አየር መንገዱ በመንገደኞች ፍላጎት መሠረት የመቀለ የበረራ ቁጥርን ከፍ አደርጋለሁ አለ

አየር መንገዱ ወደ መቀለ የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር ለመጨመር አስፈላጊው ሁኑ እንዳለው ገልጿል

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines

የምስሉ መግለጫ, አየር መንገዱ ወደ መቀለ የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር ለመጨመር አስፈላጊው ሁኑ እንዳለው ገልጿል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀለ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የመንገደኞች ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የበረራ ቁጥርን ከፍ ማድረግ እችላለሁ አለ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያደቻ ለቢቢሲ ሲናገሩ በአሁኑ ወቅት ወደ መቀለ እየተደረጉ ያሉ የበረራ ቁጥሮችን መጨመር ይቻላል ብለዋል።

አየር መንገዱ ዘግየት ብሎ ሐሙስ አመሻሽ ታኅሣሥ 20/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ወደ ትግራይ መዲና የሚያደርገውን በረራ በቀን ወደ ሦስት ከፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በረራውን አቋርጦ የነበረው አየር መንገዱ፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 19/2015 ዓ.ም. ወደ መቀለ የሚያደርገውን በረራ ጀምሯል።

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት 82 ሰዎች የመጫን አቅም ያላቸውን ቦምባርድኤይር ዳሽ 8-ኪው400 በተባሉ አውሮፕላኖች በቀን ሁለት በረራዎችን እያደረገ ይገኛል።

አየር መንገዱ በረራውን መጀመሩን ተከትሎ በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ወደ መቀለ ለመጓዝ ፍላጎት ቢኖራቸውም የአየር ቲኬት ማግኘት እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው።

አቶ ለማ ያደቻ ግን አየር መንገዱ የተጓዥ ደንበኞቹን ፍላጎት እያሟላ ከመሆኑም በላይ፣ ወደ መቀለ እና ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ በሚደረጉ በረራዎች ላይ ክፍት ወንበሮች እንዳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ለጊዜው ከሚጠበቀው በላይ ፍላጎት የለም። ምናልባት የሰው መሻት ሊሆን ይችላል እንጂ አስፈላጊ ከሆነ በግማሽ ቀን ውስጥ አምስትም፤ ስድስትም በረራ ማድረግ እንችላለን ችግር የለብንም” ብለዋል።

የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ረቡዕ ዕለት ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ በነበረው በረራ 12 ክፍት ወንበሮች እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን፤ ዛሬ 5 ሰዓት ላይ ወደ መቀለ በነበረው በረራ ላይ ደግሞ 21 እንዲሁም በሁለተኛው በረራ ከአዲስ አበባ የተነሳው አውሮፕላን 34 ክፍት ወንበሮች ነበሩት ብለዋል።

“ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚንጸባረቀው እና መሬት ላይ ያለው እውነታ ልዩነት ያሳያል” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ለማ ያደቻ ይህን ይበሉ እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ-ገጽ ከአዲስ አበባ - መቀለ እንዲሁም ከመቀለ - አዲስ አበባ ለሚደረጉ በረራዎች ያሉ ትኬቶች አስከ ታኅሣሥ 29/2015 ዓ.ም. ተሽጠው ማለቃቸውን ያሳያል።

በስልክ ጥሪ ለበረራ ለመመዝገብ ሙከራ ቢደረግም በተጠባባቂ ከመመዝገብ ውጪ የበረራ ቲኬት ማግኘት አይቻልም።

“በቀን ሁለቴ የሚደረገው በረራ አሁን ያለውን ፍላጎት ያሳካ ይመስላል። . . .አውሮፕላን አለን፣ የበረራ ሠራተኞች አሉን፣ ቦታውም ቅርብ ከመሆኑ አንጻር ተመላልሶ መስራት ይቻላል፤ ስለዚህ ፍላጎቱ ካለ ያለምንም ገደብ መንገደኞችን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን” ብለዋል አቶ ለማ።

የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ የሚያደርገው በረራ በአገር ውስጥ ከሚደረጉት ውስጥ በብዛት ቀዳሚው የነበረ ሲሆን፣ ወደ መቀለ በቀን ከ10 እስከ 14 በረራዎች ይደረጉ ነበር።

ከመቀለ በተጨማሪ ወደ ሽረ ከተማ ዕለታዊ በረራ ይደረግ የነበረ ሲሆን፣ ወደ ታሪካዊቷ የአክሱም ከተማ ደግሞ በቀን እስከ ሁለት በረራዎች ይደረጉ ነበር።

አቶ ለማ ያደቻ አየር መንገዱ ከመቀለ በተጨማሪ በቅርብ ቀናት ወደ ሽረ ከተማ በረራ ማድረግ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

አየር መንገዱም ሐሙስ አመሻሽ ባወጣው መግለጫ ከሰኞ ታኅሣሥ 24/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሽሬ ከተማ በቀን አንድ በረራ ማድረግ የሚጀምር መሆኑን አስታውቋል።

አቶ ለማ ከሽረ በተጨማሪ አየር መንገዱ የአክሱም አየር ማረፊያ የሚያስፈልገው ሥራ ከተከናወነለት በኋላ ወደ አክሱም በረራ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።

በትግራይ ውስጥ የጦርነቱን መባባስ ተከትሎ ከአየር ትራንስፖርት በተጨማሪ የስልክ፣ የመብራት፣ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ከአንድ ዓመት በላይ ተቋርጠው ቆይተዋል።

በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ እነዚህ መሠረታዊ አገልግሎቶች ቀስ በቀስ ሥራ እየጀመሩ ይገኛሉ።