ኤሎን መስክ የሚተካኝ ሳገኝ ከትዊተር ኃላፊነቴ እለቃለሁ አለ

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኤሎን መስክ “ሥራውን ለመረከበር ፍቃደኛ የሚሆን ሞኝ የሆነው ሰው ሳገኝ” ከትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚነት እለቃለሁ አለ።

ቢሊየነሩ የትዊተር ባለቤት ቀደም ሲል ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያስባሰበው የሕዝብ አስተያየት ከዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲነስ የሚጠይቅ ነበር።

መስክ ከሁለት ቀናት በፊት ከትዊተር ኃላፊነቱ መነሳት እንዳለበት ተከታዮቹን የጠየቀ ሲሆን፣ ውጤቱንም እንደሚያከብር ገልጾ ነበር።

122 ሚሊዮን ተከታዮቹ ባሉት የትዊተር ገጹ ባቀረበው የሕዝብ አስተያየት መለኪያ ጥያቄ “ከትዊተር ኃላፊነቴ መልቀቅ አለብኝ? ይህን የሕዝብ አስተያየት ውጤት አከብራለሁ” ሲል ጽፎ ነበር።

ታዲያ 17.5 ሚሊዮን የትዊተር ተጠቃሚዎች ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 57.5 በመቶ የሚሆኑት ኃላፊነቱን የመልቅ ሃሳብን ደግፈዋል።

በዚህ መሠረት መስክ እርሱን የሚተከ ሰው ከተገኝ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነቱን ለቅቆ የሶፍትዌር እና ሰርቨር ቡድንን እንደሚመራ ገልጿል።

የዓለማችን ቁጥር ሁለት ባለጸጋ ማኅበራዊ ሚዲያውን በ44 ቢሊዮን ዶላር ከገዛ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያው አጠቃቀም ዙሪያ እያስተዋወቃቸው ባላቸው ፖሊዎች እየተተቸ ይገኛል።

መስክ ትዊተርን የግሉ ካደረገ በኋላ ግማሽ ያክል ሠራተኞችን ቀንሷል እንዲሁም የሰዎች እና ተቋማት ትክክለኛ ገጾች መለየ የሆነው ሰማያዊ ምልክት ከእንግዲህ ወዲያ ወራሃዊ ክፍያ ይጠየቅበታል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ለማስተዋወቅ ብቻ የተከፈቱ የትዊተር አካውንቶችን እዘጋለሁም ብሏል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

ትዊተር እየተመራ ያለበት ሁኔታ ያላስደሰታቸው የተባበሩት መንግሥት እና የአውሮፓ ኅብረት ጭምር ማስጠንቀቂያዎችን አውጥተዋል።

ተመድ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት “መጫወቻ አይደለም” ሲል የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ ትዊተር ላይ ማዕቀብ እጥላለሁ ሲል አስፈራርቷል።

መስክ ሥልጣኑን እንዲለቅ ከጠየቀው የሕዝብ አስተያያት በኋላ ትዊተርን መምራት የሚፈልግ ሰው አይኖርም ሲል በትዊተር ገጹ ጽፏል።

እስካሁን ድረስ መስክ በማን ሊተከ እንደሚችል የተባለ ነገር ባይኖርም፣ አንዳንዶች ግን ግምታቸውን እየሰነዘሩ ይገኛሉ።

ከእነዚህም መካከል የቀድሞ የፌስቡክ ሥራ አስኪያጅ ሼርለይ ሳንድበርግ፣ የመስክ የቅርብ ጓደኛ የሆነው ስሪራም ክሪሽናን እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አማካሪ እና የትራምፕ ልጅ ባለቤት የሆነው ጃሬድ ኩሽነር ይገኙበታል።