የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ ‘የማይቀመስ’ የሆነው ለምንድን ነው? ወደፊትስ ይቀንስ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ መዲና፣ ናይሮቢ የበረሩ ሦስት ተሳፋሪዎች በነፍስ ወከፍ 28 ሺህ ብር ከፍለናል ይላሉ።
ሦስቱ ጓደኛሞች በአማካኝ 1፡45 ሰዓት ለሚወስደው የኢኮኖሚ ክፍል በረራ ደርሶ መልስ በድምሩ 84 ሺህ ብር ከፍለዋል።
እርግጥ ነው የአውሮፕላን በረራ ዋጋ በተሳፋሪ የበረራ ቀን እና ሰዓት እንዲሁም ‘በኢኮኖሚ እና በቢዝነስ ክፍሎች’ ምርጫ ይለያያል።
ቢሆንም በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ በአህጉረ አፍሪካ የአውሮፕላን በረራ አቅሙ ያላቸው የሚጓዙበት እየሆነ ነው።
ስሙን እንድንጠቅስ ያልፈለገ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ከናይሮቢ ወደ አዲስ አበባ የበረራ ዋጋ የማይቀመስ በመሆኑ “በሞያሌ በኩል በባስ አገር ቤት ደርሼ መጥቻለሁ” ይላል።
የኬንያ አየር መንገድ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ለበረራ ብዙ በማስከፈል ከአፍሪካ ቁንጮው ሆኖ ብቅ ብሏል።
አየር መንገዱ አፍሪካ ውስጥ አሉ ከሚባሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ እንዲሁም ከፈረንሳዩ ኤር ፍራንስ የላቀ ገንዘብ ለቲኬት ያስከፍላል ተብሏል።
ኬኪው (KQ) በተሰኘ ምሕፃረ ቃል የሚታወቀው የጎረቤት አገር ኬንያ አየር መንገድ ውድ ነው የተባለው ወደ 24 የአፍሪካ አገራት ሲበር የሚያስከፍለው ዋጋ ተጠንቶ ነው።
አፍሪካን ኮምፒቲሽን ፎረም የተሰኘው ድረ ገጽ የኬንያ አየር መንገድ ለአገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ በረራ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል ሲል ፅፏል።
ነገር ግን የደቡብ አፍሪካው እና የኢትዮጵያ አየር መንገድም እንዲሁ እጅግ ብዙ ለቲኬት ከሚያስከፍሉ የአፍሪካ አየር መንገዶች መካከል ናቸው።
የኮቪድ ወረርሽኝ እና የዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ የአውሮፕላን በረራ ዋጋ ጭማሪ ቢያሳይም በተለይ የአፍሪካ በረራዎች እጅግ መወደዳቸው ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ ሆኗል።
በቅርቡ በዩናይትድ ኪንግደሙ ብሪቲሽ ኤርዌይስ ወደ ናይሮቢ ደርሶ መልስ የቆረጠው ዙሪች 800 ፓውንድ ገደማ እንደከፈለ ይናገራል።
በተቃራኒው በቅርቡ የሚካሄደውን የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫን ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ ለማቅናት ያቀደችው ሚሼል የቲኬት ዋጋው ከ800 ዶላር በላይ እንደሆነባት በትዊተር ገጿ ፅፋለች። ይህ አሁን ባለው የምንዛሪ ዋጋ 97 ሺህ ሽልንግ ገደማ ነው።
ከኮቪድ ወረርሽኝ በፊት ከናይሮቢ አዲስ አበባ ደርሶ መልስ በኢትዮጵያ አየር መንገድም ይሁን በኬንያ ኤርዌይስ ለመብረር ከ19 ሺህ እስከ 25 ሺህ ሽልንግ ይጠይቅ ነበር።
አሁን ግን ከ80 ሺህ ሽልንግ በላይ ይጠይቃል።
ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? የነዳጅ ዋጋ ወይስ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት?

