የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርትራውያን ተጓዦች የገጠማቸው የቴክኒክ ችግር መሆኑን አስታወቀ

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርትራውያን መንገደኞች በኢንተርኔት አማካይነት ጉዞን ቅድሚያ ማረጋገጥ (ቼክ ኢን) ያልቻሉት በተፈጠረ ጊዜያዊ የቴክኒክ ችግር መሆኑን አስታወቀ።

ከሰሞኑ አየር መንገዱ የኤርትራ ፓስፖርት የያዙ መንገደኞች በኦን ላይን ቼክ ኢን እንዳያደርጉ እግድ አውጥቷል የሚሉ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያ መውጣታቸውን ተከትሎ ነው ችግሩ በሲስተም ላይ በተፈጠረ እክል የተነሳ ማጋጠሙን ለቢቢሲ የገለጸው።

አየር መንገዱ፣ ኤርትራውያን መንገደኞችን ኦን ላይን ቼክ እንዳያደርጉም እግድም ሆነ የኤርትራንም ፓስፖርት ከሲስተሙ ዝርዝር አውጥቷል መባሉን ለቢቢሲ በላከው ኢ-ሜይል ትክክል አይደለም ብሏል።

ጊዜያዊ ችግሩ የተፈጠረው ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (አይቲኤ) ከሚጠቀምበት ቲማቲክ ከተባለው ሥርዓት ጋር ተያይዞ ነው።

አይቲኤ ቲማቲክ አየር መንገዶች እና የጉዞ ወኪሎች ለመዳረሻዎቻቸው እንዲሁም ለማንኛውም የመተላላፊያ አገራት ተሳፋሪዎች አስፋላጊውን የጉዞ ሰነድ ለማረጋገጥ የሚጠቀሙበት ሥርዓት ነው ።

ከአይቲኤ ቲማቲክ የቀረበው መረጃ ያልተሟላ በመሆኑ በኢንተርኔት አማካይነት ጉዞን ቅድሚያ ማረጋገጫ ሥርዓት ላይ ጊዜያዊ ችግር ፈጥሯል ብሏል።

አገልግሎቶቹን ዲጂታይዝ ወይም በቀላሉ በኢንተርኔት እየሰጠ እንደሆነ የገለጸው አየር መንገዱ የኤርትራውያን መንገደኞች ጉዳይ ለሌሎች መንገደኞች ከሚሰጠው አገልግሎት የተለየ አይደለም ብሏል።

“ሁሉም ተጓዦቻችን በኢንተርኔት ላይ ገብተው ቼክ ኢን እንዲያደርጉና የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው እንፈልጋለን” ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሁኑ ጊዜ ችግሩን ለማቅረፍ እየሰራ እንደሆነ የገለፀው አየር መንገዱ፣ ኤርትራውያን መንገደኞችም በቅርቡ በኦንላይን ቼክ ኢን ማድረግ እንደሚችሉም ለቢቢሲ አስረድቷል።

ሌላኛው ኤርትራውያን መንገደኞች ያነሱት ጉዳይ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽን ኤርትራውያንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ፓስፖርት የያዙ መንገደኞች አዲስ አበባ ሲደርሱ “ቪዛ በመዳረሻቸው” ይሰጣቸዋል ቢልም ኤርትራውያን መንገደኞችን አግልሏል የሚል ነው።

ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከየትኛውም አገር ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ የኤርትራ ፓስፖርት ለያዙ መንገደኞች በኢንተርኔት ቼክ ኢን የቪዛ ዝርዝር መረጃ መጠየቁን ተከትሎ ነው።

ይህንንም አስመልክቶ አየር መንገዱም ለቢቢሲ በላከው ምላሽ ኤርትራውያን መንገደኞች ኢትዮጵያ ሲደርሱ ቪዛ ማግኘት እንደሚችሉና ቪዛም ቀድመው ማግኘት እንደማይጠበቅባቸው ገልጿል።

ኤርትራውያን መንገደኞች በአሁኑ ወቅት እያጋጠማቸው ያለው ጉዳይ ከኦንላይን ቼክ ኢን ሥርዓት ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የቴክኒካል ችግር ጋር የተያያዘ ነው ብሏል።

ሌላኛው ከሰሞኑ የተነሳው ጉዳይ ከአዲስ አበባ ወደ አሥመራ በብቸኝነት የሚበረው የአየር መንገዱ ዋጋ ጋር ተያይዞ ነው።

ተጓዦች አንድ ሰዓት ከ40 ደቂቃ ለሚወስደው የአየር ጉዞ እስከ 1ሺህ የሚጠጋ ዶላር እየተጠየቅን ነው በሚልም ሲያማርሩ ተሰምተዋል።

በተለይም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት የነበረውን የዋጋ ሁኔታ እያነሱ ዋጋው ተጋንኗል ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድም በምላሹ፣ ከወረርሽኙ በኋላ የአየር ቲኬቶች ዋጋ ላይ መጠነኛ ጭማሪ መታየቱን ጠቅሷል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ የአየር መንገድ የቲኬት ታሪፍ ዋጋ ከሁለት ዓመት በፊት (ከኮሮናቫይረስ ከወረርሽኝ በፊት) ከነበረው ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጿል፤ በወቅቱም ለአንድ ጉዞ የነበረው 279 ዶላር መሆኑን አስታውሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአየር ቲኬት ዋጋ በወቅቱ ሁኔታ እና መቀመጫዎች መኖራቸው ጋር ተያይዞ ሊለያይ እንደሚችልም አስገንዝቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ75 ዓመታት በላይ አፍሪካውያንን አንድ ላይ ለማምጣት ሲጥር የቆየ አየር መንገድ መሆኑን አስታውሶ “አፍሪካውያን ወገኖችን ለመበዝበዝ አላማ የለውም” በማለት ምላሽ ሰጥቷል።

እንዲያውም ለአፍሪካ አየር መንገዶች የአስተዳደር እና የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጠም ነው ብሏል።

አየር መንገዱ ቴክኖሎጂው የደረሰበትን የላቁ አውሮፕላኖችን እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የደንበኞች አገልግሎት ለአፍሪካውያን በመስጠት ለማገልገል ኔትወርኩን በአህጉሪቱ በማስፋት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሷል።