መላውን ዜጎቿን ሊገድል የሚችል ፌንታሊን የተባለ ዕጽ መያዟን አሜሪካን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የዕጽ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እየተጠናቀቀ ባለው 2022 መላውን የአሜሪካ ዜጋ ለመግደል በቂ የሆነ ፌንታሊን የተሰኘ አደገኛ አደንዛዥ ዕጽ መያዛቸውን አስታወቀ።
የዕጽ ቁጥጥር አስተዳደር (ዲኢኤ) በአንዴ እንዲወሰዱ ተደርገው የተዘጋጁ እያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊ ግራም የሚመዝኑ ገዳይ የሆኑ 379 ሚሊዮን ፌንታሊን የተሰኘ ዕጾችን ይዣለሁ ብሏል።
ባለሥልጣኑ እንደሚለው ይህ አደንዛዥ ዕጽ ከሄሮይን 50 እጥፍ በላይ ገዳይ መሆኑን አመልክቶ፣ ፌንታኒል አሜሪካ በአሁኑ ወቅት የገጠማት ገዳይ ስጋት ነው ሲል ገልጾታል።
ኤጀንሲው እንደሚለው ከሆነ ከፍተኛ መጠን ያለው ፌንታሊን ወደ አሜሪካ የሚገባው ከሜክሲኮ ነው።
ዲኢኤ ከ4 ሺህ 500 ኪሎ ግራም በላይ ፌንታሊን እና 50.6 ሚሊዮን በእንክብል መልክ የተዘጋጁ ዕጾችን ይዟል።
ኤጀንሲው እንዳለው በእንክብል መልክ የተዘጋጁት ዕጾች ህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች እንዲመስሉ መደረጋቸውንም ጨምሮ ገልጿል።
እየተጠናቀቀ ባለው በዚህ የፈረንጆቹ ዓመት የተያዘው የዕጽ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል።
በአሜሪካ የሚያዙት ዕጾች በሲናሎዋ እና ጃሊስኮ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች አማካይነት ሜክሲኮ ውስጥ በምስጢራዊ ስፍራ በሚገኙ ፋብሪካዎች በገፍ ይመረታሉ።
ኤጅንሲው እንዳለው ከሆነ ደግሞ ዕጹን ለማምረት ግብዓቱ የሚመጣው ከቻይና ነው።
ፌንታሊን እጅግ አደገኛ የሆነ ዕጽ ሲሆን የእርሳስ ጫፍ ላይ ልትቀመጥ የምትችል ትንሽ መጠን እክኳን የመግደል አቅም አላት።
ባለፈው ዓመት 100 ሺህ አሜሪካውያን ከመጠን በላይ ዕጽ ወስደው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ ከዚህ አሃዝ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ሞት ከፌንታሊን ጋር የተገናኘ ነው።
በዚህ ዓመት የተያዘው ፌንታሊን መጠን 330 ሚሊዮን የአሜሪካ ነዋሪዎች መግደል የሚችል ስለመሆኑ ኤጀንሲው አመልክቷል።
“የዲኢኤ ቀዳሚው ዓላማ በሜክሲኮ ያሉትን ግዙፍ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች - ሲናሎዋ እና ጃሊስኮ ማሸነፍ ነው። ዛሬ ላይ አሜሪካውያን በፌንታሊን እንዲሞቱ ምክንያት እየሆኑ ያሉት እነዚህ ሁለት ቡድኖች ናቸው” ሲሉ የኤጀንሲው አስተዳዳሪ አን ሚልግራም ተናግረዋል።
ከፌንታሊን በተጨማሪ ዲኢኤ 60 ሺህ ኪሎ ግራም ሜታአምፊታሚን እና ወደ 2 ሺህ ኪሎ ግራም ሄሮይን እንዲሁም 200 ሺህ ኪሎ ግራም ኮኬይን መያዙን አስታውቋል።












