አዲሶቹ አጥፍቶ ጠፊ ‘ካሚካዚ’ ድሮኖች በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ሚናቸው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያ ጦር በኪዬቭ ከተማ ባሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ተጠቅማለች ስትል ዩክሬን ትከሳለች።
እነዚህ ድሮኖች ጉዳት የሚያደርሱት ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዞ በመብረር ከዒላማቸው ጋር እየተላተሙ በሚፈጥሩት ፍንዳታ ነው።
ካሚካዚ በሚባል የሚታወቁት አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች በአንድ ጊዜ ብዙ ሆነው ጥቃት ለማድረስ ስለሚነሱ ለመከላከል ከባደ ናቸው።
የሩሲያው ካሚካዚ ድሮን ምንድነው?
የሩሲያ ጦር ባለፉት ወራት ኢራን ሰራሽ ሻሂድ-136 ድሮኖችን በዩክሬን ጦርነት ሲጠቀም መቆየቱ ይገመታል።
ሩሲያ ጌራኒየም-2 ብላ የምትጠራው ይህ ድሮን ተቀጣጣይ ነገር ከፊተኛው አካሉ ላይ በመያዝ ጥቃት እንዲፈጽም ትዕዛዝ እስኪሰጠው ድረስ ዒላማው ላይ በመሸከርከር ይቆያል።
ሻሂድ-136 ድሮን 2.5 ሜትር የሚረዝም ክንፍ ያለው ሲሆን ከራዳር ውጪ ሆኖ የመብረር አቅም አለው።
ሩሲያ እነዚህን ድሮኖች በቁጥር ስንት እንዳላት በግልጽ ባይታወቅም አሜሪካ ግን ኢራን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሻሄድ-136 ድሮኖችን ለመላክ አቅዳለች ትላለች።
ኢራን በበኩሏ ድሮኖችን ለሞስኮ እንዳላቀረበች አስተባብላለች።

የፎቶው ባለመብት, DRONEUA
ካሚካዚ ድሮኖች ምን ጉደረሱ?
ሩሲያ እነዚህን ድሮኖች መስከረም መጀመሪያ ላይ ኻርኪቭ በተሰኘችው የዩክሬን ግዛት ላይ ጥቅም ላይ አውላለች።
ባለፈው ወር ደግሞ እነዚህ ድሮኖች በደቡብ ዩክሬን ጥቃት ለመሰንዘር ጥቅም ላይ ውለዋል። የድሮኑ ስብርባሪ በኦዴሳ እና ማይኮሌይቭ ውስጥ ተገኝቷል።
ከአንድ ሳምንት በፊት የዩክሬን ባለሥልጣናት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሻሂድ ድሮኖች መትታ መጣሏን ገልጻ ነበር።
ተንታኞች እንደሚሉት ሩሲያ ከረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ይልቅ እነዚህን ድሮኖች መጠቀም የመረጠችው ዋጋቸው ያነሰ ስለሆነ ነው ይላሉ።
ካሚካዚ ድሮኖች እያንዳንዳቸው እስከ 20 ሺህ ዶላር ያወጣሉ።

ዩክሬን እራሷን እንዴት እየተከላከለች ነው?
የዩክሬን መከላከያ ኃይል ድሮኖቹን በነፍስ ወከፍ ጦር መሳሪያ፣ በከባድ መሳሪያ፣ በተንቀሳቃሽ ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ በመምታት እና ከቁጥጥር ውጪ [ጃም] እንዲሆኑ በማድረግ እየተከላከለ ነው።
የዩክሬን ኃይሎች ከሁለት ወራት በፊት በ36 ቀናት ውስጥ 223 ሻሂድ-136 ድሮኖችን መትተው ስለመጣላቸው ገልጸው ነበር።
ይሁን እንጂ እራሳቸውን አጥፍተው ዒላማቸውን ለመምታት በከፍተኛ ቁጥር የሚመጡ ድሮኖችን ሙሉ በሙሉ መትቶ መጣል እጅግ አዳጋች ነው።
“ዝቅ ብለው ይበራሉ። እንደ ማዕበል በአንድ ላይ መላክ ይቻላል። እነዚህ ድሮኖች በአየር ኃይል መከላከል በጣም ከባድ ነው” በማለት የጦር ባለሙያው ጀስቲን ክራምፕ ለቢቢሲ አስርድተዋል።
ዩክሬንስ ካሚካዚ ድሮን ተጠቅማለች?
ዩክሬን እነዚህን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ስለመጠቀሟ የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁን እንጂ አሜሪካ እራሷ ያመረተቻቸውን 700 ስዊችብሌድ ካሚካዚ ድሮኖች ለዩክሬን እንደምትልክ አስታውቃ ነበር።
ባለሙያዎች እነዚህ ድሮኖች በቅርብ ጊዜ በተካሄዱ ጦርነቶች ላይ ጥቅም ላይ ሳይውሉ አይቀሩም ይላሉ።
ዒላማቸው ደግሞ በምዕራብ ክሬሚያ የሚገኝ የሩሲያ ጦር ሰፈር እና ሌላ አየር ማሪፈያ ይገኝበታል።
በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የመከላከያ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ማሪና ሚሮን ከድሮኖቹ መጠን እና ከሚፈጥሩት ፍንዳታ አንጻር በቀላሉ የሚሰሩ እና መጠናቸውም አነስተኛ መሆኑን ማወቅ ይቻላል ብለዋል።

ዩክሬን እና ሩሲያ ሌላ ምን አይነት ድሮን አላቸው?
የዩክሬን ዋነኛው ድሮን ቱርክ ሰራሹ ባይራክታር ቲቢ2 ነው። የዚህ ድሮን መጠን ከትንሽ አውሮፕላን ጋር ይስተካከላል። ካሜራ የተገጠመለት ሲሆን ጨረር ተከትሎ ቦምብ መጣል የሚችል ቴክኖሎጂም አለው።
የዘርፉ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ጃክ ዋትሊንግ ዩክሬን ከ50 ያነሱ ባይራክታር ቲቢ2 ድሮኖች ያሏት ይላሉ። አሜሪካ 700 ስዊችብሌድ ድሮኖችን እልካለሁ በማለቷ ዩክሬን ካሚካዚ ድሮኖችን ስለመታጠቋ ይታመናል።
ሩሲያ ደግሞ “መሠረታዊ እና በመጠን አነስተኛ የሆነ” ኦርላን-10 የተባለ ባለ ካሜራ እና ቦምብ መሸከም የሚችል ድሮን አላት።
የጦር ድሮኖች ጥቅም እንዴት ይውላሉ?
ለሁለቱም ወገን- ለሩሲያም ሆነ ለዩክሬን የጠላትን ቦታ ለማወቅ እና የከባድ ጦር መሳሪያ አረሮችን ወደ እነርሱ አቅጣጫ ለመተኮስ የድሮኖች ጥቅም ከፍ ያለ ነው።
ዶ/ር ዋትሊንግ የሩሲያ ጦር ኦርላን-10 የተባለውን ሰው አልባ አውሮፕላን በመጠቀሙ በጠላት ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት ፍጥነት እንዲጨምር ማስቻሉን ይናገራሉ።
ዶ/ር ማሪና ሚሮን የዩክሬን ጦር ያለውን የተገደበ ሃብት አስፍቶ እንዲጠቀም አስችሎታል ይላሉ። ሃሳባቸውን ሲያስረዱ፤ “ከዚህ ቀደም የጠላት መገኛ ቦታን ለመለየት ሰላይ የሆኑ የልዩ ኃይል አባላትን መላክ ግድ ይሆን ነበር፤ . . . በዚህ መካከል ወታደር ሊገደል ይችላል። አሁን ግን አደጋ ላይ የሚወድቀው ድሮን ብቻ ነው” ይላሉ።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በተጀመረ የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ቱርክ ሰራሹ ባይራክታር ቲቢ2 ድሮን ብዙ ተወድሶ ነበር። ዶ/ር ሚሮን የሩሲያዋ ጦር መርከብ ሞስኮቫን መትቶ በማስመጥም እነዚህ ድሮኖች አስተዋጽኦ ነበራቸው ይላሉ።
ይሁን እንጂ ባይራክታር በመጠኑ ትልቅ እንዲሁም ከሌሎቹ ጋር ሲነጻጸር ፍጥነት የሌለው ዝግ ብሎ የሚበር ነው። በዚህም ምክንያት የሩሲያ አየር ኃይል እነዚህን ድሮኖች ጥሩ አድርገው መከላከል ችለዋል በማለት ያስረዳሉ።

የጦር ያልሆኑ ድሮኖች ለጦርነት እንዴት ይውላሉ?
