የኢትዮጵያ እና የኬንያ አየር መንገዶች ምንና ምን ናቸው?

የኢትዮጵያ እና የኬንያ አየር መንገዶች አርማ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‘በአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ’ የሚል ስያሜን በተከታታይ ዓመት ሲያገኝ ቆይቷል።

አየር መንገዱ የአፍሪካ ሃገራትን ከእስያ ጋር በማገናኘት ተወዳዳሪ የሌለው ሲሆን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውንም ታሪክ እየቀየረ ይገኛል።

በአህጉሪቷ ሌላ ትልቅ ስም ያለው የኬንያው አየር መንገድም ራሱን ‘የአፍሪካ ኩራት’ ብሎ ይጠራል።

ሁለቱ አየር መንገዶች በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአህጉሪቷ ትልቅ ስፍራ አላቸው።

ሁለቱ ጎረቤት አገራት በአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ መሪ ሆነው ቆይተዋል።

ሆኖም በባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተከታታይ አንደኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ እና በአትራፊነት ቀዳሚ ሆኖ ዘልቋል።

በ2021 ሦስተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የኬንያ አየር መንገድ፣ በሞሮኮው የአየር መንገድ ኤይር ማሮክ እና በደቡብ አፍሪካ የአየር መንገድ በ2022 ተበልጦ በአራተኛ ስፍራ ላይ ተቀምጧል።

ስካይትራክስ የዓለም ምርጥ 100 አየር መንገዶችን ይፋ ባደረገበት በዚህም ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንደኛነቱን አስጠብቋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኬንያ አየር መንገድ በዓለም አቀፉ መድረክ የተሰጠው ደረጃ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከምርጥ ሰላሳዎቹ አንዱ በመሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው ደረጃ ከፍ በማለት 26ኛ ስፍራ ላይ ተቀምጧል።

የኬንያ አየር መንገድ በበኩሉ 81ኛ ደረጃ ስፍራ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ የኤይር ማሮክ 66ኛ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ደግሞ 79ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ስካይትራክስ ከ350 በላይ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችን የአገልግሎት ጥራትም በተመለከተ የደንበኞች የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ነው ደረጃውን የመደበው።

የኳታር አየር መንገድ ከአውሮፓውያኑ 2001 ጀምሮ ለሰባት ጊዜ በቀዳሚነት በማሸነፍ የዓለማችን ምርጡ አየር መንገድ ተብሏል። 

የኢትዮጵያና የኬንያ አየር መንገድ ምንና ምን ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኬንያ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዓመታት ቀዳሚ ለመሆን ፉክክር ቢያሳዩም ያለፉት ዓመታት የአፍሪካ አቪዬሽን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበላይነት መቀየሩን ያሳየ ነው።

ለምሳሌ የአፍሪካ አየር መንገዶች በአውሮፓውያኑ 2019 ምን ያህል መንገደኞች እንዳጓጓዙ ስናይ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 13.3 ሚሊዮን፣ የኬንያ 4.9 ሚሊዮን እና የደቡብ አፍሪካ 4.6 ሚሊዮን መሆኑን ከሩትስ ኦንላይን የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ነገር ግን ዘጠኝ ዓመታትን ወደኋላ ሄደን በአውሮፓውያኑ 2010 የነበረውን አሃዝ ብናየው ደቡብ አፍሪካ ስምንት ሚሊዮን መንገደኞችን ሲያጓጉዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ ከሦስት ሚሊዮን ትንሽ ላቅ ያለ ነበር

የኬንያ አየር መንገድ የተመሰረተው የምስራቅ አፍሪካው አየር መንገድ በተበተነበት በአውሮፓውያኑ 1977 ነበር። መዳረሻዎቹንም ሆነ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር በ80ዎቹ በመጨመር አየር መንገዱ መስፋፋቱን ተያያዘ።

በ1990ቹ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተለየ አቅጣጫን በመከተል የተወሰነ ድርሻውን ወደ ግል አዛውሮ እስከ አውሮፓውያኑ 2012ም በፍጥነት ማደግ ያሳየ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያም አየር መንገድ የላቀ የመንገደኞች ቁጥር ነበረው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድፍረት የተሞላበት የማስፋፊያ ዕቅድ በጥሩ ሁኔታ ሲሄድ፣ እያደገ የነበረው የኬንያ አየር መንገድ ችግር ገጠመው።

ከፍተኛ ወጪ፣ የነዳጅ ግዢው ዕቅድ እና ከአንደኛው ባለ ድርሻ ኬኤልኤም ጋር የነበረው ችግር ለኬንያው አየር መንገድ መውደቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጅማሮ አገሪቱን ለማዘመን ከተያዘው ዕቅድ ጋር የሚገናኝ ሲሆን፣ ወቅቱም በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1945 ነው።

አየር መንገዱ ከተቋቋመ በኋላ በነበሩት አስር ዓመታት ከፍተኛ መስፋፋት እና ዕድገትን ያሳየ ሲሆን፣ ከአሜሪካው ትራንስ ወርልድ አሊያንስ አየር መንገድ እንዲሁም ከአሜሪካው ኤክዚም ባንክ ድጋፍ እንደነበረው መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 አውሮፕላንን በማዘዝ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አየር መንገድ ሲሆን፣ አሁን ያለበትን መመንደግ የታየውም በአውሮፓውያኑ 2005 እንደሆነ የአቪዬሽን ተንታኞች ይናገራሉ።

ሆኖም በወቅቱ አየር መንገዱ ከኬንያ፣ ከደቡብ አፍሪካም ሆነ ከግብፅ አየር መንገዶች አንጻር ደረጃው ዝቅ ያለ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2010 የመንገደኞቹን ቁጥር ወደ ሦስት ሚሊዮን የማሳደግ ዕቅድን በመያዝ ማሳካት ብቻ ሳይሆን የያዘውንም ዕቅድም አለፈ።

ዓመታትን ተሻግረን በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ በመንገደኞች ብዛት፣ በመዳረሻዎች እንዲሁም በትርፋማነቱ ስኬታማ ሆኗል።

በአውሮፓውያኑ 2025 ወደ 18 ሚሊዮን መንገደኞችን የማጓጓዝም ዕቅድ እንዳወጣ ተዘግቧል።

አየር መንገዱ በሌሎች አፍሪካ አገራት አየር መንገዶች ውስጥም ድርሻዎችን በመግዛት የአህጉሪቷ ቁንጮ የአየር ትራንስፖርት ሰጪ ግዙፍ ተቋም ለመሆን ችሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስተዳደር ሚና ወይም በስትራቴጂክ አጋርነት ስድስት የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን ለማነቃቃት እየሰራ ይገኛል።

በማላዊ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ ኢንቨስት ከማድረግ በተጨማሪ፣ አስካይ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ሞዛምቢክ አየር መንገድ እና የዛምቢያ አየር መንገድ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች ትብብርን እየተመለከተ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ጀርባ ያሉት አቶ ተወልደና የኬንያ አየር መንገድ

ለዚህ ስኬት ደግሞ አንድ ሰው በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። አየር መንገዱን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ለአስራ አንድ ዓመታት የመሩትና በቅርቡ "በጤና ምክንያት የለቀቁት" አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ናቸው።

በቅርቡም ከኬንያ አየር መንገድ ጋር በተያያዘ ስማቸው እየተነሳም ይገኛል።

በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የተመራው የኬንያ ልዑካን ቡድን በዋሽንግተን ከዴልታ አየር መንገድ ባለሥልጣናት ጋር የኬንያን አየር መንገድን ለመሸጥ በቀረበው ሃሳብ ላይ ሲወያዩ አቶ ተወልደ ከአሜሪካውያኖቹ ጋር ተቀምጠው ነበር።

ለአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት የአንበሳውን ድርሻ የያዙት አቶ ተወልደ፣ በስብሰባው ላይ እንደ እሳቸው የአፍሪካ አቪዬሽንን የሚያውቀው ማንም የለም ብሏል ዘ ኢስት አፍሪካን ባወጣው ጽሑፍ።

የዴልታ አየር መንገድ ከፍተኛ የስትራቴጂ አማካሪ የሆኑት አቶ ተወልደ በሁለቱ አየር መንገዶች መካከል ሊደረግ የሚችለውን ስምምነት እንዲቃናም ሆነ እንዲፈርስ ወሳኝ ሰውም ናቸው በማለት ዘገባው አስፍሯል።

ለዚህ የግብይት ስምምነት ዴልታን የወከሉት አቶ ተወልደ የኬንያን የአየር መንገድ የአፍሪካ ሰማይን የመቆጣጠር ተስፋ የቀበሩ ብሏቸዋል።

በዚህ ድርድር ላይ አቶ ተሳታፊ የነበሩት ተወልደ ሲመሩት የነበረው የኢትዮጵያን አየር መንገድ ያጓጓዛቸው መንገደኞች በአውሮፓውያኑ 2021 ከ7 ሚሊዮን በላይ ሲሆን የኬንያ አየር መንገድ 1.5 ሚሊዮን ነበር።

ፕሬዝዳንት ሩቶ በአሜሪካ- አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ በግማሽ ዓመቱ 80 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የከሰረውን የአገራቸውን አየር መንገድ ለመሸጥ ፍላጎት እንዳላቸው ማስታወቃቸውን የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ባለፉት ሳምንታት ሲዘግቡ ቆይተዋል።

ይህ ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ ዴልታ በኬንያ አየር መንገድ የመንግሥት ድርሻ የሆነውን 48.9 በመቶ የሚቆጣጠር ይሆናል፤ ይህም በውጭ አየር መንገድ ውስጥ በአሜሪካ አየር መንገድ ትልቁ የአክሲዮን ድርሻ ይሆናል።

ሌሎቹ ባለድርሻዎች ደግሞ የአገር ውስጥ አበዳሪዎች ጥምረት 38.1 በመቶ፣ ኤይር ፍራንስ እና ኬኤልኤም 7.8 በመቶ እና አናሳ ባለድርሻዎች ደግሞ ሁለት በመቶ ይኖራቸዋል።

ነገር ግን የኬንያ መንግሥት ሙሉ ድርሻውን ወይስ የተወሰነውን ነው የሚሸጠው የሚለውን ለማወቅ ጊዜው ገና ነው።

ሆኖም የትኛውንም ድርሻ ይሁን የኬኪውን ድርሻ የሚወስኑት የግብይት አማካሪዎቹ ይሆናሉ።

በአሁኑ ወቅት አቶ ተወልደ በዴልታ ያላቸው ስፍራ የኬኪውን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ሲሆን፣ አየር መንገዱ ያለበትን ብድር ከፍሎ ወደ ትርፋማነት መንገድ ያመራ ይሆን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድስ ጋር ተፎካካሪ ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በቀጣይ በሚደረገውም ስምምነት የሚመለስ ይሆናል።

ባለፉት 11 ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድን በበላይነት የመሩት አቶ ተወልደ አየር መንገዱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ወደ 4.5 ቢሊዮን ገቢ፣ ከ33 አውሮፕላኖች ወደ 140 እንዲሁም ከወረርሽኙ በፊት 12 ሚሊዮን መንገደኞችን ወደ ማጓጓዝ እንዲያድግ አድርገውታል።

አየር መንገዱ ከ700 ሚሊዮን በላይ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ የአቪዬሽን አካዳሚ እና ሌሎችንም ማሳካት ችሏል።

በተጨማሪም በእሳቸው አመራር ከኤምሬትስ አየር መንገድ በመብለጥ በእስያ እና በአፍሪካ እንዲሁም በአፍሪካ አገራት መካከል ግዙፉ አገናኝ አየር መንገድ ለመሆን ችሏል።

በመንገደኞች ብዛት እና በአውሮፕላን ቁጥርም፣ ከፍተኛ ትርፍ ማግኘትም፣ የመበደር አቅሙም ሆነ የካርጎ አገልግሎቱም ያደገው በእሳቸው አመራር ወቅት ነው።

በተለይም በወረርሽኙ ያሳዩት አመራርና ስትራቴጂ አድናቆትን አትርፎላቸዋል።

የኬንያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች

የፎቶው ባለመብት, Kenya Airways

የአየር መንገዶቹ ከወረርሽኙ በኋላ ያለው ጉዞ

የቦይንግ 737 ማክስ ስምንት አደጋ እንዲሁም የኮሮኖቫይረስ ወረርሽኝ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ዓመታት መጥፎ ጥላን ቢያጠሉበትም ከፍተኛ ትርፍ ከማግኘት ግን አላደናቀፉትም።

ያለፈው በጀት ዓመትን በምናይበት ወቅት 79 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ትርፉ ደግሞ 90 በመቶ እንዲሁም ጭማሪ በማሳየት 937 ሚሊዮን መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን ዋቢ አድርጎ ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቦ ነበር።

የአየር መንገዱ ስኬት “በዓለም ላይ ያለው የምጣኔ ሀብት ቀውስ መባባስ፣ የነዳጅ ዋጋ መናር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ” ባለበት ወቅት መሆኑንም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማሞ ምህረቱ በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው አስፍረው ነበር።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በዋነኝነት ይጠቀሳል።

በዚህም ከተጎዱት በአፍሪካ ተወዳዳሪ ከሆኑት የደቡብ አፍሪካና የኬንያ አየር መንገዶች ይጠቀሳሉ። ወረርሽኙ ያስከለተው ቀውስ ሳይቀረፍ የዩክሬን ጦርነት መነሳቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር እንዲሁም አየር መንገዶቹ በነበራቸው ቀውስ ላይ እንዲንኮታኮቱ ምክንያት ሆኗል።

የኬንያ አየር መንገድን (ኬኪው) ስናይ ባለፈው ዓመት እስከ ሰኔ በነበሩት ስድስት ወራት ብቻ 82 ሚሊዮን ዶላር ከስሯል፤ ከዚያ በፊት በነበረው ስድስት ወር ደግሞ 95 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ማሳየቱ ተነግሯል።

የኬንያ አየር መንገድ ለዓመታት እየተንገታገተ ሲሆን፣ መንግሥትም ተቋሙን ከዚህ ቀውስ ለማውጣት ከቅርብ ቀናት በፊት 34.95 ቢሊዮን ሺልንግ (283.7 ሚሊዮን ዶላር) ድጎማ እንደሚያደርግ ተዘግቧል።

ይህም በኪሳራ ላይ ያሉ ድርጅቶችን ትርፋማ ለማድረግ ግፊት እያደረገ ያለው የአይኤምኤፍ ጫና አካልም ነው ተብሏል።

የኬንያ አየር መንገድ በዚህ ኪሳራ ላይ በዕዳ መዘፈቁም ተነግሯል።

የኬንያ መንግሥት ለመጪው ዓመት ካቀደው ድጎማ በፊትም መስከረም ወር ላይ አየር መንገዱ ዕዳውን ለማቅለል ይረዳው ዘንድ 81.2 ሚሊዮን ዶላር ከግምጃ ቤቱ ተቀብሏል።

ኬኪው ለአውሮፕላን አከራዮች፣ ለጥገና፣ ለነዳጅና፣ ለግብርና ለሌሎች ወጪዎች 357 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅበታል። የኬንያ ግምጃ ቤት ለአየር መንገዱ የሰጠው ድጎማ ኪሳራውን በመቀነስ ረገድ ፍሬያማ ሆኗል ብሏል።

አየር መንገዱ በተጨማሪ ኪሳራ እያስከተሉብኝ ነው ያላቸውን 12 በረራዎች ያቆመ ሲሆን በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃም ወደ 16 መዳረሻዎች የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡንም መረጃዎች ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት እና ለመስፋፋት ባቀደበት ወቅት የኬንያ አየር መንገድ ኪሳራውን ለመቀነስ የያዘው አቅጣጫ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር መቀነስ ነው።

በዚህም አንዳንድ የአውሮፕላኖችን የሊዝ ውል እንደሚያቋርጥም ተገልጿል። በተጨማሪም የሠራተኞችን ቁጥር መቀነስን ጨምሮ ጥገና፣ የነዳጅ እና ሌሎች ወጪዎችንም ለመቆጠብ አቅዷል።

በተቃራኒው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰሞኑ ከአሜሪካው ኤክዚም ባንክ 688 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጸድቆለታል። የአሜሪካው ኢምፖርት ኤክስፖርት የዳይሬክተሮች ቦርድ በሙሉ ድምጽ ያጸቀዱት ይህ ብድር በሁለት ዙር የሚለቀቅ ይሆናል።

የመጀመሪያው ዙር፣ 281 ዶላር ሲሆን አየር መንገዱ የተወሰኑ አውሮፕላኖች መስከረም ወር መረከቡም ተገልጿል። አየር መንገዱ ከኤክዚም ባንክ ብድሩን የወሰደው 26 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን በዓመታት ለመግዛት እንዲያስችለው መሆኑም ተነግሯል።

የኬንያ አየር መንገድ በአፍሪካ ውስጥ ካሉት እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የደቡብ አፍሪካ እና ኤይር ፍራንስ ካሉት ውድ በሆነ ዋጋ ቲኬት እንደሚያስከፍል አንድ ጥናት አመላክቷል።

24 የአፍሪካ አገራትን የሚወክሉ የዘርፉ ባለሥልጣናት ባደረጉት አዲስ ጥናት የኬንያ አየር መንገድ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ በረራዎች ከፍተኛውን ዋጋ እንደሚያስከፍል ይፋ አድርገዋል።

ግኝቱ አየር መንገዱ እንደ የኢትዮጵያ እና ወደ ገበያው በቅርቡ የተቀላቀለው የኡጋንዳ አየር መንገድ ተመጣጣኝ የቲኬት ዋጋ በሚያቀርቡ አየር መንገዶች የገበያውን ድርሻ ሊያጣ እንደሚችልም ጠቁሟል።

ለአየር መንገዱ ከወረርሽኙም ሆነ ከዩክሬን ጦርነት ካስከተለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሬ በፊት በነበረው የአመራር ችግር ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

በአውሮፓውያኑ 2015 የአገሪቱ የሴኔት ኮሚቴ ምርመራ እንዳሳየው አውሮፕላኖችን ለመግዛት እና ለመከራየት የነበረው የኢንቨስትመንት ውሳኔ የደከመ መሆኑን ነው።

ለአየር መንገዱ ሌላኛው መውረድ የተጠቀሰው ፊውል ሄጂንግ (ነዳጅን በዋጋ ገደብ የመግዛት ስምምነት) ትርፋማ ያልሆነ መንገድ እንዲከተል ማድረጉንና፤ በዚህም ወደ ከፍተኛ ዕዳ እንዲገባ ምክንያት መሆኑም ተጠቅሷል።

በወቅቱም ውድ ቲኬቶችን የሴኔት ኮሚቴው ቢጠቅስም፣ ደንበኞቹ ወደ ተፎካካሪዎቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች አየር መንገዶች ቢዞሩም አየር መንገዱ ክፍያውን መቀነስ አልቻለም ተብሏል።

ምርመራው የኬኪው ውድ ቲኬት በገበያው ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆን እንዳደረገውና በዚህም መንገደኞችን እንዲሁም ገቢውን እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ካለበር ቀውስ ለመውጣት የኬንያ መንግሥት ድርሻውን ለአሜሪካው ዴልታ አየር መንገድ ለመሸጥ እየተደራደረ ሲሆን ለተፎካካሪው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ተጠሪ የሆኑት አቶ ተወልደ ዕጣውን የሚወስኑ ይሆናል ተብሏል።