የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጓዦች ቁጥር ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ መጨመሩ ተገለጸ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, ethiopian

የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞች ቁጥር ከዓለም አቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ጭማሪ ማሳየቱን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ኩባንያው የበጀት ዓመቱ ሰኔ 2015 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ የተጓዦች ቁጥር ወረርሽኙ ከመከስቱ በፊት ወደነበረበት ይመለሳል ብለዋል።

ሮይተርስ አቶ መስፍን ጣሰውን ጠቅሶ እንደዘገበው አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 12.7 ሚሊዮን መንገደኞችን አጓጉዛለሁ ብሎ ይጠብቃል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ዓመት 8.6 ሚሊዮን ሰዎችን ያጓጓዘ ሲሆን፣ የኮሮናቫይረስ ከመቀስቀሱ በፊት ደግሞ ያጓጓዛቸው የደንበኞቹ ቁጥር 12.1 ሚሊዮን ነበር።

ዓለም አቀፍ ስጋት የነበረው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ የሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስን አስከትሎ የነበረ ሲሆን በተለይ ደግሞ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ጉዳትን አስከትሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በወረርሸኙ ስርጭት ወቅትም የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ወደ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች በመቀየር በመንገደኞች መቀነስ ያጣውን ገቢ ማካካስ ችሏል።

ሮይተርስ በዘገባው ከወረርሽኙ በኋላ አየር መንገዱ የተጓዦቹን ቁጥር ከፍ ማድረግ አስችለውታል ያላቸውን ምክንያቶች የኩባንያውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጠቅሶ ዘግቧል።

አየር መንገዱ አዳዲስ አውሮፕላኖች መግዛቱ፣ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን መጨመሩ እና የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ለማብቃት የሰላም ስምምነት መፈረሙ ለስኬቱ እንደምክንያት ተጠቅሰዋል።

ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 141 አውሮፕላኖች አሉት።

ከእነዚህ መካከል እጅግ ዘመናዊ እና ግዙፍ የሆኑት 19 ኤርባስ ኤ350-900 እና 19 ቦይንግ ቢ787-8 እና 8 ቦይንግ ቢ787-9 የመንገደኞች አውሮፕላኖች ይገኙበታል።

ዘመናዊዎቹን 4 ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላኖችን ጨምሮ 21 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ደግሞ አንዲቀርቡለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

አየር መንገዱ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከአሜሪካው ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ኦፍ ዘ ዩናይትድ ስቴትስ የጠየቀው ብድር ዋስትና በዚህ ሳምንት ሊፈቅድለት እንደሚችል የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዋና ሥራ አስኪያጁን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

አየር መንገዱ ባንኩን የጠየቀው የብድር ዋስትና በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ በነበረው የርስ በርስ ጦርነት እና በፖለቲከኞች ጫና ምክንያት መዘግየቱን መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የብድር ሂደቱን የማጽደቅ ሂደት መጀመሩን እና በተያዘው ሳምንት ፍቃዱ ሊገኝ እንደሚችል ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN AIRLINES

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አየር መንገዱ ለስኬቱ እንደ ምክንያት የተጠቀሰው ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን መጨመሩ ነው።

ኩባንያው በአውሮፓውያኑ 2035 የአውሮፕላን ቁጥሮችን እና መዳረሻዎችን ከፍ በማድረግ ዓመታዊ ገቢውን በ400 ፐርሰንት እንዲሁም የተጓዦቹን ቁጥር ደግሞ በ440 ፐርሰንት የመጨመር ዕቅድ እንዳለው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርብ ከጀመራቸው ወይም ከሚጀምራቸው አዳዲስ መዳረሻዎች መካከል የስዊትዘርላንዷ ዙሪክ፣ ሕንዷ ቺናይ፣ ጆርዳን አማን እና የዚምባብዌዋ ቡላዋዮ ተጠቃሽ ናቸው።

ከወራት በኋላ ደግሞ ወደ ሲንጋፖር የሚያደርገውን የቀጥታ በረራ ዳግም ይጀምራል።

“በተመሳሳይ ጊዜ የመንገደኞች ቁጥር እና የዕቃ ጫኝ በረራዎችን እየጨመርን ነው” ሲሉ ለዜና ወኪሉ የተናገሩት መስፍን፤ የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ አገራት ጥለው የነበሩትን የጉዞ ገደቦችን እያላሉ እና እያነሱ በሄዱ ቁጥር የመንደኖች ቁጥር እንዲጨምር ይፈቅዳል ሲሉ ተናግረዋል።

የ2022 የስካይትራክስ የዓለም አየር መንገዶች ውድድር ላይ በርካታ ሽልማትን የተቀበውለው አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ፤ ኩባንያው ካላደገ በቅር ተልዕኮውን ማሳካት አይችልም ያሉ ሲሆን ይህን ለማድረግም የአየር መንገዱን ኦፕሬሽን ማስፋፋት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ መንገደኞችምን ይሁን የዕቃ ማጓጓዝ ሥራ ላይ ቁልፍ መዳረሻ በሆነችው ቻይና የአገሪቱ መንግሥት የኮቪድ ስርጭትን ለመቆጣጠር ሲባል እየተገበራቸው ያሉት ጥብቅ ቁጥጥሮች ለአየር መንገዱ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ተመላክቷል።

ከሦስት ወራት በፊት በተካሄደው የስካይትራክስ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ አየር መንደጉ ለተከታታይ አምስት ዓመታት የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ፣ የአፍሪካ ምርጥ ቢዝነስ ክላስ፣ የአፍሪካ ምርጥ የኢኮኖሚ ክለስ ተብሎ ተመርጧል።