ኮቪድ እና ጦርነት
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና የኦፕሬሽን ኦፊሰር [ሲኦኦ] ለማ ያደቻ፣ ለዚህ አንዱ ምክንያት የሌሎች አገራት መንግሥታት የሚጡልብን “ግብር” ነው ይላሉ።
አቶ ለማ እንደሚሉት የአየር በረራ ዋጋ የሚተመነው በሚያስወጣው ወጪ ላይ ተመርኩዞ ነው። ለዚህም አየር መንገዳቸው ወደ ተለያዩ አገራት ሲጓዝ የሚያወጣውን ወጪ አስልቶ እንዲሁም አየር መንገዱ የሚያቀርበውን አገልግሎት ከግምት አስገብቶ ዋጋ ይተምናል።
ይህንን በምሳሌ ሲያብራሩ አንድ ሰው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጥታ ከደቡብ አፍሪካ ሲመጣና ከደቡብ አፍሪካ ተነስቶ ናይሮቢ አርፎ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ምቾቱ አንድ አይደለም ይላሉ።
“አውሮፕላኑ ቀጥታ ከመምጣት ይልቅ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ እያቆራረጠ የሚጓዝ ከሆነ ይህ አንድን መንገደኛ ምቾት ይነሳል። ስለዚህ ቀጥታ ሲመጣ ዋጋው ይጨምራል፤ እያቆራረጠ ሲመጣ ደግሞ ዋጋው ሊቀንስ ይችላል” ይላሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብዛኛውን ጊዜ ከአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና የአሜሪካ አገራት ቀጥታ በረራ እንደሚያደርግ የሚናገሩት ኃላፊው፣ ይህ ማለት ደንበኞች ሳይጉላሉ በምቾት ይመጣሉ ማለት ነው። ስለዚህ በገበያው መሠረት ላቅ ያለ ክፍያ ሊከፍሉ ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ።
ኦፕሬሽን ኦፊሰሩ ሌላው ለበረራ ቲኬት ዋጋ መወደድ እንደ ምክንያት የሚያነሱት በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ መናሩን ነው።
አልፎም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የአየር ማረፊያ የአገልግሎት ክፍያ ከፍ ማለቱን ኃላፊው ይጠቅሳሉ።
አቶ ለማ፤ በአየር መንገዶች አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች መንገደኛ ከመመዝገብ ጀምሮ ለማሳፈር፣ ምግብ ለማቅረብ፣ ነዳጅ ለመሙላት፣ ለፅዳት ሥራ እና ለሌሎችም አገልግሎቶች የሚያስከፍሉት ዋጋ መጨመሩ ለቲኬት ዋጋ መናር ምክንያት ነው ይላሉ።
“እነዚህ ወጪዎች እየጨመሩ በሚመጡበት ጊዜ እኛ ደግሞ የሚያካክስ ክፍያ እንጠይቃለን።”
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራሱን የሚያስተዳድረው ራሱ በሚያገኘው ገንዘብ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ለማ፤ “ሠርቶ ከሚያገኘው ገቢ ደግሞ ወጪውን መሸፈን ይኖርበታል” ይላሉ።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 1
በፈረንጆቹ 2022 የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው የቲኬት ዋጋ ጭማሪ ያሳየው በተለያዩ ምክንያቶች ነው ሲሉ የኬንያ ኤርዌይስ ኃላፊ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ የኬንያ ኤርዌይስ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ፌሊክስ ምዋንጋንጊ የቲኬት ዋጋ ገበያ ላይ ባለው ፍላጎትና አቅርቦት ላይ የተወሰነ ነው ይላሉ።
ፌሊክስ እንደሚሉት ከኮቪድ በፊት ኢንዱስትሪው ድጎማ ያገኝ ነበር። ነገር ግን በድኅረ-ኮቪድ ይህ ድጎማ እምብዛም አይደለም።
ኃላፊው እንደሚገልጹት በተለይ በአህጉረ አፍሪካ ያለው አቅርቦት በተወሰኑ አየር መንገዶች ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ የቲኬት ዋጋው ላይ ለውጥ ታይቷል።
“አፍሪካ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አየር መንገዶች ጥቂት ናቸው። ይህ ማለት አቅርቦቱ የተወሰነ ነው ማለት ነው። ይህ በተዘዋዋሪ የበረራ ዋጋ እንዲወደድ ያደርጋል።”
ኃላፊው ከኮቪድ በኋላ የፍላጎት ጭማሪ መታየቱን ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎ የቲኬት ዋጋ ከፍ ማለቱን ይናገራሉ።
