በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ዙሪያ የወጣውን የምርመራ ሪፖርት የአሜሪካ ባለሙያዎች ተቹ

አደጋው የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ስባሪ አካል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አደጋው የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ስባሪ አካል

ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ ምክንያት በተመለከተ ባለፈው ሳምንት የወጣውን የምርመራ ሪፖርት የአሜሪካ የአየር በረራ ደኅንነት ባለሙያዎች ተቹ።

ከአራት ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወድቆ የተከሰከሰውና ለ175 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው የቦይን 737 ማክስ-8 አውሮፕላን አደጋ መንስኤን ለማወቅ የተደረገው ምርመራ የማጠቃለያ ሪፖርት ታኅሣሥ 14/2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በኩል ይፋ ተደርጓል።

በዚህ ሪፖርት መሠረት ለአውሮፕላኑ መከስከስ ቦይንግ የገጠመው ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም” የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግር እንደሆነ ማረጋገጡን አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎ የአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት ደኅንት ባለሙያዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ባለሙያዎች የተደረገው ምርመራ ሪፖርት የአብራሪዎች ሥልጣናን እና በአደጋ ጊዜ ሊተገበሩ ስለሚገባቸው ቅደም ተከተሎች ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም ሲሉ መተቸታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

በተጨማሪም ቦይንግ ስለ በረራ መቆጣጠሪያ መተግበሪያ በቂ መረጃ እንዳልሰጠ እና ለአብራሪዎቹም በምስለ በረራ የታገዘ የኤምካስ ስልጠና አለማዘጋጀቱ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል አምደዬ አያሌው መግለጻቸው ተዘግቧል። 

የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ በሪፖርቱ ላይ በሰጠው አስተያየት ላይ ለቦይንግ 737 ማክስ-8 አውሮፕላን አደጋ ምክንያት ናቸው በተባሉ ቢያንስ በሁለት ቁልፍ ግኝቶች ላይ እንደማይስማማ አመልክቷል።

ተመሳሳይ አደጋ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በፊት በኢንዶኔዢያው ላየን ኤር ላይ ያጋጠመ ሲሆን፣ ከሁለተኛው አሰቃቂ አደጋ በኋላ ቦይንግ 737 ማክስ- ስምንት አውሮፕላኖች በመላው ዓለም ከበረራ ውጪ ሆነው መቆየታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የዘገየውን የአደጋውን የምርመራ ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ጊዜ የኢቲ 302 በረራ አውሮፕላን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የተሳሳቱ መረጃዎች ወደ በረራው መቆጣጠሪያ ሥርዓት በመላክ አፍንጫው የመድፈቅ ችግር ስላጋጠመው ከቁጥጥር ውጪ መሆኑን ገልጿል።

የአደጋ ምርመራ ስራው በሚከናወንበት ወቅት በርካታ ጫናዎች እንደነበሩ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የመጨረሻ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት የተጠቀሰ ሲሆን ሁሉንም ተቋቁሞ የሁለቱንም ወገን ጥያቄ የሚመልስ ሪፖርት እንደተሰራ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የመርማሪ ቡድኑ መሪ የሆኑት ኮሎኔል አምደዬ አያሌው አንዳንድ “የጥቅም ግጭት ቢኖርም በዚህ ምርመራ ከቦይንግ ኩባንያ፣ ከአሜሪካው ፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር፣ ከብሔራዊ ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ ፣ ከፈረንሳዩ የአዉሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ጋር ተባብሮ መሰራቱንና የመረጃ ልውውጥ መደረጉም ተዘግቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቦይንግ 737-ማክስ 8 ላይ የተገጠመው ኤምካስ የተባለው ዘመናዊ የአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ላይ የነበረ ችግር አደጋው ለመፈጠሩ መንስዔ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ በሪፖርቱ ላይ በሰጠው አስተያየት፣ የመረጃ ማስተላለፊው አውሮፕላኑ በተነሳበት ጊዜ በአእዋፋት ጉዳት ደርሶበት ሊሆን ይችላል በማለት የኢትዮጵያ የምርመራ ውጤት ይህንን አጋጣሚ ችላ ብሎታል ብሏል።

