ኢቢሲ ያልተፈቀዱለትን የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በማስተላለፉ ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቀው ፊፋ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በኳታር ዶሃ እየተካሄደ የሚገኛውን የዓለም ዋንጫ በቀጥታ እንዲያስተላለፍ ከተፈቀዱለት ጨዋታዎች ውጪ በመቅረቡ ቅጣት እንደሚጠብቀው ፊፋ ለቢቢሲ ገለጸ።
ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቢሲ ሁለት ሳምንት የሆነውን በኳታር እየተካሄደ የሚገኘውን የዓለም ዋንጫ ውድድር ሁሉንም ጨዋታዎች ለተመልካቾቹ እንደሚያቀርብ ሲገልጽ እንደነበር ይታወሳል።
ነገር ግን ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደገለጹት የቴሌቪዥን ጣቢያው ለተመልካቾቹ እንዲያቀርብ የተፈቀደለት የተወሰኑ ጨዋታዎችን ሆኖ ሳለ ከዚህ ውጪ ውድድሮችን አስተላለፏል ብሏል።
ይህም ኢቢሲ እንዲያስተላለፍ መብት ከተሰጠው ጨዋታዎች ውጪ ነጻ በሆነ ስርጭት ማስተላለፉ በኢቲቪ በኩል ለተመልካች በማቅረቡ ከፊፋ ጋር የገባውን ውል በግለጽ የሚጥስ ነው ሲል ቅሬታውን ገልጿል።
በዚህም ሳቢያ የዓለም ዋንጫን ለተመልካቹ እንዲያቀርብ ፊፋ ከኢቢሲ ጋር የገባው ስምምነት መቋረጡን ገልጾ፣ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ “ጠንካራ” ያለውን እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ነገር ግን ከዚህ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በኢቢሲ ላይ እወስዳለው ስላለው እርምጃ ምንነት ከመግለጽ ተቆጥቧል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ የበላይ አካል ጋር የገባው ውል በመቋረጡ ተቋሙ በኳታር እየተካሄዱ ያሉትን ቀሪ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ማስተላለፍ አልተፈቀደለትም።
ፊፋ ይህንን ቢልም ኢቢሲ የኳታር ዓለም ዋንጫ አንዳንድ ጨዋታዎችን እያስተላለፈ እንደሚገኝ ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።
ፊፋ ለቢቢሲ እንደገለጸው የዓለም እግር ኳስ ውድድርን ለማስተላለፍ ከተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር ከስምምነት ደርሶ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ጨዋታዎችን ማስተላለፍ አይቻልም።
ስለዚህም የፊፋ ፈቃድ ሳይኖር “በየትኛውም አይነት የሥርጭት ዘዴ፣ በመስመር ቴሌቪዥን ወይም በዲጂታል መድረኮች አማካይነት የሚደረጉ የሥርጭት ስርቆቶችን” አጥብቆ እንደሚከታተል እና እርምጃ እንደሚወስድ አመልክቷል።
ይህንንም ለመከላከል ፊፋ ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ በመላው ዓለም ከትትል ከማድረጉ በተጨማሪ ከብሮድካስተሮች፣ ከዲጂታል ሚዲያ መድረኮች እና ከማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች ጋር በጋራ ይሰራል።
በተጨማሪም የሥርጭት የቴክኒክ አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም የብሮድካስት ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት በመተባበር “በውድድሮች ሥርጭት ላይ የሚፈጸሙ ማንኛውንም አይነት የተዘረፋ ስርጭቶችን ለመለየት እና ለማቆም ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል” በማለት የፊፋ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናገረዋል።
ከኢቢኢ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር እንዳለው “በቴሊቪዥንም ይሁን በሌሎች ዲጂታል አማራጮች የሚደረጉ “ስርቆቶችን” በቸልታ አልመለከትም” ያለ ሲሆን፣ ለዚህም ከአጋሮቹ ጋር በመተባበር ክትትል እና እርምጃ ይወስዳል ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ፊፋ ስለሰጠው ማስጠንቀቂያም ሆነ ቅጣቱን አስመልክቶ እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።
በባሕረ ሰላጤዋ አገር ኳታር እየተካሄደ ያለው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድርን በዓለም ዙሪያ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በቴሌቪዥን አማካይነት እየተከታተሉት ነው።
አስካሁን ባለው ግምት መሠረት የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ በተለያዩ የሥርጫት መንገዶች አመካይነት አስከ አምስት ቢሊዮን የሚደርስ ሕዝብ እንደሚመለከተው ተነግሯል።