አክለው ደንበኞች አፍሪካ ውስጥ ለሚደረግ በረራ ከየትኛው የዓለም ክፍል ሆነው ቲኬት ቢቆርጡ ዋጋው ተመሳሳይ ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገዱ ኃላፊ አንደኛው የድርጅቱ ዓላማ “ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ደንበኞችንና ኢትዮጵያውያንን ማገልገል ነው” ካሉ በኋላ “በአጠቃላይ ኦፕሬሽኑ ትርፋማ ሲሆን በአንዳንድ የበረራ መስመሮች በኪሳራም ይሁን ከሌሎች መስመሮች በሚገኘው ትርፍ እንሠራለን” ይላሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወዳዳሪዎች አንዳንድ ጊዜ ዝቅተኛ ዋጋ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ የሚያምኑት ኃላፊው “ብሔራዊ አየር መንገድ ከሆነ በአገሩ መንግሥት ሊደገፍ ይችላል።”
“እንደምታውቁት በኮቪድ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድና አንድ ሌላ ድርጅት ናቸው ከኪሳራ ማገገሚያ ገንዘብ [bailout] ያልተቀበሉት። እኛ ወጨያችንና ገቢያችንን በደንብ አመዛዝነን ነው የምንሠራው።”
ኃላፊው፤ የቲኬት ዋጋ ቲኬቱ በሚቆርጥበት ወቅት ላይ የተመሠረት ሊሆን እንደሚችልም ይገልጣሉ።
ለምሳሌ አንድ ደንበኛ ቲኬቱን የገዛው በረራው ከሚደረግበት ጊዜ ከስድስት ወራት በፊት ከሆነ ዋጋው የሚቀንሰው አየር መንገዱ ብሩን ተቀብሎ ስለሚሠራበት ይህ ታሳቢ ተደርጎ ቅናሽ እንደሚኖረው ያብራራሉ።
በተቃራኒው ቲኬቱ የተቆረጠው ለበረራው ቅርብ በሆነ ጊዜ ከሆነ ‘ቢድ ፕራይሲንግ’ በተባለው መንገድ እንደሚሸጥ ይጠቅሳሉ።
‘ቢድ ፕራይሲንግ’ ምን እንደሆነ የሚያብራሩት አቶ ለማ፤ ይህ ማለት ደንበኞች በቀሩት ወንበሮች ይወዳደሩ እና የተሻለ ዋጋ የከፈለ ያገኘዋል ማለት ነው።
ፌሊክስ፤ ልክ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር ለማ ያደቻ ሁሉ ደንበኞች የጉዞ ቀን ሲቃረብ ቲኬት የሚቆርጡ ከሆነ ዋጋው ከፍ ሊልባቸው እንደሚችል ይገልጻሉ።
ማኔጀሩ አክለው ‘አይታክስ’ [አይ ገቨርንመንት] ታክስ ተብሎ የሚታወቀው የግብር ዓይነት ለቲኬት ዋጋ መወደድ አስተዋፅዖ እንዳለው ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ይህ ማለት አየር መንገዶች ለሚያርፉበት አገር መንግሥት የሚከፍሉት የአገልግሎት ክፍያ ነው።
“ለምሳሌ ከናይሮቢ ወደ ኢንቴቤ [ኡጋንዳ] ሲኬድ ለመንግሥት የሚከፈል የመነሻ ክፍያ አለ። ይህ የበረራ ዋጋ ላይ ለውጥ ያመጣል። አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት ግብር ከቲኬቱ ዋጋ አስከ 30 በመቶ ይደርሳል።”

“የመንግሥታት ግብር”
እየተገባደደ ያለው የፈረንጆቹ 2022 በአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ በጉዞ መሠረዝ፣ በዕቃዎች መጥፋት እና በበረራዎች መዘግየት ምክንያት ደንበኞች እጅግ የተጉላሉበት ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል።
በርካታ አየር መንገዶች ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት የነበራቸውን ገቢ እና የበረራ ቁጥር ለማሳደግ በሚል በወሰዱት እርምጃ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ማኅበር [IATA] ዋና ሥራ አስኪያጅ ዊሊ ዌልሽ የነዳጅ ዋጋ በመጨሩ ምክንያት የበረራ ቲኬት ዋጋ “ያለጥርጥር ይጨምራል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ማኅበሩ እንደሚለው በፈረንጆቹ 2021 የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስሯል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር እንደጠቀሱት ድጎማ ካለገኙ ጥቂት አየር መንገዶች መካከል የሆነ አየር መንገደዱ [ኢቲ]፣ በወረርሽኙ ወቅት በጭነት አውሮፕላኖች ምክንያት ትርፋማ መሆኑን አውጆ ነበር።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአፍሪካ ቁንጮ የሚባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ ሌሎች ዋና ዋና አየር መንገዶች የቲኬት ዋጋቸው የማይቀመስ ሆኗል።
የበርካታ ደንበኞች ቅሬታ የሆነው የቅርብ ርቀት በረራዎች ዋጋ እጅግ መናር ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዚህ ማብራሪያ ይኖረው ይሆን?
ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰሩ አቶ ለማ ለዚህ ምክንያቱ ‘ፌቬኒው ማኔጅመንት’ ነው ይላሉ።
“ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ወደ አሥመራ ስንበር፣ አሥመራ ላይ የምንከፍላቸው ክፍያዎች አሉ። መንግሥት የሚጥለው ግብር ማለት ነው።”
እንግሊዝ ውስጥ የአየር ማረፊያ ታክስ በጣም ከፍተኛ ነው የሚሉት ኃላፊው ውሃ መቀየር፣ ነዳጅ መሙላት እና ሌሎች መሬት ላይ የሚከናወኑ ሥራዎችን የሚሠሩ ድርጅቶች ክፍያቸው ላቅ ያለ እንደሆነ ይናገራሉ።
አብዛኛውን ጊዜ አየር መንዱ ራቅ ወዳሉ፣ እንደ አውሮፓ እና አሜሪካ ሲጓዝ አማራጮች ስላሉት ዋጋቸው ተመጣጣኝ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር እንደሚሠራ የሚናገሩት ኃላፊው፣ በአፍሪካ አገራት ግን ‘በሞኖፖሊ’ ስለተያዘ የዋጋ ልዩነት ያመጣል ይላሉ።
“እንዳለመታደል ሆኖ አየር መንገዱ በቀዳሚነት በሚሠራባቸው የአፍሪካ አገራት ወጪው (ኮስት ኦፍ ቢዝነስ) በጣም ከፍተኛ ነው የሚሉት ኃላፊው፣ በዚህ ምክንያት የቲኬት ዋጋ እንደተወደደ ያስረዳሉ።
በተለያዩ አገራት ያሉ የታክስ ሕጎች ለቲኬት ዋጋ መጨመር ሚና እንዳላቸው በማንሳት፣ አንዳንድ አገራት የገቢ ግብር ጭምር እንደሚያስከፍሉ ይናገራሉ።
“በኢትዮጵያ መንግሥት እና በረራው በሚደረግበት አገር መንግሥት መካከል ታክስ አለመጠየቅ ስምምነት ካለ ታክሱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንጂ ውጪ አገር አንከፍልም።”
ነገር ግን ይህ ስምምነት ከሌለ የቲኬት ዋጋው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ኃላፊው ያብራራሉ።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 2
በኢትዮጵያ የኬንያ ኤርዌይስ ኃላፊ የሆኑት ፌሊክስም፣ አንዳንድ ጊዜ አጭር ርቀት የሚጓዝ በረራ ከረዥሙ የሚወደድበትን ምክንያት ያስረዳሉ።
ለምሳሌ ይላሉ ኃላፊው፤ “ወደ ዱባይ የሚደረግ በረራ ረዥም ሰዓት ይወስዳል። ስለዚህ አንድ አሊያም ሁለት ሰዓት ከሚወስድ በረራ የላቀ ዋጋ ሊኖረው ይገባል ማለት አይደለም።”
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከናይሮቢ ዱባይ የሚያደርገው በረራ፤ ከናይሮቢ አዲስ አበባ ከሚያደርገው ያነሰ የቲኬት ዋጋ ነው ያለው።
ከናይሮቢ አዲስ አበባ በአማካኝ ከአንድ ሰዓት ተኩል እስከ ሁለት ሰዓት ሲወስድ፣ ከናይሮቢ ዱባይ የሚደረግ በረራ 6 ሰዓታት ሊፈጅ ይችላል።
የኬንያ ኤርዌይስ በረራም በተመሳሳይ ለአጭር ርቀት በረራ የሚያስከፍለው ክፍያ ላቅ ያለው ነው የሚል ወቀሳ ይደርስበታል።
ፌሊክስ፤ ይህ የሚሆነው ‘ቫሊዩ ቤዝድ ፕራይሲንግ’ ስለምንጠቀም ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