ነገር ግን በምርመራው ሂደት ይህ ጉዳት መድረሱን የሚያመለክት ምንም አይነት ማስረጃ አለመገኘቱ በሪፖርቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ከአሜሪካ በኩል ደግሞ አደጋው በደረሰበት ስፍራ ፍለጋ ቢደረግም የመረጃ ማስተላለፊያው ክፍል አልተገኘም ብሏል።

በተጨማሪም የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርዱ የኢትዮጵያ መርማሪዎች በአውሮፕላኑ ዲዛይን ላይ ያለው ችግር ለአደጋው ባለው አስተዋጽኦ ላይ በማተኮር በበረራ ሠራተኞቹ ሥልጣና እና በአደጋው ጊዜ የወሰዷቸው እርምጃዎችን ችላ ብሏቸዋል ብሏል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ የምርመራው ውጤት ይፋ በሆነበት ጊዜ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የምርመራ ሪፖርቱ የበረራ ቡድን አባላቱ ብቃት ማሳየታቸውን እንዲሁም የታደሰ ፍቃድ ነበራቸው ብለዋል።

በተጨማሪም አውሮፕላኑ በአየር ላይ ለመብረር በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንደነበርና ሕጋዊ ማረጋገጫም እንደነበረው መረጋገጡንም ተገልጿል። የአውሮፕላኑ ክብደትና እና ሚዛንም በተፈቀደው ልክ ነበር ብለዋል።

ቦይንግ 737- ማክስ 8ን አምርቶ ካወጣ በኋላ ለአደጋው ምክንያት ነው የተባለው የኤምካስ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር መገጠሙ በምስጢር እንደተያዘ እና ለአብራሪዎችም በሥልጠና ማኑዋሎች ላይ እንዳልተካተተ መገለጹ ይታወሳል።

የኢንዶኔዥያ ላየን ኤር አውሮፕላን አደጋ መድረሱም ተከትሎ ኤምካስ መገጠሙ ይፋ እንደተደረገና የኢትዮጵያ አብራሪዎችም አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለውን በቦይንግ የተሰጠውን መመሪያ መከተላቸው ተገልጿል።

ነገር ግን ይህም ሆኖ አውሮፕላኑን በተደጋጋሚ ለመቆጣጠር ቢሞክሩም ሳይታዘዝ ቀርቶ ወደ ምድር አሽቆልቁሎ ተከስክሷል።

በኢትዮጵያው አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ ከወራት በፊት በኢንዶኔዢያ ውስጥ ተመሳሳይ ከተከሰተ በኋላ ሲሆን፣ ለሁለቱም አደጋዎች ምክንያቱ ቦይንግ ለዘመናዊው አውሮፕላን የዘረጋው የበረራ መረጃ መቆጣጠሪያ ሥርዓት መሆኑ በስፋት ሲገለጽ ቆይቷል።

በተለይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ አደጋ ከደረሰ በኋላ በአሜሪካው ግዙፍ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ለማስነሳቱ ባሻገር በቢሊዮን ዶላሮች የሚደርስ ኪሳራን አስከትሎበታል።

እጅግ ዘመናዊ ነው የተባለው ቦይንግ 737 ማክስ-8 አውሮፕላን ለደኅንነት ስጋት በመሆኑ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በመላው ዓለም ከትራንስፖርት አግልግሎት ውጪ ሆነው ቆይተዋል ይታወሳል።

በአውሮፕላኖቹ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ አስፈላጊው ማስተካካያ በቦይንግ ተደርጎ ተገቢው ምርመራ እና ሙከራ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ አየር መንገዶች አውሮፕላኑ ወደ አገልግሎት እንዲመለስ አድርገዋል።

የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ከአዲስ አበባ አውሮፕላን ማሪፊያ ወደ ኬንያ ለማቅናት በተነሳ በስድስት ደቂቃ ውስጥ ተከስክሶ ከ35 አገራት ተሳፍረው የነበሩ መንገደኞች ሕይወት መቅጠፍ ምክንያት ሆኗል።