- የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ
- የ2020/21 የአውሮፓ ህብረት እግር ኳስ ማህበራት ጨዋታዎች (ዩኢኤፍኤ)
- አምስት የሊግ ዋንጫዎች (አራት በፓሪስ ሴይንት ዠርሜይን፣ አንድ በሞናኮ)
- አራት የፈረንሳይ ዋንጫዎች
- ሁለት የፈረንሳይ ሊግ ዋንጫዎች
እነዚህ በቡድን ስር ታቅፎ ሲሆን፣ በግልም በርካታ ሽልማቶችን ተቀዳጅቷል። በአውሮፓ ምርጥ ከ21 ዓመት በታች ተጫዋች የሚሰጠውን ‘ጎልደን ቦይ’ ሽልማት በአውሮፓውያኑ 2017 አሸንፏል።
ሁለት ጊዜ በፈረንሳይ ምርጥ ተጫዋችነት፣ በሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች እንዲሁም ሦስት ጊዜ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች የሚሉ ሽልማቶችን የወሰደ ድንቅ ተጫዋች ነው።
በ2018 የዓለም ዋንጫ ምርጥ ወጣት ተጫዋች እንዲሁም በመጀመሪያው ሊግ በአራት የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ አግቢ ነበር።
ክለቡን ፒኤስጂን በ2020 ለመጀመሪያ ጊዜ የሻምፒዮን ሊግ ፍጻሜ በማድረስም ታሪክ ሰርቷል።
3. የዓለም ዋንጫዎችን የሚያደምቅ ተጫዋች
ምባፔ ፈረንሳይ አሸናፊ የሆነችበት የ2018 ዓለም ዋንጫ ሲካሄድ ገና የ19 ዓመት ታዳጊ ነበር። በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ቁልፍ ስፍራ የነበረው ምባፔ አራት ጎሎችን አስቆጥሯል።
ፈረንሳይ ክሮሺያን 4 ለ 2 ባሸነፈችበት የፍጻሜ ጨዋታ ምባፔ ለአገሩ አንድ ጎል አስመዝግቧል። በዓለም የፍጻሜ ዋንጫ ጎል ያስቆጠረ ሁለተኛው ታዳጊ በመሆንም ታሪክ ሰርቷል።
ከእሱ በፊት ታዋቂው የብራዚል ተጫዋች ፔሌ በ1958 በነበረው የፍጻሜ ጨዋታ ነበር ጎል ያስቆጠረው።
ምባፔ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው የኳታር የዓለም ዋንጫ አምስት ጎሎችን በማስቆጠር ቀዳሚ ስፍራን ይዟል።
በአጠቃላይ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎው ባስመዘገበው ዘጠኝ ጎል፣ ለአርጀንቲና ስምንት ጎል ያስቆጠረውን ዲያጎ ማራዶናን እና ፖርቹጋላዊውን ክርስቲያኖ ሮናልዶን በመብለጥ የቁንጮነት ስፍራውን ተቆጣጥሯል።
በ24 ዓመቱ ለፖርቹጋል ስምንት ጎል በማስቆጠር በዩሴቢዮ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በመስበር ዘጠኝ ጎሎችን በዓለም ዋንጫ ያስቆጠረ ትንሹ ተጫዋች ነው - ምባፔ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
4. በለጋ እድሜው ክብረ ወሰን መስበር የቻለ
ምባፔ የተወለደው ከፓሪስ ወጣ ብላ በምትገኝ ስፍራ ነው። በአካቢው በሚገኝ ኤኤስ ቦንዲ በሚባል ቡድን እግር ኳስ ጨዋታን ቢጀምርም የትልልቅ ክለቦችን ቀልብ ለመሳብ ረዥም ጊዜ አልወሰደበትም።
በአውሮፓውያኑ 2015 ከፈረንሳይ ታዋቂ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነውን የሞናኮ ክለብን ተቀላቀለ።
በወቅት እድሜው 16 ዓመት የነበረ ሲሆን፣ በክለቡ ታሪክ ትንሹ ተጫዋች መሆን ችሏል። ከዚህ ቀደም የፈረንሳይ እና የአርሰናል ታላቅ ተጫዋች በነበረው ቲየሪ ኦንሪ በ88ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ለትንሽ ደቂቃ በመጫወት ተይዞ የነበረውንም ክብረ ወሰን ምባፔ መስበር ችሏል።
ክለቡን ከተቀላቀለ ከሦስት ወራት በኋላም ትሮይስ ክለብ ላይ ባስቆጠራት ጎል ትንሹ ጎል አግቢ ሆነ። ከዚህ ቀደም የነበረውን ክብረ ወሰን ይዞት የነበረው ቲየሪ ኦንሪ ነበር።
5. አስደናቂ ፍጥነትን የተላበሰ ተጫዋች