“እኔ የማቀርበው አገልግሎት ዋጋ እና ገበያው ላይ ያለው ዋጋ ምን ያህል ነው? የሚለው ይታያል። ይህ ዋጋ ገበያ ላይ ባለው ውድድር የሚወሰን ይሆናል። ስለዚህ ረዥም ርቀት ያላቸው በረራዎች ከአጭር ርቀቱ በተነፃፃሪ ዝቅተኛ ዋጋ እንዲኖራቸው የሚያደርገው ያለው የአቅርቦት አቅም ነው።”
ኃላፊው ሌላው ለአጭር ርቀት በረራዎች መወደድ ምክንያት ነው የሚሉት አገልግሎቱን የሚሰጡት ድርጅቶች ቁጥር ውሱን መሆኑ ነው።
ከአዲስ አበባ-ናይሮቢ፤ ከናይሮቢ-አዲስ አበባ፤ የሚደረገውን በረራ በምሳሌነት የሚያነሱት ፌሊክስ ይህን አገልግሎት የሚሰጡት ‘ኬኪው’ እና ‘ኢቲ’ ብቻ ናቸው ይላሉ።
ከሌሎች አገራት የሚነሱ አየር መንገዶች ይህ አገልግሎት ሊሰጡ ቢችሉም የሚወስዱት ሰዓት ግን ረዥም ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ።
አጭር ርቀት በረራ የሚሰጡ አየር መንገዶች ጥቂት መሆናቸው ውድድር ስለማይኖር ዋጋ ከፍ እንዲል እንደሚያደርገው ነው የሚገልጹት።
ደንበኞች ወደ መዳረሻቸው ቀጥታ ሳይሆን አቆራርጠው ሲሄዱ ዋጋ የሚቀንሰው የሚወስድባቸው ሰዓት ከቀጥታ በረራ ከፍ ያለ ስለሆነ ነው የሚል ትንታኔ ይሰጣሉ።
የበረራ ዋጋ ወደፊት ይቀንስ ይሆን?
አሁን ባለው ሁኔታ የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ የመቀነሱ ነገር ከባድ እንደሆነ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ተንታኞች ይናገራሉ።
ኤሜሬትስ፣ የጃፓን አየር መንገድ፣ ኤር ኤዥያ. . . በቲኬቶቻቸው ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ካሳዩ አየር መንገዶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ፣ በነዳጅ ዋጋ መናር እና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ባሉ ግጭቶች ምክንያት የተሰቀለው የበረራ ዋጋ በቅርቡ ይወርዳል ተብሎ አይገመትም።
ፌሊክስ ግን ምናልባት “ከአንድ ዓመት በኋላ” የሚል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
“አየር መንገዶች አሁን ያለው ዋጋ ባለበት ይቀጥል ወይስ ገበያው ላይ ሌሎች አየር መንገዶች ይጨመሩ የሚል ጫና አለባቸው።”
ፌሊክስ፤ ገበያው ላይ ተጨማሪ አየር መንገዶች እንዲመጡ ማድረጉ ዋጋውን ያረጋጋዋል የሚል እምነት አላቸው።
“ይህ በዓመት ሁለት ጊዜ ይጓዝ የነበረ መንገደኛ በእጥፍ እንዲጓዝ ያስችለዋል ማለት ነው። ነገር ግን የበረራ ዋጋ ምናልባት ለአንድ ዓመት ባለበት የሚቀጥል ይመስለኛል። ምክንያቱም አየር መንገዶች ኪሳራታቸውን መመለስ ይፈልጋሉ።”
ነገር ግን ደንበኞች ሁለት አማራጮችን ተጠቅመው የተሻለ የበረራ ዋጋ ሊያገኙ እንደሚችሉ ኃላፊው ይጠቁማሉ።
አንደኛው ‘ፕሮሞሽናል ፌር’ [የማስታወቂያ ቅናሽ] መጠቀም ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ጉዞን አስቀድሞ በማቀድ በቅናሽ ቲኬት መቁረጥ ነው።