አብዛኞቹ ወታደራዊ ድሮኖች ዋጋቸው የሚቀመስ አይደለም። ለምሳሌ ባይራክተር ቲቢ2 ወጪው ሁለት ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ይጠይቃል።
በዚህም ምክንያት በሁለቱም ወገን ያሉት በተለይ ደግሞ ዩክሬን አስተኛ እና ከገበያ መግዛት የሚቻል ድሮንን ለጦር ሜዳ አገልግሎት እያዋሉት ይገኛሉ።
በተለይ ደግሞ ዲጂአይ ማቪክ 2 የተበላው እና 2ሺህ ዶላር ገደማ የሚሸጠው ድሮንን ሁለቱም አገራት ጥቅም ላይ እያዋሉት ነው።
እነዚህ ድሮኖች ላይ አነስተኛ ቦምብ መግጠም ይቻላል፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉት የጠላትን አቅጣጫ ለመለየት እና ለማስተኮስ ነው።
“ዩክሬን ሩሲያ ያላትን ያክል ተተኳሽ የላትም” የሚሉት ዶ/ር ሚሮን፤ “ከሰማይ ላይ ሆኖ የማየት አቅም መኖር ዒላማን በቀላሉ መለየት ያስችላል፤ ጠላት ወዳለበት አቅጣጫ መተኮስ ያላቸውን በአግባቡ መጠቅም እንዲችሉ ያደርጋል” ይላሉ።
ይሁን እንጂ እነዚህ ማንም ሊገዛቸው የሚችሉት ድሮኖች አቅም ከወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጋር ሊነጻጸር አይችልም።
ለምሳሌ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው ዲጂአይ ማቪክ 2 ለ46 ደቂቃዎች ብቻ መብረር የሚችል ሲሆን፣ ሊሸፍን የሚችለው ርቀት ደግሞ 30 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው።
ሩሲያ ደግሞ እነዚህን ድሮኖች ለመከላከል ኤሌክትሮኒክ ቁሶችን እየተጠቀመች ትገኛለች። “ሩሲያ ኤሌክትሮማግኔቲክ ለይቶ የሚመታ ስቱፖር መሳሪያ አላት። ይህ ከገበያ የሚገዙ ድሮኖችን ጂፒኤስ ተጠቅመው እንዳይቀሳቀሱ ያግዳል” በማለት ያስረዳሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ሩሲያ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም በድሮኖች እና በማዘዣ ጣቢያ ከሚገኙ ኦፕሬተሮች ጋር ያለን ግንኙነት በማቋረጥ እራሷን ትከላከላለች።
ይህም የሰው አልባ አውሮፕላኖቹን ግንኙነት በማቋረጧ ከዒላማው ሳይደርስ እንዲከሰከስ አልያም ወደ ማዛዠ ጣቢያው እንዲመለስ ያስገድዳል።












