ኪሊያን ምባፔ፣ ማርቲኔዝ ደስታውን ስለገለጸበት መንገድ ተጠይቆ ምን አለ?

ምባፔ እና ማርቲኔዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፈረንሳይ የፊት መስመር ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ ከዓለም ዋንጫው የፍጻሜ ጨዋታ በኋላ የአርጀንቲናው ግብ ጠባቂ ደስታ አገላለጸን በተመለከተ አስተያየቱን ሲጠየቅ “ረብ የለሽ በሆኑ ነገሮች አቅሜን አላባክንም” አለ።

የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ኢሚሊያኖ ማርቲኔዝ ብሔራዊ ቡድኑ ፈረንሳይን አሸንፎ የዓለም ዋንጫን ካነሳ በኋላ ያሳየው የደስታ አገላለጽ በበርካቶች አስተችቶታል።

ማርቲኔዝ ከዋንጫ ጨዋታው በኋላ የመልበሻ ክፍል ውስጥ ለምባፔ የአንድ ደቂቃ የጽሞና ጊዜ እንዲደረግ የቡድን አጋሮቹን ከመጠየቁም በላይ፣ ቡድኑ አርጀንቲና ከደረሰ በኋላ የምባፔ ምስል የታተመበት አሻንጉሊት በእጁ ይዞ ታይቷል።

“የደስታ አገላለጾች ለእኔ ችግር አይደሉም” ሲል ምባፔ ለአርኤምሲ ስፖርት ተናግሯል። “እንዲህ ረብ የለሽ በሆኑ ነገሮች ላይ አቅሜን አላባክንም” ብሏል ፈረንሳያዊው እግር ኳሰኛ።

ማርቲኔዝ ስፖርታዊ ሥነ-ምግባር የጎደላው የደስታ አገላለጽ ከማድረጉም በላይ የዓለም ዋንጫው ኮከብ ግብ ጠባቂ ተበሎ በተሰጠው የወርቅ ጓንት አስነዋሪ የተባለ ምልክት አሳይቷል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የአንስቶን ቪላ ክለብ ግብ ጠባቂ የሆነው ማርቲኔዝ ዛሬ ቡድኑን ተቀላቅሎ ልምምዱን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

የቪላ አሰልጣኝ ኡናይ ኢምሪ የደስታ አገላለጹን በተመለከተ ከማርቲኔዝ ጋር እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።

በፍጻሜ ጨዋታው ማርቲኔዝ ላይ ሦስት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው ምባፔ፤ የዋንጫ ጨዋታው ውጤት ከክለብ አጋሩ ሊዮኔል ሜሲ ጋር ምንም አይነት ችግር እንደማይፈጠር ተናግሯል።

“ከጨዋታው በኋላ ሜሲን አነጋግሬዋለሁ፤ እንኳን ደስ ያለህም ብዬዋለሁ” ሲል ምባፔ ተናግሯል።

“ይህ ለእኔም ሆነ ለእርሱ ትልቅ የሕይወት ስኬት ነው፤ እኔ አልተሳካልኝም፤ ሁሌም ስፖርታዊ ጨዋነት ሊኖረን ይገባል” ብሏል።

ማርቲኔዝን በተለይ ምባፔን ዒላማ ያደረጉ የደስታ አገላለጾቹ ፈረንሳያውያንን ያስቆጣ ነበር።

የቀድሞ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ አዲል ራሚ፤ በፈረንሳይ “በጣም የተጣለ ሰው ቢኖር ማርቲኔዝ ነው” ሲል፣ የፈረንሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ካርል ኦሊቭ ደግሞ ፊፋ ለማርቲኔዝ የሰጠውን የኮከብ ግብ ጠባቂ ሽልማትን መንጠቅ አለበት ብለዋል።

ከዓለም ዋንጫ መጠናቀቅ በኋላ በፍጥነት ወደ ክለቡ የተመለሰው ምባፔ፤ ቡድኑ ትናንት ረቡዕ ታኅሣሥ 19/2015 ዓ.ም. ከስትራስቦሮ ጋር በነበረው ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃዎች ጎል አስቆጠሮ ክለቡ ፒኤስጂ የደረጃ ሰንጠረዡን በ8 ነጥብ ልዩነት መምራት እንዲመራ አስችሏል።

የ24 ዓመቱ ፈጣኑ አጥቂ ምባፔ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ 8 ጎሎችን በማስቆጠር የወርቅ ጫማ አሸናፊ ለመሆኑ ችሏል።