የአፍሪካ ኅብረት ልዑካን እና የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች መቀለ ከተማ ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Tigray TV
የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የፌደራሉን መንግሥት እና ህወሓትን ሲያደራድሩ የነበሩ የአፍሪካ ኅብረት ልዑካን ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ገቡ።
ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ጦርነት ለመቋጨት ድርድሩን ሲመሩ የቆዩት ከአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ አዳራዳሪዎች መካከል የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እና የኬንያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መቀለ መግባታቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ከሁለቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ጋር የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበያው (ዶ/ር) በተመሳሳይ መቀለ ይገኛሉ።
የህወሓት ንብረት የሆነው ድምጺ ወያኔ ደግሞ የ32 አገራት አምባሳደሮች ዛሬ ሐሙስ ታኅሣሥ 20/2015 ዓ.ም. ረፋድ መቀለ መግባታቸውን በፎቶ አስደግፎ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የብሪታኒያ አምባሰደርን ጨምሮ የሌሎች የአውሮፓ እና አፍሪካ አገራት አምባሳደሮች መቀለ ሲገቡ፣ በክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል ተብሏል።
ከአምባሳደሮቹ ጋርም የፌደራል መንግሥቱ የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) አብረው ወደ መቀለ የተጓዙ ሲሆን፤ አምባሳደሮቹ በመቀለ ቆይታቸው ከፌደራል እና ከትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ እና የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸምን እንደሚመለከቱ ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Dimtsi Woyane
የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ ቡድን አባላት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) በመቀለ ቆይታቸው በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ የደረሱት የሰላም ስምምነት አፈጻጸመን ይገመግማሉ ተብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ሠራዊት ከዛሬ ሐሙስ ታኅሣሥ 20/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ መቀለ መግባት እንደሚጀመር እና የህወሓት ኃይሎችም ከባድ መሳሪያ ማስረከብ እንደሚችሉ ገልጸው ነበር።
ነገር ግን ከአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች እንዲሁም በርካታ ዲፕሎማቶች ወደ መቀለ ከመጓዛቸው ውጪ አስካሁን አምባሳደር ሬድዋን ያሉት ተግባራዊ መሆን ስለመጀመሩ የተለባለ ነገር የለም።
ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት ሲፋለሙ የነበሩት ሁለቱ አካላት ጦርነት አንድ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ፤ ሁለት ግዜ ደግሞ በናይሮቢ ኬንያ ተገናኝተው ዝርዝር ስምምነት ተፈራርመዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነትን በዘላቂነት ለማቆም፣ የህወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ የውጭ ኃይሎችን ከትግራይ ለማስወጣት፣ መሠረታዊ አግልግሎቶችን ለማስጀመር እና የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።
በሁለቱ ወገን ያሉት የጦር አዛዦች ናይሮቢ ኬንያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ላይ ከስምምነት ደርሰው ነበረ።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እና ሐሙስ ታኅሣሥ 12 እና 13/2015 ዓ.ም. ባደረጉት ሁለተኛ ዙር የናይሮቢ ንግግር ደግሞ ለሰላም ስምምነቱ ተገዢ በመሆን የስምምነቱን አፈጻጸም በጋራ ለመቆጣጠር እና ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የመከታተያ ነጥቦች ላይ ተስማምተዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ሁለተኛው ዙር የናይሮቢ ንግግር ስምምነትን ይፋ ሲያደርጉ የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ መቀለ ያመራል ማለታቸው ይታወሳል።
ኡሁሩ በዕለቱ የኅብረቱ አደራዳሪዎች ወደ ትግራይ የሚያቀኑት ከሳምንታት በፊት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰውን ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት አፈጻጸምን ለመታዘብ መሆኑን ተናግረው ነበር።
የአገራት አምባሳደሮች እና የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች ወደ መቀለ መጓዛቸው የእርስ በርስ ጦርነቱን ለመቋጨት የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የትግራይ ኃይሎች ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል።
አምባሳደሮቹ እና የአፍሪካ ኅብረት ልዑካን ወደ መቀለ የተጓዙት የፌደራል መንግሥቱ ልዑካን ጉዞን ተከትሎ ነው።
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ታኅሳስ 18/2015 ዓ.ም. በኢፌድሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌደራል መንግሥቱ ልዑካን ወደ መቀለ ተጉዞ ከክልሉ መሪዎች እና ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርጎ ተመልሷል።
ከልዑኩ ጉብኝት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞ በረራ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ በረራ የጀመረ ሲሆን፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 19 አመሻሽ ላይ ደግሞ የክልሉ መዲና መቀለ የስልክ አገልግሎት ማግኘት ትችላለች።