ፈረንሳይ ፖላንድን 3 ለ 1 ባሸነፈችበት በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ምባፔ ያስመዘገበው ፍጥነት በሰዓት 35.3 ኪሎሜትር ነው።
ከእሁዱ ጨዋታ በፊትም ይህንን ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን፣ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ፈጣን ሰዓትን ያስመዘገቡ ስድስት ተጫዋቾች ብቻ ናቸው።
በሊጉም በሰዓት ከ36 ኪሎሜትር ፍጥነት በማስመዝገብ ፈጣኑ ተጫዋች እንደሆነም ተጠቅሷል።
ይህንንም በአግባቡ ለመረዳት ጃማይካዊው የአጭር ርቀት የኦሊምፒክ የሩጫ ውድድር አሸናፊ እና ከፈጣኑ ዩሴን ቦልት አንጻር እንየው።
ቦልት በ2009፣ የ100 ሜትር ውድድር፣ በ9.58 ሰከንዶች የዓለም ክብረ ወሰንን በሰበረበት ወቅት በአማካይ የሮጠው 37.58 ኪሎ ሜትር ነበር።
ሆኖም ከ60 እስከ 80 ሜትር እየሮጠ በነበረበት ወቅት ያስመዘገበው ፈጣን ሰዓት 44.72 ኪሎ ሜትር በሰዓት ነው።
6. ከፍተኛ የዝውውር ገንዘብን ውድቅ ያደረገ
ከሪያል ማድሪድ ፕሬዚዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ከረዥም ጊዜ መጠናናት በኋላ ከላሊጋው ታላቅ ክለብ ጋር በገንዘብ ፖኬጅ ተስማሙ።
ሆኖም ምባፔ ስምምነቱን ውድቅ በማድረግ በፓሪስ ለመቆየት ወሰነ። ከክለቡም ጋር አዲስ የሦስት ዓመት ውል ፈረመ።
የስፔን እግር ኳስ ኤክስፐርት ጊሌም ባላግ እንደተናገሩት ሁለቱም ክለቦች ለምባፔ ለፊርማ ብቻ 150 ሚሊዮን ዩሮ ለመክፈል ፈቃደኞች ነበሩ ብለዋል።
ይሁን እንጂ ለወደፊቱ ወደ ስፔን እና አውሮፓ ሻምፒዮን ሊግ ክለቦች ሊቀላቀል ይችላል የሚለውን ሃሳብ አላቆመም።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ የሪያል ማድሪድ ህልሙ “በፍፁም አላበቃም” ሲል ምባፔ ተናግሯል።
7. ባለጸጋ እና ለጋሽ የእግር ኳስ ኮከብ
በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ምባፔ በፎርብስ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው የእግር ኳስ ተጫዋቾች ዘንድ ቀዳሚ ስፍራ ላይ ተቀምጧል።
ለዘጠኝ ዓመታት ያህልም ከባለጸጎቹ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሜሲ ወይም ሮናልዶ ውጪ ይህንን ስፍራ ማግኘት የቻለ የለም።
በአሁኑ የውድድር ዘመንም 128 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያገኝ ተገምቷል።
ምባፔ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይም ታዋቂ ሲሆን በፌስቡክ፣ በኢንስታግራም እና በትዊተር መድረኮች ላይ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች አሉት።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ላይ በመጫወት ከሮናልዶ፣ ከሜሲ እና ከኔይማር ጋር ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጣሪ በሚልም በኢንስታግራም ተሰይሟል።
እጆቹን በማጣመር እና ደስታውን ለመግለጽ በጉልበቱ የሚንሸራተተው ምባፔ በፊፋ 21 ጨዋታዎች መጽሄት ሽፋን ላይ በመውጣት ትንሹ ስፖርትኛ ነው። በዘንድሮው እትምም ተጫዋቹ እንደገና ተመልሶ መምጣት ችሏል።
ምባፔ ከአራት ዓመት በፊት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የዓለም ዋንጫን ካሸነፈ በኋላ ለውድድሩ የሚከፈለውን 380 ሺህ ፓውንድ የውድድር ደመወዙን ለሕፃናት በጎ አድራጎት ድርጅት መለገሱን አስታውቋል።












